
ከ 8 ሰአት በፊት
ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመገናኘት ፍሎሪዳ ገብተዋል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በካናዳ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸውን ተከትሎ ነው የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሎሪዳ በሚገኘው የትራምፕ መኖርያ የተገኙት።
የካናዳ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ትሩዶ አርብ አመሻሽ ላይ ትራምፕን በመኖርያ ቤታቸው ማር-አ-ላጎ ለማግኘት በፓልም ቢች ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል።
ትራምፕ በጥር ወር ስራ ሲጀምሩ ከሜክሲኮ እና ካናዳ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጣል በተናገሩበት ሳምንት ሁለቱ በስልክ ተነጋግረው ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትም ሆነ የትራምፕ ቡድን በጉብኝቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
የትሩዶ ጉዞም ቢሆን በዕለታዊ ሥራ ዝርዝራቸው ውስጥ ያልተካተተ ሲሆን፣ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር እራት እንደሚበሉ ግን ምንጮች ገልጸዋል።
ምንም እንኳን የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት አልፎ አልፎ መንገራገጭ ቢኖርበትም፣ ትሩዶ በትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን አገራቱ ትልልቅ የንግድ ስምምነትን በተሳካ ሁኔታ መደራደር መቻላቸውን አጽንኦት ይሰጡታል።
ትሩዶ በፕሪንስ ኤድዋርድ ደሴት ላይ በተካሄደ ዝግጅት ሲናገሩ ሁለቱ አገራት “በድንበሮቻቸው በኩል ስራዎችን ለመፍጠር ጠንክረው ሰርተዋል” ብለዋል ።
አክለውም ከትራምፕ ጋር ብዙ “ትልልቅ” ውይይቶችን ለማድረግ በጉጉት እንደሚጠባበቁ ገልጸዋል።
ይህ የፍሎሪዳ ጉብኝት ካናዳ ታሪፎችን ለማስቀረት የወሰደችው የቅርብ ጊዜ እርምጃ ነው።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋት29 ህዳር 2024
- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዘጠኝ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ተናገሩ29 ህዳር 2024
- ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ፡ የሳምንቱ ጨዋታዎች ግምት29 ህዳር 2024
ተመራጩ ፕሬዝደንት ግባቸውን ለማሳካት ከዚህ ቀደም ዛቻዎችን እንደ መደራደርያ ዘዴ እንደሚጠቀሙ የሚገልጹት ተንታኞች፣ መጪው የትራምፕ አስተዳደር እጥለዋለሁ ባለው ታሪፍ አቋሙ ይፀና እንደሆን ግልፅ አይደለም ይላሉ።
ትራምፕ በሜክሲኮ ላይ ተመሳሳይ ቀረጥ ለመጣል ያስፈራሩ ሲሆን፣ ሜክሲኮ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የጋራ ድንበር ለመጠበቅ እስከሚሰራ ድረስ ባለበት እንደሚቆይ አመልክተዋል።
ትሩዶ አርብ ዕለት “ትራምፕ እንደዚህ አይነት መግለጫዎችን ሲሰጡ ለማስፈጸም አቅደዋል ማለት ነው” ብለዋል ።
አላማው ታሪፉ ካናዳውያንን ከመጉዳት ባለፈ በአሜሪካውያን ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፍ ነው ሲሉም አክለዋል።
ከትራምፕ ጋር ካደረጉት የስልክ ምልልስ በኋላ ትሩዶ ረቡዕ እለት ከካናዳ አውራጃዎች እና ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋር የአሜሪካ እና የካናዳ ግንኙነትን እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደዋል።
ካናዳ ከአሜሪካ ትላልቅ የንግድ አጋሮች መካከል አንዷ ስትሆን ከጠቅላላ የወጪ ንግዷ 75 በመቶውን ወደ አሜሪካ ትልካለች።
ትሩዶ ከግብር ጋር በተያያዘ የአገራቸውን ጥቅም የሚያስከብር አቋም እንደሚከተሉ ቃል ገብተዋል።
በርካታ የካናዳ አውራጃዎች አስተዳዳሪዎች የትራምፕን እቅድ በመተቸት የነዳጅ፣ የጋዝ እና የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት በእጅጉ ይጎዳል ብለዋል።
በዚህ ሳምንት የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት የሆኑት ክላውዲያ ሺንባም ከትራምፕ ጋር በስልክ አውርተዋል።
እንደ አሜሪካ ድንበር ተቆጣጣሪ መሥርያ ቤት መረጃ ከሆነ፣ የአሜሪካ ካናዳ ድንበር ማቋረጫዎች ቁጥር ከሜክሲኮ አሜሪካ ድንበር በጣም ያነሰ ነው።
እ.ኤ.አ. በ 2024 የበጀት ዓመት በሰሜናዊ የአገሪቱ ድንበር ላይ ወደ 23,700 የሚጠጉ ስጋቶች የነበሩ ሲሆን፣ በሜክሲኮ በኩል ባለው የአገሪቱ ደቡባዊ ድንበር ደግሞ ከ 1.53 ሚሊዮን በላይ ስጋቶች ተፈጥረዋል።
ነገር ግን የካናዳ ባለስልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድንበር ደህንነትን ለማሻሻል በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።