በኢትዮጵያ የሚገኙ ሴት ዲፕሎማቶች ልምዳቸውን አካፍለዋል

ማኅበራዊ ሴቶች በዲፕሎማሲው

ምሕረት ሞገስ

ቀን: December 1, 2024

ሴቶች በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከምዕት በላይ ቢያገለግሉም፣ ያደረጉት አስተዋጽኦ በአብዛኛው ተሸፍኖ ቀርቷል፡፡ ሆኖም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቀ አበርክቶ አድርገዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እንደሚለውም፣ የሴቶች የመምራት አቅም፣ ብልሃት፣ ቅድሚያ የሚሰጧቸው አጀንዳዎች ጉዳዮችን በስፋት የሚያይና ውጤቱም ጥራት ያለው ነው፡፡

ሴቶች በየአገራቸው ካቢኔም ሆነ ፓርላማ ወይም በዓለም አቀፍ ተቋማት ሲያገለግሉ የሚያሳልፏቸው ሕጎችና ፖሊሲዎች ብዙኃኑን ያማከሉ፣ አካባቢንና ማኅበረሰብን የሚያስተሳስሩ ናቸው፡፡

ሆኖም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ሴቶች ሊያበረክቱ ከሚችሉት አስተዋጽኦ እንዲደናቀፉ እያደረገ ነው፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ከመጣስ ባለፈም ከፖለቲካ ተሳትፎ የሚያግድ ሆኗል፡፡

ይህ ደግሞ ሴቶች በፖለቲካ እንዳይሳተፉ፣ ድምፃቸውን እንዳያሰሙ፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ለማኅበረሰቡ ሊያበረክቱ ከሚችሉት አስተዋጽኦ እንዲገደቡ የሚያደርግ ነው፡፡ ሆኖም እንደ አገሮቹ ነባራዊ ሁኔታ ቢለያይም፣ ችግሮችን ተቋቁመው፣ ለከፍተኛ የመምራት ደረጃ የበቁ፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍም የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ፣ እያሳረፉ ያሉና ለማሳረፍ የሚንደረደሩ አሉ፡፡

የእነዚህን ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ለማስቀጠል ደግሞ ልምድ መለዋወጥ፣ መተጋገዝ፣ መረዳዳት፣ መመካከርና አብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህንኑ ሴቶች በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያላችውን አበርክቶ ለማፅናት፣ ለማስቀጠልና የቀደሙት ለቀጣዩ ትውልድ እንደ ድልድይ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ የልምድ መለዋወጫ መድረክ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. አዘጋጅቶ ነበር፡፡

መድረኩ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን፣ የፖርቹጋል፣ የሞሮኮ፣ የአውስትራሊያ፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጉልህ አበርክቶ እያደረጉ የሚገኙት፣ በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ ልምዳቸውን ያካፈሉበት ነው፡፡ ለወጣት ሴት ዲፕሎማቶች የሚመጡ መልካም አጋጣሚዎችን እንዲጠቀሙ ችግሮችን አልፈው የሴቶችን የኃላፊነት ሚና እንዲያስቀጥሉ የመከሩበት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደሯ ናታሊን ኤድዋርድ፣ በታሪክ ሲታይ የዲፕሎማሲ ሥራ ወንድ የበዛበት ነው ሲሉ የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ይገልጹታል፡፡ ሆኖም በጊዜ ሒደት የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሴቶች አምባሳደር ሆነዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በመሪነት ደረጃ እየመጡ ነው፡፡ ይህንን ታዲያ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖርቱጋል አምባሳደሯ ሊዊሳ ፍራጎሶ በበኩላቸው፣ ሰሞኑን እየተከናወነ ያለውን የ16 ቀናት የሴቶች ውትወታ ጊዜን አስታውሰው፣ የሴት አምባሳደርነት ሚና የሴቶችን ሁለንተናዊ ዕድገት ማፋጠን ነው ብለዋል፡፡

ሴቶች ማኅበረሰብን ለመምራት ወሳኝ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የሴቶች አቅም እንዲገነባ እንደሚሠሩና በዓለም ደረጃ ሴቶችን መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ወደ መምራት ሚና እንዲመጡ የቤተሰብ ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑም ሴቶችን በቤተሰብ ደረጃ መደገፍ እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡

በሞሮኮ የሴቶች ሚና ይበልጥ እየጎላ የመጣውና የሴቶች ተሳትፎ የተጠናከረው በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1999 ወዲህ እንደሆነ በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደሯ ነዚሃ ዓሎዩ ይናገራሉ፡፡ በአገራቸው የሴቶች ተሳትፎ አቅም እንዲጎለብት ያደረገው ደግሞ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ሥፍራ መገኘታቸው ነው፡፡ ይህም ዛሬ ላይ በሞሮኮ ሥራ ላይ ካለው የሰው ኃይል 43 በመቶ፣ አገሪቱን በመምራት ደረጃ ካሉት ደግሞ 25 ከመቶ ያህሉ ሴት ተሿሚዎች እንዲሆኑ አስችሏል፡፡

የሴቶች የመምራት ሚና አጠቃላይ ለውጥና ዕድገት ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑም፣ ለአገሪቱ ለውጥ የሚያመጡ ፖሊሲዎች እንዲኖሩ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፣ እየተጫወቱ ነው ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1945 የመጀመሪያዋን ሴት ዲፕሎማት ለሾመችው አውስትራሊያ፣ ሴቶች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ የረዳው በአገሪቱ ያለው መዋቅር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደሯ ጁሊያ ኒብሌት እንዳሉትም፣ በአገሪቱ የተዘረጋው መዋቅር ሴቶች በሁሉም ቦታ እንዲታዩ አድርጓል፡፡

‹‹በአገሪቱ ያሉ ፖሊሲዎች የመጣንበት ማኅበረሰብ ነፀብራቅ ናቸው፤›› ያሉት አምባሳደር ጁሊያ፣ የሴቶች በየመዋቅሩ መምጣት በአገሪቱ በተለይ ሴቶችን ከትምህርት፣ ከሥራ፣ ከሥልጣን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ልማዶች እንዲቀለበሱ፣ ፖሊሲዎች እንዲሻሻሉና ሴቶች በኃላፊነት ደረጃ እንዲመጡ አድርጓል ብለዋል፡፡

በአውስትራሊያ ሴቶችን ወደ ሥልጣን ለማምጣት እንደሚሠራ፣ አሁን ላይ አገሪቱ ካሏት ዲፕሎማቶች 55 በመቶ ያህሉ ሴቶች እንደሆኑም አስታውሰዋል፡፡

‹‹ይህ በአንዴ አልመጣም፤›› ያሉት አምባሳደሯ፣ የሴቶች ተሳትፎና የፖለቲካ ውክልና በሒደት እየሰፋና እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ዲፕሎማትነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች በኃላፊነት ደረጃ መሥራት ብቻ እንዳልሆነ ያሰመሩበት ደግሞ አምባሳደር ሒሩት ዘመነ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የሴቶች የመምራት ውክልና ከምዕት ዓመት በፊት መጀመሩን ንግሥት ሳባን በመጥቀስ የተናገሩት አምባሳደር ሒሩት፣ በሰብዓዊ አገልግሎት ዙሪያ እንደ አበበች ጎበና ያሉ ከውጭ ግንኙነት በመፍጠር ሲሠሩ የነበሩና እየሠሩ ያሉም ለአገራቸው ዲፕሎማት ናቸው ብለዋል፡፡

ሴቶች የያዙትን የዲፕሎማሲ ሥራ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን የሚያሰምሩበት አምባሳደሯ፣ በዚህ በሥራ ላይ ያሉ ሆነ ኃላፊነታቸውን የጨረሱ አምባሳደሮች ለተተኪ ወጣቶች ልምድ ማካፈል፣ ማሠልጠን፣ መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ሴቶች በኃላፊነት ቦታ ሲሆኑ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋምና ማለፍ፣ በሥራ ሒደት ሁሉ መማር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡  

ለወጣቱ ትውልድ ልምድ ማካፈል፣ መደገፍና መምከር እንደሚገባ ይህ ከአካባቢ፣ ከቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤትና ከሥራ አለቆች ሊመነጭ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

‹‹ራስን ነፃ ለማውጣትና ከሚፈለገው ቦታ ለመድረስ እርስ በርስ መደጋገፍ አለብን፣ ይህ ግዴታ ሴት ለሴት ብቻ መሆን የለበትም፣ ወንዶችም ሊደግፉ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ሴት ዲፕሎማት ስትሆን እንደ ወንድ ዲፕሎማት መሆን እንዳልሆነ፣ ሴት የተለየ ስጦታ ስላላት ይህንን ተጠቅማ አበርክቶዋን ማጉላት እንዳለባትም መክረዋል፡፡

ሴቶች ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ፣ ሦስት ልጆች እያላቸው ማስተርሳቸውን ይዘው የሚመሩ እንዳሉ፣ የአሁን ወጣት ሴቶች እንደ እነሱ ጊዜ እንዳልሆኑ፣ ለቤተሰብም ለራስም እንደሚሆኑና እነዚህን ማበረታታት እንደሚገባ በመግለጽም፣ ቤተሰብ የመመሥረት አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የፖርቱጋሏ አምባሳደርም፣ ‹‹ቤተሰቦቻችሁን አትጡ፤›› ሲሉ ሴቶች መምራት እንደሚችሉ፣ ቤተሰብ መንከባከብ፣ ሥራ መሥራትም ሆነ ሁሉንም ማድረግ እንደሚችሉ ችግሮችን መቋቋምና በሥነ ልቦና መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ሴቶች በራሳችሁ ተመማኑ፣ ተማሩ፣ ግንኙነታችሁን አጠናክሩ፣ ወጣቶች ሴቶች ወደ መምራት እንዲመጡ እንዲደገፉ ያሉት ደግሞ የሞሮኮዋ አምባሳደር ነዚሃ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር በበኩላቸው፣ ሴቶች ‹አንችልም› የሚለውን አመለካከት መቀየር አለባቸው ብለዋል፡፡   

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ብርቱካን አያኖ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ፍትሐዊነትንና አሳታፊነትን ለማስቀጠል፣ በከፍተኛና በወጣት ሴት ዲፕሎማቶች መካከል መተባበር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።