
ከ 8 ሰአት በፊት
ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ ወሲብ ነክ ይዘት ያላቸው ታሪኮችን አካቷል።
ሶፊ ቤልጂየም ውስጥ በወሲብ ንግድ ትተዳደራለች።
“የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር ሆኜ እየሠራሁ ነበር። ልጅ ልወልድ ሳምንት ቀርቶኝ ከደንበኞቼ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እፈጽም ነበር” ትላለች።
የአምስት ልጆች እናት ሆኖ መሥራት “በጣም ከባድ ነው” ስትል ሶፊ ትገልጻለች።
አምስተኛ ልጇን በቀዶ ሕክምና ነው የወለደችው። ለስድስት ሳምንታት እረፍት እንድታደርግ በሐኪም ተነገራት።
እረፍት መውሰድ ስላልቻለች ግን ወደ ሥራ ተመለሰች።
“ገንዘብ ስለሚያስፈልገኝ ሥራ ማቋረጥ አልቻልኩም” ትላለች።
የወሊድ ፈቃድ ተሰጥቷት ከአሠሪዋ ክፍያ ብታገኝ ሕይወቷ ቀላል ይሆን ነበር።
ቤልጂየም በቅርቡ ያወጣችው ሕግ በዓለም የመጀመሪያው ነው።

ሕጉ፣ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ይፋዊ የሥራ ውል እንዲፈርሙ፣ የጤና መድኅን እንዲኖራቸው፣ ጡረታ እንዲያገኙ፣ የወሊድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው እና ሲታመሙ እረፍት እንዲወጡም ይፈቅዳል።
በዚህ ሕግ መሠረት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ሌላ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ።
“እንደ ሰው እንድንኖር ዕድል የሚከፍት ነው” ስትል ሶፊ ሕጉን ታወድሳለች።
በዓለም ላይ 52 ሚሊዮን የሚጠጉ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች እንደሚገኙ ዓለም አቀፉ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ማኅበር ይገልጻል።
ቤልጂየም በአውሮፓውያኑ 2022 ሥራው ላይ የተጣለውን የሕገ ወጥነት ክልከላ አንስታለች።
ቱርክ እና ፔሩን ጨምሮ በሌሎችም አገራት የወሲብ ንግድ ሕጋዊ ነው።
በወሲብ ንግድ ለተሰማሩ ሰዎች በቤልጂየም የተሰጠው የሠራተኞች መብት በዓለም ቀዳሚው ነው።
በሂውማን ራይትስ ዋች አጥኚ የሆነችው ኤሪን ኪልብሬድ “እስካሁን በየትኛውም የዓለም ክፍል ካየነው አካሄድ የተሻለው ነው” ትላለች።
ሁሉም አገራት ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉም ትመክራለች።
ለወሲብ ንግድ ሰዎችን ማዘዋወር እና ብዝበዛን የሚያስከትል ሥራ ነው ብለው የሚተቹ አሉ።
ኢስላ የተባለው በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎችን የሚደግፈው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ውስጥ በጎ ፈቃደኛ የሆነችው ጁሊያ ክሩሚሬ “ሕጉ ከመጀመሪያውም ብዝበዛ የሚበዛበትን ሥራ ሕጋዊ መልክ የሚያላብስ ነው” ትላለች።
- ድብቁ የወሲብ ንግድ በሶማሊያ25 መጋቢት 2023
- ችላ ተብለው በአሳሳቢ ደረጃ በመላው ዓለም እየተስፋፉ የመጡት የአባላዘር በሽታዎች23 መጋቢት 2024
- ግድያና ጠለፋ መገለጫው የሆኑት የሴራሊዮን የወሲብ ንግድ!12 የካቲት 2021
አብዛኞቹ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ሕጉ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ።
በወሲብ ንግድ የምትተዳደረው ሜል ለአባላዘር በሽታ በሚያጋልጣት መንገድ ከአንድ ደንበኛዋ ጋር ያለ ኮንዶም አፋዊ የወሲብ ግንኙነት እንድታደርግ መገደዷ እንዳስደነገጣት ትገልጻለች።
አማራጭ ስላልነበራት የታዘዘችውን ፈጽማለች።
“አማራጬ ገንዘብ አለማግኘት ወይም በሽታውን ማስተላለፍ ነበር” ትላለች።
ገንዘብ ያስፈልጋት ስለነበር በ23 ዓመቷ ነው ወደ ሥራው የገባችው። ጥሩ ገቢ ማግኘቷ ተስፋ ቢሰጣትም ለአባላዘር በሽታ መጋለጧ አሰጋት።
አሁን ላይ ምቾት የሚነሳት ነገር እንድታደርግ ደንበኞቿ ከጠየቋት አትቀበልም።
“ያኔም ቢሆን አሠሪዬ ሕግ እየጣሰች መሆኑን መንገር ነበረብኝ። በምን መንገድ መሥራት እንዳለብኝ ስገልጽ ሕግ አጣቅሼ እናገር ነበር” ትላለች።
ቤልጂየም ሕጉን ያጸደቀችው እአአ በ2022 ለወራት ያህል የተቃውሞ ሰልፎች ከተካሄዱ በኋላ ነው።
ተቃውሞው የተነሳው በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ጥበቃ ስላልተደረገላቸወ ነበር።
በቤልጂየም በወሲብ ንግድ ለተሰማሩ ሰዎችን መብት የሚሟገተው ማኅበር መሪ ቪክቶሪያ በሙያው ለ12 ዓመት ቆይታለች።
ሥራው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከመፈጸም በላይ እንደሆነ ትናገራለች።
“ለሰዎች ትኩረት የመስጠት፣ ታሪካቸውን ሲናገሩ የማዳመጥ እና አብሯቸው ጊዜ የማሳለፍ ሥራ ነው። ምክንያቱም ወደኛ የሚመጡት ብቸኝነት ስለሚሰማቸው ነው” ትላለች።

እስከ 2022 ድረስ ሙያዋ ሕገ ወጥ መሆኑ ይፈትናት ነበር። ደኅንነቷ ሳይጠበቅ ለመሥራት ተገዳለች። ቀጣሪዎቿ ከፍተኛ ገንዘብ ይወስዱባትም ነበር።
ከደንበኞቿ አንዱ እንደደፈራት ቪክቶሪያ ትናገራለች። ፖሊስ ጣቢያ ስትሄድ ያነጋገረቻት ሴት ፖሊስ “በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች አይደፈሩም” እንዳለቻት ታስታውሳለች።
“ሥራውን በመሥራቴ ልታሸማቅቀኝ ሞከረች” ትላለች።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች እንደሚሉት የማይፈልጉትን ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚገደዱበት ጊዜ አለ።
ስለዚህም አዲሱ ሕግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ቪክቶሪያ ታምናለች።
“ሕግ ከሌለ እና ሥራው ሕገ ወጥ ከሆነ እኛን የሚጠብቅ መርህ የለም ማለት ነው። ይሄ ሕግ ሥራችንን ደኅንነታችን ተጠብቆ እንድንሠራ ያደርጋል” ትላለች።
አዲሱ ሕግ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎችን ለሚያስተዳድሩ ሰዎችም ዕውቅና ይሰጣል። የሚከተሉት ደንብም በሕጉ ተካቷል።
በወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎችን መቅጠር አይችልም።
ኪርስ ሬክማስ እና ባለቤቱ አሌክሳንድራ በቤኮቮርት ከተማ ማሳጅ ቤት አላቸው።
“ብዙ ቀጣሪዎች በወንጀል የተከሰሱ ስለሆኑ፣ ቢዝነሴ መዘጋቱ አይቀርም” ይላል ኪርስ።
ማሳጅ ቤቱ መዋኛ ገንዳን ጨምሮ ሌሎችም አገልግሎቶች የሚሰጡ ክፍሎች አሉት።
ጥንዶቹ 15 በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ተቀጣሪዎች አሏቸው።
ሠራተኞቻቸውን እንደሚንከባከቡ እና ጥሩ ክፍያ እንደሚሰጡም ይናገራሉ።
“ክፉ አሠሪዎች ተወግደው ሥራውን በታማኝነት የሚያከናውኑ ሰዎች የተሻለ ይሠራሉ ብዬ አምናለሁ” ይላል ኪርስ ስለ አዲሱ ሕግ ሲገልጽ።
በሂውማን ራይትስ ዋች አጥኚ የሆነችው ኤሪን ኪልብሬድም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች።
አዲሱ ሕግ ቀጣሪዎች ያላቸውን ያልተመጣጠነ ኃይል እንደሚቀንስ ትናገራለች።

ኢስላ የተባለው በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎችን የሚደግፈው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ውስጥ በጎ ፈቃደኛ የሆነችው ጁሊያ ክሩሚሬ ግን የተለየ አስተያየት አላት።
“እኛ ከምናግዛቸው ሴቶች አብዛኞቹ ከዚህ ሥራ ወጥተው መደበኛ ሥራ መያዝ ነው የሚፈልጉት። በብርድ ቆሞ ከማያውቁት ሰው ጋር በክፍያ ወሲብ ለመፈጸም መጠበቅ አይደለም ሕልማቸው” ስትል ትገልጻለች።
በቤልጂየም አዲስ ሕግ መሠረት የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጸምባቸው ክፍሎች የአደጋ ጊዜ ደውልን ጨምሮ ሌሎችም የጥንቃቄ መሣሪያዎች ይኖሯቸዋል።
የአደጋ ጊዜ ደውሎቹ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች አደጋ ሲገጥማቸው እንዲደርሱላቸው ከሚፈልጓቸው ሰዎች ጋር ያገናኛሉ።

ጁሊያ ግን የወሲብ ንግድን ደኅንነቱ የተጠበቀ ሙያ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ ታምናለች።
“የአደጋ ጊዜ ደውል የሚያስፈልገው ሌላ ሥራ አለ? የወሲብ ንግድ በዓለም ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው ሥራ ሳይሆን በዓለም ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው ብዝበዛ ነው” ትላለች።
የወሲብ ንግድን እንዴት ማስተካል ይቻላል? የሚለው ጉዳይ የተለያየ አስተያየት የሚሰጥበት ነው።
በወሲብ ንግድ ለተሰማራችው ሜል ግን ሙያተኞችን ከተደበቁበት እንዲወጡ መንገድ መክፈት ጥሩ ጅማሮ ነው።
“ቤልጂየም ከሁሉም ቀድማ ይህንን ሕግ በማውጣቷ ኩራት ተሰምቶኛል። የተሻለ የወደፊት ሕይወት ይኖረኛል ማለት ነው” ትላለች።