በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ዮሃንስ ተክለሚካኤል
የምስሉ መግለጫ,በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ዮሃንስ ተክለሚካኤል

28 ህዳር 2024, 12:10 EAT

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ዮሃንስ ተክለሚካኤል ተናገሩ።

አምባሳደሩ ይህንን የተናገሩት ባልተለመደ ሁኔታ በብሪታኒያ የኤርትራ ኤምባሲ የዩቲዩብ ቻናል ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሲሆን፣ ቪዲዮው ይፋ ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ እንዲነሳ መደረጉን ቢቢሲ ትግርኛ አረጋግጧል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ተሻሽሎ የነበረ ሲሆን፣ የኤርትራ ወታደሮች ለሁለት ዓመት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፈው መዋጋታቸው ይታወሳል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም የሀገራቱ ግንኙነት ተቀዛቅዟል።

ይህንን በተመለከተ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ ባለሥልጣናት በኩል የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እና የስልክ ግንኙነት መቋረጥ ግንኙነቱ ስለመሻከሩ ማሳያ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ቆይቷል።

በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር ዮሃንስ ተክለሚካኤል ‘ኤርትራ ኤምባሲ ሚዲያ’ (Eritrea EmbassyMedia) ከተሰኘ የዩቱዩብ ቻናል ጋር ባደረጉት ያልተለመደ ቃለ መጠይቅ፣ ኤርትራ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት መልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግን “እንደ ቀድሞው አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በለንደን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ በሚያስተዳድረው ዩቲዩብ ቻናል ላይ በትግርኛ ቋንቋ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መበላሸት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ተጠያቂ አድርገዋል።

“በአሁኑ ወቅት . . . አራት ኪሎ የሚገኘው. . . [ጠቅላይ ሚኒስትር] የሚፈጥራቸው ችግሮች በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ሞቶ እንዲቀበር እያደረጉ ናቸው” ሲል አምባሳደሩ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ችግር እንደገጠመው አመልክተዋል።

አምባሳደሩ ቃለምልልስ ከሰጡበት ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ፎቶ
የምስሉ መግለጫ,አምባሳደሩ ቃለምልልስ ከሰጡበት ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ፎቶ

በቃለ ምልልሱ ላይ አምባሳደር ዮሃንስ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ሚና ሊኖራት ይገባል በሚል የያዙትን አጀንዳ በማንሳት የተቹ ሲሆን “የማይጨበጥ ህልም በመያዝ አሁን ተመልሶ የኤርትራን ነጻነት አላስፈላጊ ወደ ሆነ ነገር ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት ቀጠናው ላይ ጫና ፈጥሯል” ብለዋል።

አምባሳደሩ በተደጋጋሚ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረውን ውጥረት በማንሳት ኢትዮጵያ በቀጠናው አለመረጋጋት እየፈጠረች ነው ሲሉ በይፋ ከስሰዋል።

በደቡብ ሱዳን የኤርትራ አምባሳደር በአፍሪካ ቀንድ ተፈጥሯል ለሚሉት ቀውስ በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] . . . ቀጣናውን አውኮታል። አውኮታል ብቻ ሳይሆን . . . ሀገሪቷን በህልም ለማስተዳደር ነው የሚጥረው” ሲሉ ተችተዋል።

በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በተደረገው ቃለ ምልልስ ላይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ግንኙነት በተመለከተ የጠቀሱት አምባሳደሩ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደነበረው አለመሆኑን ገልጸዋል።

ይህ በደቡብ ሱዳን ኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ዮሃንስ ተክለሚካኤል የሰጡት ቃለ ምልልስ በአሁኑ ጊዜ ከዩቲዩብ ቻናሉ ላይ የተነሳ ሲሆን፣ ምክንያቱም አልተገጸም።

በቃለ ምልልሱ ላይ ስለተነሱት ጉዳዮች ከኤርትራ በኩል ማስተባበያም ሆነ ማብራሪያ ያልተሰጠ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ በኩልም የተባለ ነገር የለም።

ኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መድረሷን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገባች በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በተደጋጋሚ ወደ ኤርትራ በመጓዝ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ኤርትራ የሶማሊያን ሉዓላዊነትን እንደምትደግፍ መግለጿ ይታወሳል።

በተጨማሪም በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ እየተወዛገበች ያለችው ግብፅ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ጋር የጋራ ትብብር ስምምነት በቅርቡ አሥመራ ውስጥ መፈረማቸው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ችግር ውስጥ ከገቡት ሀገራት ጎን ለመሰለፍ መወሰኗን አመላካች እንደሆነ ሲገለጽ ነበር።

ዩቲዩብ
የምስሉ መግለጫ,ከዩቲዩብ ላይ የተነሳው የቃለምልልሱ ቪዲዮ