

ማኅበራዊ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ 53ኛው የምሥረታ ቀኗን በኢትዮጵያ አከበረች
ቀን: December 1, 2024
በአብርሃም ተክሌ
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ 53ኛውን የውህደት (የምሥረታ) ቀኗን ኅዳር 29 ቀን 2024 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አከበረች።
በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ቡድን አባላት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የንግድ መሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአዲስ አበባ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አምባሳደር መሐመድ ሳሌም አል ራሼዲ በበዓሉ አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከተመሠረተችበት እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 2 ቀን 1971 ጀምሮ ስላደረገችው ጉዞ ያብራሩ ሲሆን፣ በተለይም ‹‹የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በሟቹ ሼክ ዛይድ ቢን ሡልጣን አል ናህያን እና ሼክ ራሺድ ቢን ሰኢድ አል ማክቱም የመሪት ዘመን በአገር ውስጥ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉልህ ክንዋኔዎችና ስኬቶች ያስመዘገበችበት ነው፤›› ብለዋል።
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጉላት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የትብብር መስኮችን ጠቅሰዋል። አምባሳደር መሐመድ ሳሌም አል ራሼዲ አክለውም ‹‹እንደ አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮዴርስ ፕሮግራም ያሉ ከፍተኛ የልምድ ልውውጦችና የአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መካከል እያደገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ገላጮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስጋኑ አርጋ የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መካከል ያለውን ጠንካራ ወንድማዊ ግንኙነት በማድነቅ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እያስመዘገበችው ያለው ስኬትና ብልፅግና እንዲቀጥል ተመኝተዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር ያላትን ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት ከፍ አድርጋ ትመለከታለች፡፡ አመራሯና ሕዝቦቿ ቀጣይ ዕድገትና ብልፅግና እንዲኖር ትመኛለች፤›› ብለዋል። በሁለቱ አገሮች መሪዎች እየተመራ ያለው የኢኮኖሚ ትብብር መስፋፋትና በቅርቡ የተደረሰው የሁለትዮሽ ስምምነት ማዕቀፍ ለቀጣይ ግንኙነታቸው ወሳኝ ዕርምጃ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አቶ መስጋኑ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር መሆኗን ገልጸው በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲጂታል ልማት ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ጠቁመዋል። የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ለኢትዮጵያ የሦስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰው፣ ይህም የሁለቱን አገሮች ጠንካራ ወዳጅነት የበለጠ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መንግሥት በአስቸጋሪ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ስላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ ትብብር ለሁለቱም ሕዝቦች የተረጋጋ ዕድገትና ብልፅግና መንገድ ከፋች መሆኑን አመልክተዋል።