
28 ህዳር 2024, 17:19 EAT
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከሰሞኑ እገዳ በተላለፈባቸው ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ “በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ” እንደሚያስተላልፍ አስታወቀ።
ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ “አንዳንድ ክስተቶች” ምክንያት “የሲቪል ምኅዳሩ ጠቧል ብሎ መደምደም” ተገቢ አለመሆኑን የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ተናግረዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እገዳ የተላለፈባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ ይህንን አስተያየት የሰጠው ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 19/2016 ዓ.ም. በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የተጣራው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ለአራተኛ ጊዜ የሚከበረውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት አከባበር የተመለከተ ነበር።
ይሁንና ጋዜጠኞች ከሰሞኑ የታገዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በመግለጫው ላይ ለተገኙት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የምክር ቤቱ አመራሮች አቅርበዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በኅዳር ወር በቀናት ልዩነት ውስጥ እግዶች ያስተለለፈው “የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)”፣ “የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች” እንዲሁም “ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ” በተባሉት ድርጅቶች ላይ ነው።
በሰብአዊ መብቶች እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚሠሩት እነዚህ ድርጅቶች የታገዱት “ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባ፤ ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርና የሕዝብ ጥቅምን የሚጎዳ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል” በሚል ምክንያት እንደሆነ ድርጅቶቹ ባወጧቸው መግለጫዎች አስታውቀዋል።
ካርድ እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፤ በባለሥልጣኑ የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመው። ካርድ እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ፤ እግዱ ተገቢውን የሕግ ሂደት “አልተከተለም” የሚል ወቀሳም አቅርበዋል።
በዛሬው መግለጫ ላይ የተገኙት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አህመድ ሁሴን፤ ምክር ቤቱ የሰሞኑን እግዶች በተመለከተ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እና ከታገዱ ድርጅቶች አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጉን ገልፀዋል። ጉዳዩ “በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ በዝርዝር” ሊናገሩ እንደማይችሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው በበኩላቸው፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሚቆጣጠራቸው ድርጅቶች ላይ “ክትትል እንደሚያደርግ” እና በሚደርስባቸው “ግኝቶች መሠረት ግብረ መልስ” እንደሚሰጥ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
- የኤርትራው አምባሳደር ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መቀዛቀዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወቀሱ28 ህዳር 2024
- “ወደ ቤታችን ልንመለስ ነው፤ ደስ ብሎናል” – በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን28 ህዳር 2024
- በጦርነት ምክንያት በርካታ ሕፃናት የሚሸሹባት አፍሪካዊት አገር28 ህዳር 2024

አቶ ፋሲካው፤ “ቀላል ጥፋት ከሆነ ቀላል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ‘ከባድ ጥፋት ነው’ ተብሎ እምነት ከተያዘበት ደግሞ ወደ ማገድ ደረጃ ሊደረስ ይችላል። ይህ አዋጃችን፣ ሕጋችን ላይ ያለ አሠራር ነው” ሲሉ የመሥሪያ ቤቱን አሠራር አንስተዋል።
ይሁንና ባለሥልጣኑ የሚያስተላልፈው እገዳ፤ ድርጅቱ “ጥፋተኛ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ገልፀዋል። እገዳ ከተጣለ በኋላ “ቀሪ ማጣራቶች” ተከናውነው “የመጨረሻ ውሳኔ” እንደሚተላለፍ አስረድተዋል።
ባለሥልጣኑ፤ ሰሞኑን እገዳ ከተላለፈባቸው ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር “በዝርዝር” ንግግር ማድረጉን የገለጹት አቶ ፋሲካው፤ “በእኛ በኩል ያለውን ጉዳይ አንስተናል። በእነሱ በኩል ያለውንም ጉዳይ አንስተው ሰፊ ውይይት አድርገናል። በአመዛኙ፤ በቀጣይ ማከናወን በሚገባን ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ነው የተለያየነው” ብለዋል።
ከድርጅቶቹ በተጨማሪ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋርም ውይይት ማደረጉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የድርጅቶቹን ጉዳይ “የሚያጣራ ቡድን” ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ እና የታገዱት ድርጅቶቹም “ትብብር እያደረጉ” መሆኑንም አክለዋል።
አቶ ፋሲካው፤ የሦስቱ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉዳይ “በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት” ያገኛል ብለው እንደሚያስቡ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ድርጅቶቹ ላይ ረጅም ጊዜ እገዳ ቆይቶ የማይመለስ ጉዳት እንዳይደርስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማጣራቱ ሥራ ተጠናቅቆ፤ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚወሰን ተስፋ አድርገን፤ በዚያው መንገድ ተግባብተን እየሠራን ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተላለፈው እገዳ “ሕጋዊ ሂደቱን ያልጠበቀ ነው” የሚለውን ወቀሳ አጣጥለዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፤ ክትትል የሚያደርግባቸው ድርጅቶች ላይ ቀላል ጥፋት ሲገኝ “ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ” እንዲሁም “ከባድ ጥፋት” ሲሆን እስከ ሦስት ወር ድረስ የማገድ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን እንዳለው ገልጸዋል። አቶ ፋሲካው፤ ድርጅቶች “ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው የመፍረስ ውሳኔ ሊወሰንባቸው” የሚችልበት አሠራርም እንዳለ አንስተዋል።
“ተጨባጭ ማስረጃ እና ወንጀል ውስጥ የመግባት ዓይነት ነገር ከሆነ ደግሞ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠው ለቦርዱ ጋር ቀርቦ የፈረሰ አንድ ድርጅት አለ። እስካሁን ባለው ሂደት የፈረሱ ድርጅቶች በጣም ጥቂት ናቸው” ብለዋል።
“ስለዚህ ውሳኔዎች ደረጃ በደረጃ ነው የሚሄዱት የሚል የሕግ መከራከሪያ የለም፤ እርሱ ትክክል አይደለም” ሲሉ በመሥሪያ ቤታቸው እርምጃ ላይ ቀረበውን ወቀሳ ተከላክለዋል።
አቶ ፋሲካው፤ ከዚህ በፊት የታገዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጉዳይ በተመለከተም “በአንዳንድ ክስተቶች የሲቪል ምኅዳሩ በቃ ጠቧል ዋጋ የለውም ብሎ መደምደም ደግሞ ትክክል ነው ብዬ አልወስድም” ሲሉ ተደምጠዋል።