
ከ 6 ሰአት በፊት
በምስራቅ ቦራና በዋጪሌ ወረዳ የሦስት ልጆች እናት የሆነችውን ገበያ መሀል አስረው ግርፋት የፈጸሙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ።
ወ/ሮ ኩሹ ቦናያ በገበያ ቦታ ላይ ከዛፍ ጋር ታስራ በባለቤቷ በአሰቃቂ ሁኔታ ስትደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ከታየ በኋላ በርካቶችን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ይህ ግርፋት የተፈጸመው ደግሞ በአካባቢ ሽማግሌዎች ትዕዛዝ ሲሆን፣ የታሰረችውም በርካታ ሰዎች ቆመው በሚያዩበት የገበያ ስፍራ ነበር።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የዋጪሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ድርጊቱን በመፈፀም እና በመተባበር የተከሰሱ አራት ግለሰቦች ላይ ሕዳር 19 /2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ከሰባት እስከ አራት ዓመት የሚደርስ እስራት ወስኗል።
የወረዳው አቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ጉያ አሬሮ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ጥቃቱን በመፈጸም የመጀመሪያ ተከሳሽ ሆኖ የቀረበው ድብደባውን የፈጸመው ባለቤቷ ጋልጋሎ ዋሪዮ ነው።
ሁለተኛ እና ሦስተኛ ተከሳሾች ደግሞ ታስራ እንድትደበደብ ውሳኔ ያሳለፉ ሽማግሌዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሽ በስድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።
ሦስተኛው ተከሳሽ የሆኑት የአካባቢ ሽማግሌ ከዛፍ ጋር ታስራ እንድትገረፍ ብቻ ሳይሆን፣ ከግርፋቱ በኋላም ታስራ እንድትቆይ በመወሰናቸው ሰባት ዓመት ከሁለት ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።
አራተኛው ተከሳሽ የቃቃሎ መንደር የሰላም እና ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሆናቸው አቃቤ ሕግ ጨምረው ገልጸዋል።
እንደ አቃቤ ሕጉ ገለጻ ሽማግሌዎቹ በግርፋት እንድትቀጣ ሲወስኑ ሚስትየው ወደዚህ ግለሰብ ሄዳ ጣልቃ እንዲገባ እና እንዲያስቆም ብትጠይቅም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋት29 ህዳር 2024
- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዘጠኝ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ተናገሩ29 ህዳር 2024
- በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን እስር እና እንግልት በረታብን አሉከ 8 ሰአት በፊት
ተበዳይ በወቅቱ የቃቃሎ መንደር የሰላም እና ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊን “አንተ የሕግ ሰው ነህና አስቁምልኝ” ስትል ብትጠይቃቸውም “በፍርዳቸው ጣልቃ መግባት አልችልም” በማለት የመለሰ ሲሆን፣ ድብደባ ከተፈጸመባት በኋለ “ሚሊሻዎቹ ሴትዮዋን ይዘው ወደ ማቆያ ጣቢያ እንዲወስዷት አዟል… በሚል በሁለት ወንጀል ተከሷል” ብለዋል።
በግለሰቡ ላይ ፍርድ ቤት የአራት አመት እስራት እና 5ሺህ 500 ብር እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል።
ስለ ሴትዮዋ ወቅታዊ ሁኔታ የተጠየቀው የወረዳው አቃቤ ሕግ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላት መሆኑን ተናግረዋል።
“አሁን በሕክምና ሕይወቷን ማትረፍ ተችሏል” ያሉት አቃቤ ሕግ፣ በጥሩ ጤንነት ላይ መሆኗን እና ብይኑ ሲሰጥም በችሎቱ ላይ መገኘቷን ተናግረዋል።
የወረዳው አቃቤ ሕግ ጉያ አሬሮ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት በአካባቢው በገበያ ላይ ድብደባ ሲፈጸም አይተውም ሰምተውም እንደማያውቅ ተናግረዋል።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችውን ሴት የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ አላከበረችም በሚል ዋጪሌ ገበያ ላይ አስሮ የመግረፉ ድርጊት የተፈጸመው መስከረም 9/ 2017 ዓ.ም. ነበር።
ጥቃቱ የደረሰባት ሴት ዘመድ የሆኑት ጃርሶ ቡሌ ለቢቢሲ በወቅቱ ንደተናገሩት ግርፋቱ የተፈጸመባት ግለሰብ ኩሹ ቦናያ የምትባል ስትሆን፣ ገራፊው ደግሞ ባለቤቷ ገልገሎ ዋሪዮ መሆኑን ተናግረዋል።
ኩሹ እና ባለቤቷ ገልገሎ በትዳር 12 ዓመት መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ጃርሶ፣ በኑሯቸው ችግር ውስጥ ሲወድቁ ባለቤቷ ወደ ውትድርና መግባቱን ይናገራሉ።
“በውትድርና አራት ዓመት ያህል ቆይቷል” የሚሉት አቶ ጃርሶ ባለቤቱ ልጆቿን ለማሳደግ ብቻዋን ስትጥር መቆየቷን ይመሰክራሉ።
ገልገሎ ከውትድርና ከተመለሰ በኋላ ግን ባለቤቱን መደብደብ መጀመሩን የሚናገሩት የሚስት ዘመድ፣ “በተደጋጋሚ ወደ ቤተሰቦቿ እየሸሸች ሁኔታዎች ሲረጋጉ ወደ ቤቷ ትመለስ ነበር” ይላሉ።
ገልገሎ ከውትድርና ከተመለሰ በኋላ ከባለቤቱ ጋር መስማማት አለመቻሉን፣ ዘወትር ባለቤቱን እና ልጆቹን የሚደበድብ እንደነበርም ጨምረው ተናግረዋል።
በአገር ባህል መሰረት ሽማግሌዎች በባለትዳሮቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተደጋጋሚ ለሽምግልና መቀመጣቸውን የሚጠቅሱት ግለሰቡ “ችግሮች ሳይፈቱ ሲቀሩ ወደ አባቷ ቤተሰብ ሸሸች። ሽማግሌዎች ተነጋግረው ባለቤቷ ጠባዩን እንዲያሻሽል እርሷም ወደ ቤቷ እንድትመለስ መከሯት። እርሷ ግን ነገሩን በደንብ እንዲያጤኑት ወደ ቤቷ ብትመለስ አንደሚገላት’ ተናገረች” ይላሉ።
የሽማግሌዎቹን ቃል እንዳላከበረች የተቆጠረችው ኩሽ ግን ሽማግሌዎቹ የወሰኑባት ታስራ እንድትገረፍ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዘመዷ ይገልጻሉ።
“በሚኖሩበት አካባቢ ባለ ዛፍ ላይ አሰሯት። ይህንን ያደረጉት ልጇ እያለቀሰ፣ ሌሎች ቆመው እያዩ ነው” ሲሉ ያክላሉ።
በስፍራው ተገኝተው የነበሩ በሙሉ ፎቶ እንዳያነሱ፣ ቪድዮ እንዳይቀርጹ ተከልክለው እንደነበር የሚናገሩት ግለሰቡ “ስትገረፍ ከዋጪሌ ዱብሉቅ አንድ መኪና በድንገት መጣ። አንድ ልጅ ከመኪናው ወርዶ ቪድዮ መቅረጽ ጀመረ” ያሉት ጃርሶ በዚህም የተፈጸመውን ወንጀል ሌሎች ሊያዩት እንደቻሉ ያብራራሉ።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ኩሹ በዛፍ ላይ ታስራ በባለቤቷ ግርፋት ከደረሰባት በኋላ ክፉኛ መጎዳቷን ተከትሎ መጀመርያ በአሬሮ ሆስፒታል በኋላም ወደ ያቤሎ ሆስፒታል ሄዳ ሕክምና የተከታተለች ቢሆንም የተሻለ ሕክምና በማስፈለጉ ወደ ሐዋሳ ሆስፒታል ተልካ ታክማለች።