
ከ 7 ሰአት በፊት
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በመንግሥታቸው ቁጥጥር ስር ያሉና በሩሲያ ያልተያዙ የዩክሬን ግዛቶች በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስር ቢገባ ጦርነቱ ሊቋጭ እንደሚችል ጠቆሙ።
የግዛቶቹ የኔቶ አባልነት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት በአሁኑ ወቅት የተፋፋመውን ጦርነት ይገታዋል ሲሉም ነው ከስካይ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ አቋማቸውን የገለጹት።
በዚህ ረዘም ያለና ሰፊ ቃለ ምልልስ አገራቸው የኔቶ አባልነት ጥያቄን ትቀበል ይሆን የሚል ጥያቄ በቀረበላቸው ወቅት አሁን የተቆጣጠሯቸው ግዛቶች አባል መሆን ከቻሉ ብለዋል።
ነገር ግን የኔቶ አባልነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና በተሰጣት መላው ዩክሬን ግዛቶችን ባካተተ መልኩ መጀመሪያ ሊቀርብ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚያም ዩክሬን በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ተቆጣጥራቸው የምትገኘውን ግዛቶቿን “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ” ለማስመለስ በድርድር ትሞክራለች ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን ጽንሰ ሃሳብ እስካሁን ያቀረበ አካል እንደሌለ ተናግረዋል።
ኔቶ እንደዚህ አይነት እርምጃ ይወስድ ይሆን የሚለው በከፍተኛ ሁኔታ አጠራጣሪ ነው።
“ዩክሬን እንዲህ አይነቱን ምክረ ሃሳብ አጢናው አታውቅም። ምክንያቱም ያቀረበልን አካል ስለሌለ” ሲሉ ገልጸዋል።
ኔቶ ሩሲያ ተቆጣጥራቸው የሚገኙ ግዛቶችን ጨምሮ መላውን ዩክሬን ባጠቃለለ መልኩ አባልነት ሊያቀርብ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋት29 ህዳር 2024
- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዘጠኝ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ተናገሩ29 ህዳር 2024
- በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን እስር እና እንግልት በረታብን አሉከ 8 ሰአት በፊት
“አንደኛውን የአገሪቱን ክፍል የአባልነት ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም” ሲሉ በአስተርጓሚ ለስካይ ኒውስ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ አክለውም “ለምን ካላችሁ፤ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በኛ ቁጥጥር ስር ያለው የዩክሬን ግዛት ብቻ ዪክሬን እንደሆነች ዕውቅና እየሰጣችሁ ነው፤ ሌላኛው የተያዙ ግዛቶች ደግሞ በሩሲያ ግዛትነት ዕውቅና መስጠት ነው” ብለዋል።
በርካቶች የተኩስ አቁም ሃሳብ እያቀረቡ እንደሆነ የገለጹት ዘለንስኪ ነገር ግን ሩሲያ ዳግም እንዳታጠቃ ለመከላከል የሚያስችል ዘዴ ከሌለ የተኩስ አቁም አደገኛ ነው ብለዋል።
አገራቸው የኔቶ አባል መሆኗ ብቻ ዳግም እንዳትጠቃ ዋስትና ሊሰጥ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ምዕራባውያን አጋሮች ጠንከር ያለ ውሳኔ ላይ ቢደርሱ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ሊቋጭ እንደሚችል ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከዚህ ቀደም ለሁለት ተከፍላ በነበረችው ጀርመን፣ ምዕራብ ጀርመንን ብቻ የኔቶ አባል ማድረግ ልምድ በዩክሬን እንዲተገበር ምዕራባውያንን መወያየታቸው ተገልጿል።
ግን እስካሁን ድረስ በመደበኛነት የቀረበ ሃሳብ የለም።
እስካሁን ድረስ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መላውን ዩክሬን የመቆጣጠር ሃሳባቸውን ትተውት ይሆን የሚል ፍንጭ አልተገኘም።
የትኛውም የዩክሬን ግዛት ኔቶን እንዲቀላቀል ፕሬዚዳንት ፑቲን ይፈቅዳሉ የሚለው ለአሁኑ የማይታሰብ ነው።