ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የምክር ቤት ሕንጻ እና የፍትሕ አርማ

ከ 6 ሰአት በፊት

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት መሰብሰቢያዎች መካከል አንዱ የሆነው 52 ቁጥር አዳራሽ በሰዎች ተሞልቶ ነበር።

በስብሰባ አዳራሹ የሕግ እና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

እነዚህ ሰዎች በአዳራሹ የተገኙት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ ላይ ሕዝባዊ ውይይት ለማድርግ ነው።

ከአንድ ወር ገደማ በፊት ለምክር ቤቱ የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ “የአካሄድ እና የይዘት ግድፈቶች በስፋት የሚሰተዋሉበት” መሆኑን 14 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠቁመው ነበር።

መግለጫውን ካወጡት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) መግለጫው በወጣ ማግስት ኅዳር 3/ 2017 ዓ.ም. በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከሥራው ታግዷል።

ከካርድ መታገድ 10 ቀናት በኋላ ደግሞ ሌሎች ሁለት መግለጫው ላይ የተሳተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ኅዳር 12/2017 ዓ.ም. የታገዱት ድርጅቶች የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ናቸው።

ሁለቱ ድርጅቶች ከመታገዳቸው አንድ ቀን አስቀድሞ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ተወካይ፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ሕዝባዊ ውይይት ላይ ተሳትፈው ነበር።

“ማሻሻያ ሂደቱ ባለድርሻ አካላት ያልተሳተፉበት ነው። ስለዚህ ፍላጎቱ፣ ይዘቱ እና ሂደቱ ከመንግሥት በኩል የመጣ እንደሆነ ያሳውቃል። ይህም ከፖለቲካዊ ምክንያት የመነጨ እንደሆነ የሚያሳይ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ኅዳር መጀመሪያ ላይ ባወጡት መግለጫ “በሥራ ላይ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጥበቃ የሚሰጣቸውን ነጻነቶች የሚገድብ እና የሚዲያ ተቆጣጣሪውን አካል በአስፈጻሚው አካል ተጽዕኖ ውስጥ የሚጥል ነው የሚል ስጋት አለን” ብለው ነበር።

በረቂቅ ማሻሻያው ላይ ለውጥ የተደረገባቸው ጉዳዮች የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት የሚመለመሉበት እና የሚሾሙበት ሂደት አንዱ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩ ኃላፊነቶች ወደ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እንዲተላለፉ ተደርገዋል።

ይህ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ዕገዳ ወትሮም አስቸጋሪ በነበረው የዴሞክራሲ እና የሲቪል ምኅዳር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት በተደጋጋሚ በበጎ ከሚጠቀስባቸው ጉዳዮች መካከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ያደረጋቸውን የሕግ ማሻሻያዎች ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ሕጎች እና የተስተዋሉ ክስተቶች ግን በአንድ ወቅት መንግሥት “እንደ መልካም ስኬት” ሲገልጻቸው የነበሩ “ማሻሻያዎችን” ወደ ኋላ የሚቀለብስ ነው ይላሉ።

የሕግ ማሻሻያው እንዴት ተጀመረ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ‘ማሻሻያዎችን’ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበረ።ከእነዚህ መካከል አንደኛው የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ ነው።

መጋቢት 24/2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፤ “በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲያብብ ነጻነት እና ፍትህ እንዲሰፍን የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን” ማለታቸው ይታወሳል።

ከዚህ ንግግራቸው ሦስት ወራት በኋላ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር የሕግ እና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ ተቋቁሟል።

ጉባኤው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት እና ከሌሎች ቦታዎች የተውጣጡ 13 አባላት ነበሩት።

በወቅቱ የፌደራል ዋና ዐቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ጉባኤው፤ “በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ እንደ ችግር የሚነሱ ሕጎችን በመለየት እና ጥናት በማድረግ የለውጥ ሀሳቦችን በማቅረብ የማማከር ሥራ ይሠራል” ብለው ነበር።

አቶ ብርሃኑ አክለውም የሦስት ዓመታት የቆይታ ጊዜ እንዲኖረው ታስቦ ለተቋቋመው ጉባኤ መንግስት በጀት እንደሚመድብ መናገራቸው ይታወሳል።

በጉባዔው ስር ሕጎችን የማርቀቅ ኃላፊነት የተሰጣቸው የባለሙያዎች ቡድኖች (Working Groups) ተቋቁመው ነበር።

ቢቢሲ በእነዚህ የባለሙያዎች ቡድን ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አራት ግለሰቦችን አነጋግሯል።

ባለሙያዎቹ የሕግ ማሻሻያዎቹን ሂደት፣ ትኩረት እና በኋላ ላይም ያስከተሉትን ውጤት በተመለከተ በዝርዝር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ቶልቻ* የሕግ ማሻሻያዎቹ በዋናነት ያተኮሩት “ጨቋኝ ናቸው የሲቪክ ምኅዳሩን አጥብበውታል የተባሉ ሕጎች” ላይ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሌላኛው የባለሙያዎች ቡድን አባል አቶ ሚዛን፤ “ከዴሞክራሲ ሥርዓት እና ከሰብዓዊ መብት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሕጎች ችግር ነበረባቸው” ይላሉ።

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡት የሕግ ምሁራን እነዚህ ሕጎችን አጥንቶ እና ገምግሞ፤ “መለወጥ የሚገባቸው ከሆኑ እንዲለወጡ ሃሳብ ማቅረብ እና በዚያ አግባብ አዳዲስ ሕጎችን የማዘጋጀት” ኃላፊነት ነበረበት።

አቶ ሚዛን “አስቀድመው የዴሞክራሲ ሂደቱን በጣም ጎድተውታል” የተባሉት፤ የምርጫ፣ የፀረ ሽብር፣ የሚዲያ እና የሲቪል ማኅበራትን የሚመለከቱት ሕጎች በቅድሚያ እንደተሻሻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እውነተኛ ሽግግር ወይስ ቅቡልነት መሻት?

የሕግ ማሻሻያዎቹ በጥቅሉ ከሰባት ዓመታት በፊት በተፈጠረው የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥን ተከትለው የመጡ ነበሩ።

የባለሙያዎች ቡድን ውስጥ አባል የነበሩት አቶ ሰይፉ፤“ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ተካሂዷል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚተረጎመው አንድ አምባገነን መንግሥት ወደ ዴሞክራሲ ለውጥ አደርጋለሁ ብሎ ቃል ሲገባ [ነው]” ይላሉ።

“ዴሞክራሲን ቃል መግባት አዲስ ነገር አይደለም” የሚሉት አቶ ሰይፉ፤ “አዲስ የሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ተዓማኒ በሆነ መንገድ ነው ቃል የገባው። መንግሥት ቃል ሲገባ መታመኑ ሽግግር አለ የሚለውን ትርጉም እንዲያሟላ ያደርገዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።

መንግሥት ሽግግር እያደረገ መሆኑ መታመኑ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ቅቡልነት እና ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል።

“የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ድጋፍ ያገኙት ዴሞክራታይዝ እናደርጋለን ብለው ቃል በመግባታቸው ነው” ይላሉ አቶ ሰይፉ።

አቶ ሰይፉ አክለውም “የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ወደ ዴሞክራሲ ለውጥ እያደረጉ ነው ብሎ እንዲያምናቸው ምክንያት የሆነ ደግሞ የሕግ እና የፍትህ አማካሪ ጉባኤ መቋቋምን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልሂቅ እነሱን መደገፉ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

የሕግ እና ፍትህ አማካሪ ጉባኤው ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት በላይ በመንግሥት ዕይታ፤“ገዢው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እያካሄደ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ማስተጋባቱ ነበር” ይላሉ።

በጊዜው ለውጥ የሚለው ቃል የብዙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ንግግር ማሟሻ ነበር።

የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ እና በሌሎች መድረኮች በሚያደርጓቸው ንግግሮች ውስጥ ስለ ለውጥ በተለይ ደግሞ ስለ ሕግ ማሻሻያ በተደጋጋሚ ያነሱ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ባለሥስልጣኖቻቸው ‘ማሻሻያ’፣ ‘ለውጥ’ እና ‘ሽግግር’ የሚሉትን ቃላት ሲናገሩ ቢደመጡም፣ በሂደቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ግን “የሕግ ማሻሻያ የማድረግ ሃሳቡ ላይ እውነተኛ የሆነ ቁርጠኝነት አልነበረም” ይላሉ።

አቶ ቶልቻ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ፤ “መጀመሪያ ማሻሻያ ማድረግ የተፈለገው ቅቡልነት ለመገንባት ነበር። ያን ለማድረግ የተለያየ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ያስፈልግ ነበር። [መንግሥት] ተራማጅ መሆኑን ለማረጋገጥ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳየት ነበረበት” ሲሉ ይገልጹታል።

ሌላኛዋ በማሻሻያዎቹ ላይ የተሳተፉት የሕግ ባለሙያ ሐሊማ በበኩላቸው፤ “የመጀመሪያው ዓመት ላይ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ከአገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተዓማኒነትን ለመግዛት እና ቅቡልነትን ለማግኘት የተደረጉ ነበሩ” ይላሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ አራት ባለሙያዎች ለዚህ አስተያየት ማሳያ የሚሆኑ አስረጂዎችን ያቀርባሉ።

አቶ ሰይፉ “ከመጀመሪያዎቹ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች አንዱ መንግሥት የአብዛኞቹ ማሻሻያ ውጥኖች ይዘት፣ ስኬት ወይም ውድቀት ግድ የሚለው አልነበረም” ይላሉ።

“በቃላት ቁርጠኝነት ቢኖርም መንግሥት የመደበኛ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን በጀት መድቦ አያውቅም” ሲሉ ያክላሉ።

ሐሊማ፤ “በአጠቃላይ ሃሳቡ ከመንግሥት እንደ መጣ ከዚያ ደግሞ በእያንዳንዱ ዋና ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ይሰጣሉ” ይላሉ።

ሐሊማ አክለውም እነዚህ ውሳኔዎች በጊዜው ምክትል ዐቃቤ ሕግ በነበሩት ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞትዮስ በኩል ወደ ባለሙያዎቹ ቡድን ይተላለፉ እንደነበር ይገልጻሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ከመንግሥት አካላት ተቃውሞዎች ይመጡ እንደነበር ባለሙያዎቹ ያስታውሳሉ።

አቶ ቶልቻ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ ላይ ያጋጠመውን ተቃውሞ በማስረጃነት ያነሳሉ።

ረቂቅ ሕጉ ከተዘጋጀ በኋላ፤ በአዋጁ “ሥልጣናችን ተገደበ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቦርድ ውስጥ እንዲካተቱ ተደረገ፤ ለምን ድርጅት ለመሰረዝ ፈቃድ ተከለከልን?” በሚል ተቃውሞ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መቅረቡን ያስታውሳሉ።

ውጥኑ ከመንግሥት መምጣቱን የሚያስታውሱት አቶ ሚዛን፤ “የመንግሥት የወቅቱ አቋም ቢቀየር ይሄ ተቋም ሥራውን በዚያው በጀመረበት ግለት እና ትኩረት ሊቀጥል ይችላል ወይ የሚል ጥርጣሬ አስቀድሞ ነበር” ይላሉ።

አቶ ሚዛን “ሥራው ተጀመሮ አንድ ዓመት ተኩል እንዳለፈ የተጀመሩት ሥራዎችን እንኳን መግፋት አልተቻለም” ሲሉ ያክላሉ።

“መንግሥት አሁን የህልውና ጥያቄ መጥቶብኛል ብሎ ትኩረቱን ሲቀይር፣ ስብሰባዎችን ሌሎች የሚያደርጋቸውን ድጋፎች ሙሉ በሙሉ ሲያቆም፣ እንደ በፊቱ አብሮ መሥራት ሳይቻል ቀረ” ይላሉ አቶ ሚዛን።

ኢትዮጵያ ወደ ኋላ እየተመለሰች ይሆን?

ባለሙያዎች እንደሚሉት መንግሥት ወትሮም በልበ ሙሉነት ያልገባበት የሕግ ማሻሻያ ሂደት አሁን እየተቀለበሰ ይመስላል።

በአንድ ወቅት በመንግሥት ኃላፊዎች እንደ ትልቅ ስኬት ይታይ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ለዚህ ማሳያ ነው።

በማሻሻያው መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ወይም ተቀጣሪዎች የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባል እንዳይሆኑ የሚከለክለው የአዋጁ ድንጋጌ ተሰርዟል።

አቶ ሚዛን አዋጁን በማርቀቅ ሂደት ውስጥ ይህ የአዋጅ ድንጋጌ ጥያቄ ማስነሳቱን ያስታውሳሉ።

“የገዢው ፓርቲ ትልልቅ ባለሥልጣናት፣የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ቦርድ ውስጥ እንዳይካተቱ የሚል መስፈርት መቀመጡ ምቾት የነሳቸው ሰዎች ሃሳባቸውን ገልጸው ነበር” ይላሉ።

“ጥርጣሬው ነበር መጨረሻ ላይም ይጸድቃል የሚል እምነት አልነበረንም” የሚሉት አቶ ሚዛን፤ “ሲጸድቅ ግን ተማምነዋል ማለት ነው አልን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዋጁ ከጸደቀ አንድ ዓመት በኋላ ግን ፓርላማው ያጸደቀውን አዋጅ በሚቃረን መልኩ የገዢው ፓርቲ አባል እና አመራር የሆኑ ሰዎችን በቦርድ አባልነት ሹሟል።

አቶ ሚዛን በጊዜው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ፤ “መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት እና ሚዲያው በሙሉ መንግሥትን ተጠያቂ እያደረገ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ መንግሥት የማይቆጣጠራቸውን አካላት የቦርድ አባላት አድርጎ እንዴት ይሾማል ብላችሁ ታምናላችሁ?” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአማካሪ ጉባኤው በኩል የወጡ ሕጎችን ከመጣስ እና ከማሻሻል በተጨማሪ ጉባኤው ያረቀቃቸው አንዳንድ ሕጎች የደረሱበት ሳይታወቅ የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል።

አቶ ሚዛን “ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወቅቱ በርካታ የሕግ ረቂቆች እጄ ላይ አሉ፤ አሁን እነሱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አይደሉም ማለት ጀመረ” ሲሉ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተጨማሪ፤ “ረቂቆች ሲቀርቡለት ወዲያው ይወስን የነበረው ፓርላማ፣ አሁን የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠረ ለወራት ጉዳዮችን ማዘግየት ውሳኔ አለመወሰን” ይስተዋል እንደነበር ያክላሉ።

“ለውሳኔ የመረጃ ነጻነት እና የኮምፒውተር አዋጆችን አቅርበን ነበር” ይላሉ።

የሕግ ባለሙያዋ ሐሊማ የመረጃ ነጻነት አዋጅ አለመጽደቅ “ለዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ትልቅ ኪሳራ ነበር” ሲሉ በቁጭት ይገልጻሉ።

“የመረጃ ነጻነት አዋጁ በስህተት አይደለም እንዲቀር የተደረገው፤ መንግሥት ስላልፈለገው ነው። ሕዝባዊ ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ በሌላ ሕግ ይወጣል ተብሎ ቀረ” ሲሉ ያክላሉ።

ይህን ተከትሎ “ለእኔ ግልጽ የሆነልኝ [በመንግሥት በኩል] ቁርጠኝነት እንደሌለ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሐሊማ ይህን ቢሉም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፓርቲያቸውን አምስተኛ ዓመት ምሥረታ አስመለክተው ባወጡት መግለጫ፣ የዴሞክራሲ እና የሲቪክ ተቋማት እንዲሁም በሚዲያ ነጻነት እና ዕድገት ረገድ የተሰሩ “የለውጡ ውጤቶች”ን ዘርዝረዋል።

ዐቢይ በዚህ መግለጫቸው “ለውጡ ሲቪክ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለተቋማትም ሆነ ለአገር በሚበጅ መልኩ በአዲስ ሕግ እና በአደረጃጀት እንዲዋቀሩ አድርጓል” ብለዋል።

ዐቢይ በመግለጫው ያነሱት እና የመንግሥታቸው ግብር ግን ለየቅል ናቸው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።

ፓርቲያቸው አምስተኛ ዓመቱን እያከበረ ባለበት ሳምንት ብቻ ሦስት የሲቪል ማኅበራት ድርጀቶች ታግደዋል። የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የአስፈጻሚውን አካል ጡንቻ የሚያፈረጥም ሆኖ ተሻሽሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት መጨረሻ የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን የሚሻሙ እና የዜጎችን መብቶች የሚገድቡ ረቂቅ አዋጆች ለፓርላማ ቀርበው ነበር።

እነዚህ ክስተቶች ለዴሞክራሲ እና ለሲቪክ ምኅዳሩን ያጠቡታል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

አቶ ሰይፉ “በኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራታይዜሽን የሚደረገው ሽግግር ያበቃለት [እ.አ.አ] 2020 አጋማሽ ላይ ነው” ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው አክለውም፤ “የትግራይ ጦርነት በጀመረበት ሰዓት ስለ ዴሞክራታይዜሽን ማውራት ቀልድ ነው፤ ዴሞክራታይዜሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር ይችላል የሚያስብል አንድም አመክንዮአዊ፣ ንድፈ ሃሳባዊ እና ተግባራዊ መሠረት አልነበረም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በፌደራል ደረጃ የሚታየው የግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት (authoritarianism) በደንብ እየተገለጠ ነው” የሚሉት አቶ ቶልቻ “ከዚህም የባሱ እርምጃዎች ወደፊት እንደሚመጡ እጠብቃለሁ” ይላሉ።

አቶ ሰይፉ እና ሐሊማም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተስተዋሉት ክስተቶች እና “የፈላጭ ቆራጭነት (authoritarianism) መገለጫዎች እንሆኑ” ይስማማሉ።

*በዚህ ዘገባ የተጠቀሱ የሕግ ባለሙያዎች እና አስተያየት ሰጪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ ስለጠየቁ ለአንባቢ እንዲያመች በሚል ስማቸው ተቀይሯል።