
ከ 5 ሰአት በፊት
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን መዲና ኪዬቭ የሚገኙ ውሳኔ ሰጪ ማዕከላት ላይ ኦሬሽኒክ በተሰኘው አዲሱ የአገሪቱ የባለስቲክ ሚሳኤል እንደሚመቱ አስጠነቀቀቁ።
ዩክሬን ከአሜሪካ የተለገሰችውን አታካምስ ሚሳኤል በመጠቀም ሩሲያን ላይ እየፈጸመችው ያለውን ተከታታተይ ጥቃት ተከትሎ ፑቲን የተቀናጀ ነው ያሉትን አጸፋዊ ምላሽ መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ በትናንትናው ሌሊት የዩክሬን የኃይል አቅርቦትን ከመታች በኋላ ነው ፕሬዚዳንት ፑቲን የአገራቸውን አቋም የተናገሩት።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለማንኛውም የሩሲያ ጥቃት ከባድ ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው ሳምንት ዩክሬን ከአሜሪካው አታካምስ በተጨማሪ ከዩናይትድ ኪንግደም የተለገሳትን ሻዶው ሚሳኤልን የሩሲያ ግዛትን ዘልቃ እያስወነጨፈች ትገኛለች።
ምዕራባውያን አጋሮች የሩሲያን ምድር በነዚህ ሚሳኤሎች እንድትመታ ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው ዩክሬን እነዚህን ጥቃቶች እየፈጸመች ያለችው።
ሩሲያ በትናንትናው ዕለት በርካታ ሰዓታትን የፈጀ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈጽማለች። በነዚህ ጥቃቶች ሞት ባይከሰትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዩክሬን ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውጪ ሆነዋል። ዘለንስኪ የሰላማዊ ሰዎች እና የሃይል መሰረተ ልማቱን ለመምታት የክላስተር አረሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።
“ክላስተር አረር ተሸካሚ መሳሪያዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈጸምባቸው በጣም አደገኛ የሩስያ የጦር መሳሪያ አይነት ነው” ብለዋል ዘለንስኪ።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋትከ 6 ሰአት በፊት
- የዚምባብዌ ፓርላማ ስለበጀት እየመከረ ሳለ መብራት ጠፋከ 5 ሰአት በፊት
- በአፍሪካ የሩሲያ ፕሮፖጋንዳ መሪ የሆነው ግለሰብ ለምን በቁጥጥር ሥር ዋለ?ከ 6 ሰአት በፊት
ሩሲያ በፈጸመችው በዚህ ጥቃት ኦሬሽኒክን ጨምሮ 90 ሚሳኤሎች እና 100 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መሳተፋቸውን ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናግረዋል።
እንደ ፑቲን ከሆነ ኦሬሽኒክ የተሰኘው የሩሲያ አዲሱ ባለስቲክ ሚሳኤልን ማክሸፍ አይቻልም።
የአሜሪካ ባለስልጣት ሩሲያ ጥቂት ቁጥር ያላቸው የሙከራ ኦሬሽኒክ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ሊኖራት እንደሚችል የሚያምኑ ሲሆን በበርካታ ቁጥር ለማምረት ጊዜ ያስፈልጋታል ይላሉ።
ዘለንስኪ ፕሬዚዳንት ፑቲን “ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት የለውም እንዲሁም ሌሎች ይህንን ጦርነት እንዳያቆሙ መከላከል ይፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “ጦርነቱን ማባባሱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሩሲያን አቋም እንድትቀበል ጫና ለማድረግ የታለመ ነው” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው ዩክሬን የኒውክሌር መሳሪያዎችን እንድታገኝ አገራቸው እንደማትፈቅድ ገልጸዋል። መሳሪያዎቹን ካገኘች ሩሲያ ማንኛውንም መሳሪያዎች ትጠቀማለች ማለታቸውን የሩሲያው መንግሥታዊ ሚዲያ አርአይኤ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ስማቸው ያልተጠቀሰ ምዕራባውያን ባለስልጣናት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከስልጣን ከመልቀቃቸው ከጥር ወር በፊት ለዩክሬን የኒውክሌር መሳሪያ እንዲሰጡ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል መባሉን የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።