
ከ 8 ሰአት በፊት
በሶሪያ ውስጥ ያሉ አማፂ ቡድኖች በአገሪቱ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ አሌፖ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ቃኚ ቡድን (SOHR) ገለፀ።
ቡድኑ አንዳለው እስከ አርብ አመሻሽ ድረስ አማፂዎቹ ከተማዋን ከግማሽ በላይ ተቆጣጥረዋል።
ይህ እርምጃው በሶሪያ መንግሥት ላይ ከዓመታት በኋላ የተደረገ ትልቁ ጥቃት የተባለ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንት በሽር አላሳድን ጦር የሚዋጉ አማፂያን በ2016 በአገሪቱ ጦር ኃይል ተገድደው ከአካባቢው ከወጡ በኋላ አሌፖ ሲደርሱ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ከእስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሀያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) ጋር ግንኙነት ባለው ቻናል ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ የአማፂ ተዋጊዎችን በከተማዋ ውስጥ በተሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱ ያሳያል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ቪድዮው በምዕራብ የአሌፖ ዳርቻ አካባቢ የተቀረጸ መሆኑን አረጋግጧል።
የመንግሥት ኃይሎች በበኩላቸው በአሌፖ እና ኢድሊብ በሚገኙ በርካታ ከተሞች በኤችቲኤስ እና አጋሮቹ ረቡዕ ዕለት የከፈቱትን ጥቃት በመመከት ዳግም መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ. በ 2011 መንግሥት የዴሞክራሲ ደጋፊ በሆኑ ተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ በወሰደው እርምጃ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተገድለዋል ።
የአሳድ መንግሥትን የሚቃወሙ የታጠቁ ቡድኖች፣ ጂሃዲስቶችን ጨምሮ፣ ግርግሩን በመጠቀም የተለያዩ የአገሪቱን ክፍሎች ተቆጣጥረዋል።
የሶሪያ መንግሥት፣ በሩሲያ እና ሌሎች አጋሮቹ፣ በመደገፍ አብዛኛውን ያጣቸውን ቦታዎች መልሶ መቆጣጠር ችሏል።
የመጨረሻው የተቃዋሚዎች ጠንካራ ይዞታ የሆነችው ኢድሊብ በአብዛኛው በኤችቲኤስ ቁጥጥር ስር ያለች ሲሆን፣ በቱርክ የሚደገፉ አማፂ ቡድኖች እና የቱርክ ኃይሎች በአካባቢው ሰፍረው ይገኛሉ።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋት29 ህዳር 2024
- ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ፡ የሳምንቱ ጨዋታዎች ግምት29 ህዳር 2024
- ከ60 በላይ ሴት ልጆችን የደፈረው የሕጻናት እንክብካቤ ሠራተኛ እድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት29 ህዳር 2024
አርብ እለት ከአማፂያኑ ጋር ግንኙነት ባለው ቻናል ላይ የተለጠፈ መግለጫ “ጦራችን ወደ አሌፖ ከተማ መግባት ጀምሯል” ይላል።
በቢቢሲ የተረጋገጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት በከተማይቱ መሃል ከሚገኘው እና ‘የአሌፖ የመካከለኛው ዘመን ምሽግ’ በመባል ከሚታወቀው ስፍራ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የታጠቁ ሰዎች ሲሮጡ ይታያሉ ።
ሌላው በቢቢሲ የተረጋገጠ ቪድዮ ሻንጣ የያዙ ብዙ ሰዎች አሌፖ ዩንቨርስቲ አቅራቢያ ካለ አካባቢ ርቀው ሲሄዱ ያሳያል።
ይህ ቪዲዮ የተቀረፀው ከኤችቲኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች አማፂ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል ከሚሉበት ቦታ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።
መንግሥት አሁን በአሌፖ ድጋፍ ሰጪ ወታደሮች መድረሳቸውን እና አማፂያኑን እያባረሩ መሆኑን ተናግሯል።
የወታደራዊ ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ከአሌፖ የሚደረጉ በረራዎች በሙሉ መሰረዛቸውን እና የአውሮፕላን ማረፊያው መዘጋቱን ተናግረዋል።
በሶሪያ ያለውን ሁኔታ የተለያዩ ምንጮችን በመጠቀም ክትትል የሚያደርገው ድርጅት (SOHR ) እንደዘገበው የሶሪያ እና የሩስያ አውሮፕላኖች አርብ እለት በአሌፖ ግዛት ላይ 23 የአየር ድብደባዎችን ፈጽመዋል።
ድርጅቱ እንዳለው ከሆነ በጦርነቱ 255 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በሶሪያ ውስጥ በአማፂያን እና በመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች መካከል ከተደረጉ ውግያዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞት የተመዘገበበት ነው።
በኢድሊብ የሚደረግ ጦርነት እ.ኤ.አ. ከ 2020 ጀምሮ ፣ ቱርክ እና የሶሪያ ቁልፍ አጋር ሩሲያ ፣ መንግሥት ግዛቱን መልሶ ለመያዝ የሚያደርገውን ግፊት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ እየቀነሰ መጥቶ ነበር።
ነገር ግን ረቡዕ ዕለት ኤች ቲ ኤስ እና አጋሮቹ በአካባቢው እየተባባሰ የመጣውን የመንግሥት እና የአጋር ሚሊሻዎችን “ጥቃትን ለመከላከል” በሚል ተኩስ መጀመራቸውን ተናግረዋል ።
የሶሪያ መንግሥት እና አጋሮቹ በሌሎች ግጭቶች ውስጥ እያሉ የተከፈተ ጦርነት ነው።
በጎረቤት ሊባኖስ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በኢራን የሚደገፈውን የሔዝቦላህ ንቅናቄ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱ ይታወቃል።
የሔዝቦላህ ተዋጊዎች የሶሪያን የእርስ በርስ ጦርነት አቅጣጫ በመቀየር ረገድ ቁልፍ ሚና ነበራቸው።
እስራኤል በሶሪያ ውስጥ በኢራን እና በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ጋር የተገናኙ ዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባዋን አጠናክራለች።