
ከ 4 ሰአት በፊት
በአውስትራሊያ የሕጻናት እንክብካቤ ሠራተኛ የነበረ እና የከፋው የህጻናት ደፋሪ የሚል ስያሜ የተሰጠው ግለሰብ ወደ 70 የሚጠጉ ህጻናት ሴቶች ላይ የመድፈር እና ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸሙ የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነበት።
የ47 ዓመቱ አሽሊ ፖል ግሪፊት እአአ ከ2003 እስከ 2022 ባሉት ጊዜያት በአውስትራሊያዋ ኩዊንስላንድ ግዛት እና ጣሊያን ውስጥ በሚገኙ የህጻናት ማቆያ ማዕከላት 307 ወንጀሎችን መፈጸሙን አምኗል።
የደፈራቸው ህጻናት ዕድሜ ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት እንደሚደርስ ተነግሯል።
ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛው ፖል ስሚዝ የወንጀሎቹን መጠን እና ሁኔታ “አስነዋሪ” እና “አጸያፊ” በማለት ገልጸው “እምነት ተሸርሽሯል” ሲሉ ገልጸዋል።
ግሪፊት በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸም ተከሷል።
ዓርብ ላይ በብሪስቤን በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበው ግሪፊት “ህጻናት ላይ ወሲባዊ ፍላጎቶች የማሳደር (ፒዶፋይል) ስሜት ችግር” እንዳለው ለፍርድ ቤቱ የተገለጸ ሲሆን እንደገና ወንጀል ሊፈጽመበት የሚችልበት ከፍተኛ ስጋት ስላለ በሚል ዳኛ ስሚዝ ቢያንስ 27 ዓመታት ያለ ይግባኝ በጽኑ እስር እንዲቆይ ብይን አሳልፈዋል።
ግሪፊት ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ2022 በአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ ተይዞ የነበረ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ከአንድ ሺህ 600 በላይ ህጻናት ላይ የወሲብ ጥቃቶችን በመፈጸም ወንጀሎች ተከሷል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ውድቅ ተደርገዋል።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋትከ 6 ሰአት በፊት
- ፑቲን የዩክሬን ውሳኔ ሰጪ ማዕከላትን በአዲሱ ባለስቲክ ሚሳኤል እንደሚመቱ አስጠነቀቁከ 5 ሰአት በፊት
- የዚምባብዌ ፓርላማ ስለበጀት እየመከረ ሳለ መብራት ጠፋከ 5 ሰአት በፊት
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ታሪክ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል
ግለሰቡ ጥቃቶችን ከመፈጸም በተጨማሪ ቪዲዮዎችን በመቅረጽ በድብቅ ድረ ገጾች ላይ የለጠፋቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎችን መርማሪዎች አግኝተዋል።
ምንም እንኳን ቀረጻው ላይ ፊቱ እንዳይታይ ቢደረግም በቪዲዮዎቹ ላይ ባሉት እና ለኩዊንስ ላንድ ህጻናት ማቆያዎች በተሰጡ ልዩ የአልጋ ልብሶች ምክንያት ግሪፊዝት ሊደረስበት ችሏል።
28 መድፈር ክሶችን፣ ወደ 200 በሚጠጉ ህፃናትን ጥቃቶችን በመፈጸም፣ እና ከበርካታ የህፃናት ወሲባዊ ብዝበዛዎች ላይ በመሳተፍ እና ከማጋራት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን አምኗል።
ከተጎጂዎቹ መካከል አራቱ በእሱ ስር በሚተዳደረው እና በጣሊያን ፒሳ ውስጥ በሚገኝ የሕጻናት ማቆያ ጣቢያ ያሉ ሲሆኑ የተቀሩት 65ቱ ደግሞ በብሪስበን አውስትራሊያ ከሚገኙ 11 አካባቢዎች ናቸው።
ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ከማስተላለፉ በፊት ከግሪፊት ሰለባዎች እና ከወላጆቻቸው ብዙ አሳዛኝ ምስክርነቶች ተሰምተዋል።
ከመካከላቸው በመዋዕለ ሕፃናት ውስጥ ጥቃት የደረሰባቸው ሁለት እህትማማቾች የነበሩ ሲሆን ግሪፍት የምትወደው አስተማሪዋ እንደነበረች አንደኛዋ አስታውሳለች።
“እሱ ያደረገውን ነገር ማወቅ ልብ የሚሰብር ነው፤ በትንሹም ቢሆን እርስ በእርስ የሚጋጩ ስሜቶችን ይፈጥራል” ማለቷን ዘ ኩሪየር ሜይል ዘግቧል።
“አሁንም ቢሆን እንኳን ሁኔታውን መረዳት የምችል አይመስለኝም፤ ምክንያቱም በማስታውሰው እና በእውነታው መካከል ክፍተት አለ።”
ሌላዋ ሰለባው ደግሞ ድርጊቱ እንዴት የልጅነት ጊዜዋን እንደነጠቃት እና ለዓመታት ከአዕምሮ ህመም ጋር የነበራትን ትግል ተናግራለች።
“ህይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል በጭራሽ አላውቅም” ማለቷን በጋርዲያን አውስትራሊያ ዘግቧል።
“ሰዎችን ሳልፈራ ማደግ ምን እንደሚሆን በፍጹም ማወቅ አልችልም።”
ወላጆች በበኩላቸው በልጆቻቸው ላይ የተፈጸመባቸውን ወንጀሎች በማወቃቸው የተሰማቸውን ፍርሃት ለፍርድ ቤት ገልጸው በርካቶች ግሪፊትን በማመናቸው ራሳቸውን ይቅር ለማለት እንደታገሉ ተናግረዋል።
“(ልጄ) እንደ አጎት ትወድህ ነበር። አንተ ግን እንደ አሻንጉሊት ተጠቀምክባትት” ሲሉ አንድ ወላጅ መናገራቸውን ኒውስ ኮርፕ አውስትራሊያ ዘግቧል።
ሌላኛው ወላጅ ደግሞ በልጃቸው ላይ የደረሰውን በደል ከሷ ለመደበቅ እየሞከሩ እንደሆነ ገለጸዋል።
“የደረሰባትን መቀልበስ ባልችልም ግን በአእምሮዋ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ማለታቸውን ኩሪየር ሜይል ዘግቧል።