ነፍስ ኄር ካፒቴን መሐመድ አህመድ

ማኅበራዊ ካፒቴን መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ እመርታ የመሩ (1924-2017)

ሔኖክ ያሬድ

ቀን: December 1, 2024

ኢትዮጵያ ወደ ምዕት ዓመት የሚጠጋ የካበተ የንግድ አቪዬሽን ታሪክ አላት። በተለይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዓመት በኋላ ሰማንያ ዓመት ይሞላዋል፡፡ በነዚህ ዓረፍተ ዘመን የተለያዩ ደረጃዎችን አሳልፏል፡፡

ካፒቴን መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ እመርታ የመሩ (1924-2017) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላን ሲቀበሉ

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የ1930ዎቹ መጨረሻና ተከታታይ ዓመታቱ የጅማሬ፣ 1940ዎቹ የረጅም ርቀት መንገዶች የተጀመረበት፣ 1950ዎቹና 1960ዎቹ የጄት ዘመን፣ 1970ዎቹና 1980ዎቹ የቦይንግ 767 እና 767 200ER መምጣት፣ የዘመናዊ ኤርፖርት ግንባታ፣ ከ1992 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር፣ ኤርባስ ኤ350-900፣ ቦይንግ 777-200LRs ወዘተ ገብተዋል፡፡ ስታር አልያንስንም የተቀላቀለበት ነው፡፡

በነዚህ የስምንት አሠርታት ያህል ጉዞው የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለመምራት ኢትዮጵያውያን የተሰየሙት ከሩብ ክፍለ ዘመን ቆይታ በኋላ ነው፡፡ በኮሎኔል ስምረት መድኃኔ የተጀመረው አመራርነት እስካሁኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዘንድ ደርሷል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በዘለቀው የኢትዮጵያውያን በብቃት አየር መንገዱን የመምራት ጉዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዕልናን ከግንባር ቀደምነት ጋር ተያይዞ ስሙ እንዲነሳ አድርጎታል፡፡

ይሁን እንጂ መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ በ1967 ዓ.ም. ያስወገደው አብዮትን ተከትሎ ሥልጣኑን የጨበጠው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት የተከተለው ሶሻሊስታዊ ርዕዮት ለአየር መንገዱ ፈተና መሆኑ አልቀረም፡፡

ካፒቴን መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ እመርታ የመሩ (1924-2017) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ካፒቴን መሐመድ አህመድና አቶ ግርማ ዋቄ እ.ኤ.አ. በ2009 አፍሪካዊ ሽልማትን
በተቀበሉበት አጋጣሚ

በአብዮቱ የመጀመርያ አምስት ዓመታት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት መባባሱ በአየር መንገዱ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መንገዳገድ ኪሳራም አስከትሎ ነበር፡፡

ይህን አሳሳቢ ሁኔታ የተገነዘበው መንግሥትም በውጭ አገር የሚገኙ የቀድሞ አመራሮች ፍጡነ ረድኤት ሆነው አየር መንገዱን እንዲታደጉ መንቀሳቀሱ አማራጭ ሆኖ ያገኘው፡፡ በዚህ አጋጣሚም 1972/73 ዓ.ም. (1980) ላይ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ካፒቴን መሐመድ አህመድ ብቅ ያሉት፡፡

የቀድሞው ደርግ የወለደው የኢሕዲሪ መንግሥት (1980-83) ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ትውስታቸውን አጋርተዋል፡፡

ካፒቴን መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ እመርታ የመሩ (1924-2017) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ካፒቴን መሐመድ አህመድ የአፍሪካ ትራቭል ሌጀንድ ሽልማትን ሲቀበሉ
ፎቶ አፍሪካን ትራቭል ኤንድ ቱሪዝም

 ‹‹የ1966ቱ ሕዝባዊ አመፅ ሲፈነዳ የፖለቲካው ወላፈን አየር መንገዱ ውስጥም ገብቶ ያምሰውና ያተራምሰው ገባ፡፡ ተራማጅ ነን የሚሉ የደርግ አባላት፣ ሚኒስትሮችና ካድሬዎች አየር መንገዱ ከቦይንግ [አሜሪካ] ወደ ኤሮፍሎት [ሶቪየት ኅብረት] እንዲሰጥ›› ያደርጉት የነበረው ጥረት የከሸፈው ‹‹ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አየር መንገዱ ወደ ውድቀት ማምራቱን ሲገነዘቡ ሥር ነቀል ዕርምጃ በመውሰድ መፍትሔ እንዲያስገኙ ለፍሥሐ ደስታ፣ ለአማኑኤል ዐምደሚካኤልና የሱፍ አህመድ ጥብቅ መመርያ በመስጠታቸው እንደሆነ በታሪካቸው ላይ ሰፍሯል፡፡

ከአገር ወጥተው በተለያዩ አገሮች በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩት የአየር መንገዱ የቀድሞ ኃላፊዎች ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ፣ ካፒቴን መሐመድ አህመድ፣ አሰፋ አምባዬና ወልደ ገብርኤል ፀሐይ በሦስቱ ከፍተኛ ሹማምንት አማካይነት እንዲመጡ በማድረግ አየር መንገዱ ከውድቀት መታደጋቸው ተጽፏል፡፡

የካፒቴን መሐመድ መንበር

ካፒቴን መሐመድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሥራ የጀመሩት በ1950ዎቹ የአውሮፕላን ዋና መሐንዲስነት (chief aeronautical engineer) ሲሆን፣ ከቴክኒካዊ ዕውቀታቸውና ከእይታቸው በመነሳት ለአየር መንገዱ ዕድገት መሠረታዊ ሚና መጫወታቸው በገጸ ታሪካቸው ተመዝግቧል።

ካፒቴን መሐመድ እ.ኤ.አ. በ1980 የዋና ሥራ አስፈፃሚነት መንበሩን ከተረከቡ በኋላ በአሠርት ውስጥ የፈጸሟቸው ተግባራት አየር መንገዱን ወደ አዲስ ከፍታ እንዳደረሰ ይወሳል፡፡  

ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ አፍሪካን ትራቭል ኳርተርሊ ላይ የተጻፈ ማስታወሻ ይህንኑ ያመለክታል፡፡ ‹‹በእሳቸው መሪነት አየር መንገዱ በወታደራዊ አገዛዝ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆንም እያደገ ሄደ። የካፒቴን አህመድ ቅልጥፍናና የማይናወጥ ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከአላስፈላጊ ጣልቃገብነት ከለለው፡፡ ይህም በአፍሪካ በጣም ስኬታማ ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል።››

ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘላቂ ስኬት መሠረት የጣሉትን ካፒቴን መሐመድን በይበልታ ያወደሰው እናት መሥሪያ ቤታቸው ነው፡፡

‹‹ካፒቴን መሐመድ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት አየር መንገዱ ዛሬ ለደረሰበት የስኬት ደረጃ እንዲበቃ መሠረት የጣሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የማይተካ የመሪነት ሚናቸውን ተጫውተው አልፈዋል። በሕይወት ዘመናቸው ለአየር መንገዱ ባበረከቱት የመሪነት አስተዋፅዖ ምንጊዜም ያስታውሳቸዋል።››

በሐምሌ 1924 ዓ.ም. በሐረር ከተማ የተወለዱት ካፒቴን መሐመድ አህመድ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ለአጭር ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው በሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ ከአሜሪካ ሴንት ሉዊስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በኋላም በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አስፈፃሚ ፕሮግራም ሥልጠናን አጠናቀዋል፡፡

በእርሳቸው አመራር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1970ዎቹ መጨረሻ ወደ መረጋጋትና ልዕልና ገብቷል። የሰው ኃይል ማሻሻያዎችንና ስልታዊ አጋርነትንን ጨምሮ የወሰዷቸው ወሳኝ ተግባሮች የአየር መንገዱን የልዕልና ስም በላቀ ደረጃ መልሰውታል።

የካፒቴኑ ሰብዕና ለዓለም አቀፍ ዕውቅናና ውርስም የበቃ ሆኗል፡፡ ስኬታቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይወሰን አኅጉር አቀፍ ሆኗል። እ.ኤ.አ. በ1992 የአፍሪካ አየር መንገድ ማኅበር ዋና ጸሐፊ በመሆን የአፍሪካን አቪዬሽን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አስቀምጠውታል።

ከሦስት አሠርታት በፊት በማደግ ላይ ካሉት አገሮች ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ ሥራ ፈጣሪዎች አንዱ፣ ለትውልድ አገራቸውና ለዕድገቷ በከፍተኛ ቁርጠኝነት የሠሩ መሪ እንደነበሩ በመግለጽ ስለ ካፒቴን መሐመድ የጻፉት አሜሪካዊው ጸሐፊ ፖል ሄንዝ ናቸው።

 በ92 ዓመታቸው ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ያረፉት ካፒቴን መሐመድ አህመድ ሥርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ ኮልፌ ሙስሊም መካነ መቃብር በማግስቱ የተፈጸመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውና የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሠራተኞችና የቀድሞ ባልደረቦች በተገኙበት ነው፡፡

‹‹የካፒቴን መሐመድ አህመድ ሕይወት የጽናት፣ የፈጠራና ለላቀ ሥራ የማይናወጥ ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነበር። የርሳቸው ትሩፋት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ የሚጥሩትን አፍሪካውያን ትውልዶችን ማበረታታቱን ይቀጥላል፤›› ያለው አፍሪካን ትራቭል ኳርተርሊ ነው።

‹‹መሪ ብቻ ሳይሆኑ ፈር ቀዳጅ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በአጠቃላይ የአፍሪካ አቪዬሽን ላይ ያበረከቱት ከፍተኛ ተፅዕኖ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል፤›› የተባለላቸው ካፒቴን መሐመድ አህመድ፣ እ.ኤ.አ. በ2009 በአኩዋባ አፍሪካ የጉዞ ገበያ ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ ጋር መሸለማቸው ይታወሳል፡፡