በጨለማ የተዋጠው የዚምባብዌ ፓርላማ

ከ 5 ሰአት በፊት

በዚምባብዌ ፓርላማ የፋይናንስ ሚኒስትሩ ምቱሊ ንኩቤ ስለበጀት ንግግር እያደረጉ ሳለ መብራት ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ በጨለማ ተውጦ እንደነበር ተዘገበ።

በፓርላማው ይህ ክስተት ያጋጠመው መብራቱ ብልጭ ድርግም የማለት ምልክት ካሳየ በኋላ ነው የጠፋው።

በዚህም ምክንያት ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣ ምክትል ፕሬዝደንት ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ እና ሌሎች የፓርላማ አባላት ጨለማ ውስጥ ለመቀመጥ ተገደዋል።

መብራት በፈረቃ እያደለች ያለችው ዚምባብዌ በመብራት እጦት መፈተን ከጀመረች ሰንበትበት ብላለች።

መንግሥት በአገሪቱ በቀን ለ12 ሰዓታት ብቻ መብራት በፈረቃ እንዲታደል ያደረገ ሲሆን፣ ካሪባ የተባለው ግድብ በድርቅ ምክንያት ውሃ ማቆር አለመቻሉ ችግሩን አባብሶታል።

በፓርላማው መብራት ሲጠፋ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሁኔታው ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው ሲሉ ጩኸት አሰምተዋል።

የዚምባብዌ መብራት አቅርቦት ባለሥልጣን ኃላፊ ጆርጅ ማንያያ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት በፓርላማው መብራት የጠፋው ታቅዶበት አይደለም።

ዚምላይቭ ለተባለው ጣቢያ ቃለ ምልልስ የሰጡት ኃላፊው እንዳሉት የሀገሪቱ ፓርላማ ከፈረቃ መብራት ውጪ ሲሆን የራሱ የሆነ የኤሌክሪክ ኃይል አቅርቦት አለው።

ኃላፊው እንደሚሉት በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት መብራት ሊጠፋ የቻለው በመብረቅ ምክንያት ነው።

ልክ መብራት ከመጥፋቱ በፊት ስለበጀት ሲተነትኑ የነበሩት የፋይናንስ ሚኒስትሩ በዘንድሮው ድርቅ ምክንያት የግብርናው ዘርፍ ሊጎዳ ይችላል ብለዋል።

ቢሆንም በዓመት ይዘንባል ተብሎ ከሚጠበቀው በላይ ዝናብ ሊዘንብ ስለሚችል የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት 6 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ ጠቁመው ብዙ መዝነቡ ለኤሌክትሪክ አቅርቦትም መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

ዚምባብዌያውያን ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታትም በኤሌክትሪክ አቅርቦት ምክንያት ሲቸገሩ ቆይተዋል።