

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)
ማኅበራዊ በትምህርት ረቂቅ አዋጅ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ሚና በግልጽ ባለመደንገጉ በአፈጻጸም ላይ ችግር…
ቀን: December 1, 2024
በአብዛኛው ትምህርትን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቢሆኑም፣ በአጠቃላይ የትምህርት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሁለቱ ሚና በግልጽ ባለመደንገጉ በአፈጻጸም ላይ ችግር እንዳይፈጥር እንደገና መታየት እንዳለበት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማትና ሥራ ሥምሪት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ከአስረጂዎች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ እንደገለጹት፣ አጠቃላይ ትምህርትን በባለቤትነት የሚያስተዳደሩትና መምህራንን የሚያሰማሩት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሁለቱ ሚና ምን እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ስለሌለ፣ ጉዳዩ በትክክኛው መንገድ መታየት አለበት ብለዋል፡፡
በተለይ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ በርካታ መመርያዎች በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ይወጣሉ የሚል እንጂ፣ የከተማ አስተዳደሮችና ክልሎችን አሳታፊ ስለማድረግ አለመገለጹን አስረድተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የአጠቃላይ የትምህርትን አፈጻጸም ግምገማን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር ሲጠየቅ ሪፖርቱ የመጣው ከከተማ አስተዳደሮችና ከክልሎች ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጥበት እየታወቀ፣ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የሁለቱ ሚና በግልጽ አለመቀመጡ በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ለረቂቅ አዋጁ አፈጻጸም ያመች ዘንድ ምን ያህል ደንቦች ያስፈልጋሉ የሚለውን ከእነ ይዞታቸው በመለየት፣ አስፈላጊ ደንቦችን ከወዲሁ ዝግጁ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአጠቃላይ የትምህርት ምዘና ጋር ተያይዞ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ በአርሶና በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚከፈቱ ትምህርት ቤቶች፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አስፈላጊነትን ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
‹‹በተለይ የመምህራንና የትምህርት ጉዳይ በልዩ ሁኔታ መታየት አለበት፤›› ያሉት ሰብሳቢው፣ የትምህርት ዘርፍን በጥሩ ሁኔታ ለማሳለጥ ረቂቅ አዋጁን በደንብ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ከአስረጂ መድረክ ለቀረቡ ከ130 በላይ ጥያቀዎች ምላሸ የሰጡት የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ፣ የፌዴራል መንግሥት ፖሊሲ ከማውጣትና መመርያ ከማዘጋጀት በዘለለ የወጡ ሕጎችን ተፈጻሚነታቸውን የመከታተል ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣል ብለዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ የከተማ አስተዳደሮችና የክልሎች ሚና ምንድነው የሚለው በግልጽ ለምን አልተቀመጠም ለተባለው፣ ጉዳዩ በተለየ ሁኔታ መታየት ካለበት የትምህርት ሚኒስቴር ውይይት አድርጎ እንደሚፈታው አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ዘርፉን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ትልቁን ኃላፊነት መወጣት ቢኖርበትም፣ ክልሎች ደግሞ የተለያዩ ሥራዎችን የማስፈጸም ተግባር እንዳለባቸው የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የትምህርት ጥራትን፣ ፍትሐዊ ተደራሽነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ‹‹ደረጃውን የጠበቀ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ከክልሎች ጋር የተጣጣመ አሠራር እንዲኖር የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት ያስችለናል፤›› ብለዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 23 ንዑስ 6 ቁጥር የውጭ አገሮች ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶችና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶችን የማረጋገጥ ሥራ በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ለምን ሆነ? ትምህርት ቤቶቹ የሚገኙባቸው የከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ኃላፊነት ለምን አልተካተተም? የሚሉ ጥያቄዎች ከአስረጂዎች ቀርበዋል፡፡ ለቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ፣ ጉዳዩ የውጭ ግንኙነት ስላለው በሚኒስቴሩ በኩል ተግባራዊ እንዲደረግ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
የመምህራንን መብት ለማስከበር የሚያስችሉ መመርያዎችን በረቂቅ አዋጅ ለማካተት መሞከሩን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ረቂቅ አዋጁ መካተት ያለባቸው ጉዳዮችና ግልጽ ሊሆኑ የሚገባቸውን ቃላት ተለይተው እንደሚሻሻል አክለዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ የጋራ መግባባት ቢኖር ወጥና ተቀባይነት የሚያረጋግጥ አሠራር እንደሚዘረጋ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ቤተልሔም ላቀው (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በረቂቅ አዋጁ መስተካከል ያለበትን ጉዳዮች በድጋሚ በማየትና ወጥ አስተሳሰብ በማንፀባረቅ፣ አገራዊ የሆነ የትምህርት ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡