
ከ 6 ሰአት በፊት
ከጥይት እና ከፍንዳታ ሲያመልጥ እንዲሁም የሀገራትን ብርቱ ምሥጢር ሲጠብቅ ይታያል።
ቦምባስቲክ በቅርቡ የሠራው የፕሮፖጋንዳ ፊልም ማክሲም ሹጋሌይ የተባለውን ገፀ-ባህሪ ጀግና የሩሲያ የፖለቲካ ሰው አድርጎ ይስላል።
ሰውዬው በውጭ ሀገራት ሀገሩን ለማስተዋወቅ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።
ምንም እንኳ ለፊልም ተብሎ ግነት ቢታከልበትም በእውነተኛው ዓለምም ቢሆን ይህ ሰው በአፍሪካ የሩሲያ ተፅዕኖ እንዲበረታ ብዙ አበርክቷል። በተለይ ይህ ተልዕኮው እንዲሳካለት ከሩሲያው ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ጋር ሠርቷል።
ዓላማውን ከማሳካት የሚያግደው ነገር የለም የተባለለት ግለሰብ በቅርቡ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቻድ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
እሱ እና ሳሜር ሱዌፋን እንዲሁም ኢ ሳርዮቭ የተባሉ ሌሎች ሰዎች ባለፈው መስከረም ክሱ ባልታወቀ ጉዳይ በቁጥጥር ሥር ውለው ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሀገራቸው መላካቸውን የሩሲያ ኤምባሲ አስታውቋል።
ማክሲም ሹጋሌይ ማነው?
ማክሲም ራሱን “ሶሲዮሎጂስት” ሲል ነው የሚገልፀው። ነገር ግን ተንታኞች በአፍሪካ ሥራውን እያስፋፋ ያለ የፖለቲካ ቀስቃሽ እና የሩሲያ ሰላይ ነው ይሉታል።
በአፍሪካ ሀገራት የቫግነር ቡድንን በማስተዋወቅ የተሳሳተ መረጃ አሠራጭቷል በሚል ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ በአውሮፓው ኅብረት ማዕቀብ ተጥሎበታል። በዩክሬንም ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሰዎች አንዱ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ ከሟቹ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ አጋር እና የቫግነር ቡድን መሪ ከነበረው ከሟቹ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ጋር አብሮ ይሠራ ነበር።
ምንም እንኳ ሹጋሌይ ልክ እንደሌሎቹ ከፕሪጎዢን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሰዎች ይህን ጉዳይ ቢያስተባብልም ለመጀመሪያ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ የሆነው የቫግነር ቡድንን ወክሎ በምርጫ ጣልቃ በመግባት በስለላ ክሶች ሊቢያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር በዋለ ጊዜ ነው።
ፕሪጎዢን ለሹጋሌይ የሰጠው ትዕዛዝ መረጃ እንዲያደራጅ እና ለቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝደንት ሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ‘ስትራቴጂ’ እንዲነድፍ ነው።
ሹጋሌይ ሩሲያ ሲመለስ 18 ሚሊዮን ሩብል አሊያም 173 ሺህ ዶላር እንደሰጠው ፕሪጎዢን ተናግሯል። በእስር ላሳለፋቸው እያንዳንዱ ወር 1 ሚሊዮን ሩብል ማለት ነው።
- የኤርትራው አምባሳደር ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መቀዛቀዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወቀሱ28 ህዳር 2024
- ከሀገር የሸሸው የቀድሞው የሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂ ምን ይላል?26 ህዳር 2024
- ምዕራባውያንን የሚያሰጋው የሩሲያ የኒውክሌር እና የሚሳዔል አቅም ምን ያህል ነው?27 ህዳር 2024

ሹጋሌይ በሊቢያ ያሳለፋቸው ቀናት ናቸው ፊልም ሆነው የቀረቡት። ፊልሙን ስፖንሰር ያደረገው ፕሪጎዢን ነው። ፊልሙ በምሥራቅ ሊቢያ የቫግነር አጋር የሆኑት ኻሊፋ አፍጣርን ማወደስ እና ሩሲያ በአፍሪካ የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች አሳምሮ ማቅረብ ነው።
ሹጋሌይን ሆኖ የተወነው ኪሪል ፖሉኺን ሲሆን ልክ “እንደ ጄምስ ቦንድ ወይም እንደ ሚሽን ኢምፖሲብል ዓይነት” ሆኖ ነው የቀረበው ይላሉ የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኙ ላድ ስቴዋርት።
“ፊልሙ ላይ የምናየው ሰው በጣም ጠንካራ እና በማንኛውም ሁኔታ ብሔራዊ ምሥጢርን አሳልፎ የማይሰጥ ነው። ደግሞ ብቃት ያለው ቅጥር ነብሰ-ገዳይ እና ራሱን ችሎ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ማካሄድ የሚችል ሆኖ እናየዋለን።”
በ2018 ቢቢሲ ይፋ ያደረገው የምርመራ ዘገባ እንደሚያሳየው በርካታ የሩሲያ ሰላዮች በማዳጋስካር ምርጫ ለሚወዳደሩ ዕጩዎች በሻንጣ የታሸገ ገንዘብ ሲሰጡ ነበር።
ሹጋሌይ ከሩሲያ ውጭ መንቀሳቀስ ከመጀመሩ በፊት የሚታወቀው ሕይወት በ2022 የፒተርስበርግ ፓርላማ ምርጫ ወቅት የፖለቲካዊ አማካሪ ሆኖ መሥራቱ ነው።
በወቅቱ ሹጋሌይ ከዕጩዎች የአንዱ አማካሪ ነበር። በአንድ የምርጫ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ መዛግብት ማስረጃ ሆነው እንዳይቀርቡ ቦጫጭቆ በልቷቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሹጋሌይ ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው?
ፕሪጎዢን በሕይወት እያለ የሹጋሌይ ኃላፊነት የብሔራዊ ዕሴቶች ጥበቃ የተባለው የቫግነር አጋር የሆነ ድርጅትን መምራት ነበር።
ነገር ግን ኦፊሴላዊ ባልሆነ ደረጃ በአፍሪካ ሀገራት ለቫግነር ቡድን ምቹ ይሆናሉ የተባሉ አገዛዞችን ወደ ሥልጣን ማምጣት እና ሥልጣን ይዘው እንዲቆዩ ማስቻል ነበር ሥራው። ይህ እንቅስቃሴ ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ማጠናከር እና ፈረንሳይን ማስወገድ ነው ዓላማው።
ባለፈው ዓመት የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከሞቱ በኋላ ግን በቫግነር ሥር በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ እና በዩክሬን የሚዋጉ ወታደሮች የሩሲያ መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል።
በዚሁ የፕሪጎዢን የሚድያ አገዛዝ ተገረሰሰ። ሹጋሌይ የዚህ የሚድያ እንቅስቃሴ አባል ነበር።
ሹጋሌይ ብዙውን ጊዜ በድብቅ ስለሚንቀሳቀስ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደነበረው ማወቅ ከባድ ነው።
ቢሆንም አንዳንዶች እንደሚሉት ፕሪጎዢን ቢሞትም ሹጋሌይ አሁንም ያለው ተፅዕኖ ካለፈው ጊዜ ያነሰ አይደለም።
“ክሬምሊን የቫግነር ቡድን እንቅስቃሴን ብትረከብም ሹጋሌይ ግን አሁንም ያለው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም” ከፍተኛ የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆነችው ቢቨርሊ ኦቺየንግ ትናገራለች።
ሰውዬው ከፕሪጎዢን እና ከቫግነር ቡድን ጋር ያለውን ቁርኝት አይክድም። የቴሌግራም ቻናሉ የሟቹ አለቃውን ሥራ በሚያሞግሱ ፅሑፎች የተሞላ ነው። አንዳንድ ጊዜ የቫግነር ቡድን አባል ለመሆን የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችንም ይለጥፋል።
ቻድ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ባለፈው ሐምሌ ወደ አንጎላ ሲጓዝ የነበረውን ሒደት በቴሌግራም ገፁ አስፍሯል። አሁን ስላለበት ሁኔታ በልበ-ሙሉነት ማውራት ከባድ ነው።

ቻድ ውስጥ የታሰረው ለምንድነው?
ቻድ ሹጋሌይ እና ሁለቱ አጋሮቹን ለምን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለች በይፋ የሰጠችው መግለጫ የለም።
ይህን የተመለከቱ በርካታ ፅንሰ-ሐሳቦች ይወጣሉ። አንዳንዶቹ ተዓማኒነት አላቸው። ሌሎቹ ውሀ አያነሱም።
የሩሲያ መንግሥት ጣቢያ የሆነው አርቲ እንደሚለው ግለሰቡ የታሰረው በፈረንሳይ ትዕዛዝ መሠረት ነው። ኦቺየንግ ግን ይህ እውነት ብለው አያምኑም።
ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ሩሲያ የምዕራቢ ዓለም በቻድ ያለውን ተፅዕኖ እየቀዘቀዘ ነው የሚል ሐሳብ እያንሰራፋች ነው።
ምንም እንኳ ቻድ በቅርቡ ከሩሲያ ጋር በመሠረተ-ልማት እና ደኅንነት ጉዳዮች ለመተባበር ስምምነት ብትፈራረምም አሁን የፈረንሳይ ወታደሮች ቻድ ውስጥ አሉ። የፈረንሳይ የቀድሞ ግዛት የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ከፓሪስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ቢሻክርም ቻድ እና ፈረንሳይ መልካም ግንኙነት አላቸው።
ሩሲያ በቻድ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ይኑራት አይኑራት ግን አይታወቅም።
አንዳንዶች የቻድ ፕሬዝደንት ማሕማት ዴቢ ሩሲያ እና ምዕራባዊያንን እያነካኩ ለቻድ የተሻለ ነገር ለማምጣት እየሞከሩ ነው ይላሉ።
ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪብሊክ የተነሱ የቫግነር ወታደሮች ወደ ቻድ ገብተው ግጭት ከተነሳ በኋላ አፈግፍገው መውጣታቸው ተነግሮ ነበር።
ሩሲያ ከቻድ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ከቻለት በምዕራብ አፍሪካ ያላት ተፅዕኖ መጠነ ሰፊ ይሆናል ማለት ነው።
ሹጋሌይ ቻድን ሁለት ጊዜ ከጎበኘ በኋላ ባለፈው ግንቦት ከተደረገው ምርጫ በፊት ከፕሬዝደንት ዴቢ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ጋር ውይይት አድርጓል።
ባለፈው ዓመት የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ባወጡት ሪፖርት የቫግነር ቡድን ፕሬዝደንት ዴቢን ለመግደል አሲረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል ይላል።
ሹጋሌይ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ መላ ምቶች ይሰማሉ።
የሹጋሌይ እርዳታ ድርጅት ሰውዬው የቫግነር ሰላይ ነው መባሉን አስተባብሎ “ሹጋሌይ የቫግነር ቡድን በአፍሪካ ስላለው እንቅስቃሴ የሚያውቀው ነገር የለም” ይላል።
ተንታኞች እንደሚሉት በሩሲያ የሚደገፉ ማኅበራዊ ሚድያ ገፆች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና የዜና ወኪሎች በአፍሪካ ስለሩሲያ የሚያቀነቅኑ ዘገባዎችን እየሠሩ ነው።
ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው አፍሪክ ሚደያ ቲቪ ነው። ከካሜሩን የሚያሰራጨው ጣቢያው በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር ይተላለፋል። በዩቲዩብ እና ፌስቡክ በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት።
ሹጋሌይ በቴሌግራም ገፁ የሚለቃቸው ቪድዮዎች ወደ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እንደሚጓዝ ያሳያሉ። መታየት የሚወድ ሰው መሆኑንም ይጠቁማሉ።