
29 ህዳር 2024, 16:26 EAT
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ሐሙስ ዕለት ታጣቂዎች ዘጠኝ ሰዎችን ከቤታቸው በመውሰድ መግደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ግድያው የተፈጸመው ሐሙስ ኅዳር 19/ 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6፡00 አካባቢ መሆኑን ቤተሰቦች ገልጸው፤ ታጣቂዎቹ ዘጠኝ ወንዶችን ከቤታቸው ከወሰዱ በኋላ ወንዝ አካባቢ እንደገደሏቸው ገልጸዋል።
ቤተሰቦች እንሚሉት ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ይፈጽማል ባሉት “በሸኔ ታጣቂዎች” መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳው ሶሌ ፈረንቀሳ በተባለ ቀበሌ ተፈጽሟል የተባለው ግድያ “ሃይማኖት ተኮር” እንደሆነ ነዋሪዎች እና ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“በየቤቱ ይዘው በማገት ወደ ወንዝ አካባቢ ወስደዋቸው፤ ዘጠኙን አንድ ላይ አሰልፈው ነው የገደሏቸው” ያሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከከሟቹች ውስጥ አንዱ የ42 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አጎታቸው መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሟቾቹ “አንድ ሰፈር” የሚኖሩ ጎረቤቶች እና ዘመዳሞች እንደሆኑ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪ ሰለባዎቹ “በሙሉ የእኛ ቤተሰቦች ናቸው” ብለዋል።
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ አካባቢው ላይ እንደደረሱ የተናገሩ አንድ የተጎጂ ቤተሰብ ከሟቾቹ ውስጥ ወንድማቸው እንደሚገኝበት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እኩለ ሌሊት ላይ ወደ መኖሪያ መንደሩ የመጡት ታጣቂዎች “እያንዳንዱን ሟች ከየቤቱ ለቀሙት” ያሉት ወንድም፤ ወደ ወንዝ ተወስደው እንደተገደሉም ተናግረዋል።
ስጋት ውስጥ የነበረው የአካባቢው ማኅበረሰብ በማግስቱ [ዛሬ አርብ ኅዳር 20] ተኩስ ወደተሰማበት አካባቢ ፍለጋ መውጣቱን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ አስከሬን ወንዝ ዳር “እንዳለ ተረፍርፎ ተገኘ” ብለዋል።
በእርሻ እና እንጨት ሥራ የተሰማሩ ነበር የተባሉት የአራት ልጆች አባት ሟች ከሌሎች ሰለባዎች ጋር ፈረንቃሳ በተባለ ወንዝ አቅራቢያ ተገድለው ተገኝተዋል።
ከሟቾቹ መካከል ሁለት የ70 ዓመት አዛውንቶች እንደሚገኙ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከ45 ዓመት በታች የሆኑ እና በግብርና ሥራ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው ብለዋል።
ስለ ጥቃቱ መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን እና አራት ሰዎች መታገታቸውን ያሳወቀ ሲሆን፤ “የጫካው ሸኔ” የተባለ ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን እንደፈጸመ ከአካባቢው ነዋሪዎች መስማቱን ገልጿል።
አካባቢው ላይ ለገንዘብ የሚፈጸም እገታ እንዳለ የተናገሩት አንድ የሟች ቤተሰብ፤ ታጣቂዎቹ ቤተሰቦቻቸውን በደረቅ ሌሊት ሲወስዱ ሟቾች ብር ከፍለው የሚለቀቁ መስሏቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የተገደሉት ሰዎች የቀብር ሥርዓት ዛሬ አርብ ኅዳር 20/2017 ዓ.ም. ሶሌ ቅዱስ ሚካኤል በተባለ ቤተክርስቲያን እንደተፈጸመ ቢቢሲ ከቤተሰቦች እና ከነዋሪዎች ሰምቷል።
የተፈጸመው ግድያ “የመረረ ሐዘን” በነዋሪው ዘንድ መፍጠሩን የተናገሩት አንድ የሟች ወንድም ጥቃቱን “የጅምላ ጭፍጨፋ” ሲሉ ገልጸውታል።
“በተናጠል ጉድጓድ እንኳ [አልተቆፈረም]፤ መደዳውን ተሰልፈው ነው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የተፈጸመው። . . . ሁሉም ሐዘንተኛ ነው… ቆፋሪ ጠፋ” ሲሉ ሟቾቹ በጅምላ መቀበራቸውን ተናግረዋል።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋት29 ህዳር 2024
- ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ፡ የሳምንቱ ጨዋታዎች ግምት29 ህዳር 2024
- የሶማሊያዋ ጁባላንድ ክልል ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ አለች29 ህዳር 2024
ነዋሪዎች በጥቃቱ ቀን ከአካባቢው ሌሎች አምስት ሰዎችም ታግተው እንደተወሰዱ ገልጸው እስካሁን ታጋቾቹ እንዳልተገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቀብር ላይ የነበሩ አንድ ቤተሰብ የታገቱት ሰዎችን አስከሬን እየጠበቀ እንደነበር ጠቁመው ተወሰዱበት በተባለው ቦታ ቢፈለጉም አስከሬናቸው አልተገኘም ብለዋል።
ሌላ ነዋሪ ግን ከወንዙ ተሻግሮ ቡርቃ በተባለ አካባቢ አራቱ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ጠቁመዋል።
የግድያው ምክንያት እንደማይታወቅ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ሁሉም ሟቾቹ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ጠቅሰው “እምነት ተኮር” ግድያ ነው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ከዘጠኝ ዓመት በፊት በአካባቢው የሃይማኖት ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፤ በአካባቢው ሌላ እምነት ተከታዮች ቢኖሩም ክርስቲያኖች “ተመርጠው” ጥቃት ፈጽሞባቸዋል ብለዋል።
ባለፉት ቀናት በአካባቢው ተመሳሳይ ግድያዎች እና እገታዎች እንደነበሩ የተናገሩ አንድ ነዋሪ የኅዳር 19ኙ ጥቃት “ሌላ ዙር [ጥቃት] ነው” ብለዋል።
“በግራ በቀኝ ግድያ አለ። ከሦስት ቀን በፊት ሦስት ወይም አራት ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉ ስጋት እንዳለ የተናገሩት ነዋሪ፤ ወረዳቸው ግድያ እና እገታ በተደጋጋሚ የሚፈጸምበት መሆኑን አመልክተዋል።
የአካባቢው ነዋሪ በተደጋጋሚ ጥቃቶች “የተፈናቀለ ነው” ያሉ ሌላ ነዋሪው፤ አካባቢው ተረጋግቷል በሚል ሰብል ለመሰብሰብ ወደ ቀበሌው ያመሩ ሰዎችም የግድያው ሰለባ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በአካባቢው የሸኔ ታጣቂዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የፀጥታ ኃይሎች [መከላከያ ሠራዊት] ጥቃት በደረሰበት ሶሌ ፈረንቀሳ ቀበሌ “የጥይት ተኩስ” በሚሰማበት ርቀት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
“ያን ያህል ርቀት በሌለበት ቦታ ላይ ነው [ሰው] እየተገደለ፤ ሰው ሞተ የሚለውን የሚሰሙት። ሁለት ኪሎ ሜትር ቢሆን ነው። ቢያንስ ተኩስ ይሰማል። የደረሰልን ግን የለም” ብለዋል።
ዛሬ [አርብ] ረፋድ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥበቃ እንሚያደርጉላቸው ቃል መግባታቸውን የተናገሩ የሟች ቤተሰብ፤ “እንቆጣጠራለን፤ ሕዝቡ ከእኛ ጋር ይሁን” ማለታቸውን ተናግረዋል።
በአርሲ ዞን ተደጋጋሚ የንጹሃን ግድያ የሚፈጸም ሲሆን፤ በሽርካ ወረዳ ባለፈው ዓመት ኅዳር 14/2016 ዓ.ም. “የተደራጁ” በተባሉ ታታቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአርሲ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት ምዕመኖቿ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚደርስም ገልጻ ነበር።
ባለፈው ዓመት በሽርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም እና በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት 36 የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን እንደተገደሉ አስታውቃለች።