ኤልያስ ተገኝ

December 1, 2024

የጉምሩክ ኮሚሽን በገቢ ግብር ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ዕቃ ወደ አገር ውስጥ በገባበት ዓመት የንግድ ሥራ ግብር ሪፖርት ተደርጎ ያልተከፈለ ከሆነ፣ በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ጊዜ ቅድመ ግብሩ ወለዱን ጨምሮ እንዲከፈል ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡  

የቅድመ ግብር ክፍያ (Withholding Tax) ክፍያ መከፈል እያለበት ሳይከፈል ዕቃ ወደ አገር በሚገባበት ጊዜ በጉምሩክ ድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት በኩል ክፍያ መኖሩ ተረጋግጦ አስመጪዎች ክፍያ እንዲፈጽሙ መጠየቃቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ዕቃው በገባበት ወቅት ለጉምሩክ ያልተከፈለ ቢሆንም ግብር ለሚከፍሉበት መሥሪያ ቤት በዓመታዊ ትርፍ ግብር ላይ ተካቶ የተከፈለ ስለሆነ በድጋሚ ልንጠየቅ አይገባም በማለት አስመጪዎች ለኮሚሽኑ ተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረባቸውን አስታውቋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ለገቢዎች ሚኒስቴር ማብራሪያ እንዲሰጥበት መጠየቁን ያስታወቀው የጉምሩክ ኮሚሽን፣ ለጥያቄው የገቢዎች ሚኒስቴር የሰጠውን ዝርዝር ማብራሪያ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ለሚፈጸምባቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ማስተላለፉን ገልጿል፡፡

በማብራሪያው መሠረት የድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት የተደረገው ዕቃው በገባበት የግብር ዘመን ያለው የንግድ ሥራ ትርፍ ግብር ሪፖርት ተደርጎ ከተከፈለ በኋላ ከሆነ፣ በግብር ሕጉ መሠረት ሊካካስ ስለማይችል ቅድመ ግብሩ አይከፈልም፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ ዕቃው ወደ አገር ከገባበት ቀን እስከ የግብር ዘመኑ የንግድ ሥራ ግብር ቀን ድረስ ወለድ ሊከፈል ይገባል ሲል አክሏል፡፡

በሌላ በኩል የሦስት በመቶ ቅድመ ግብር ውሳኔ ለመስጠትና በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ግኝት በአስመጪው ላይ በአገር ውስጥ ታክስ በኩል ሊያስከትል የሚችለውን ኃላፊነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ታክስ ከፋዩ ከተመዘገበበት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተገቢውን መረጃ ለማግኘት የሚያስችል አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ አሠራሩ እስኪዘረጋ ከሚመለከተው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዝርዝር መረጃ ማግኘት እንደሚገባ ገልጿል፡፡

በማንኛውም ዕቃ ላይ ሊከፈል የሚገባው የቅድመ ግብር ክፍያ ሳይከፈል የገባ መሆኑ በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት የተረጋገጠ እንደሆነ፣ ዕቃው ወደ አገር ውስጥ የገባበት (ትራንዚት ያጠናቀቀበት) ቀን ከግብር ዘመኑ ጋር በማገናዘብ በጥንቃቄ እንዲፈጸም ተብሏል፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር በቀረበው ማብራሪያ የሚመለከተው ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ፣ የቅድመ ግብር ክፍያ መክፈል ሲገባው የጉምሩክ ፕሮሲጀር ኮድ በትክክል ባለመሙላት ምክንያት ሳይከፈል እንዲገባ የተደረገን ዕቃ ብቻ የሚመለከት መሆኑን  ጉምሩክ ኮሚሽን ጠቅሷል፡፡

የኦዲት  ግኝት የተገኘበት ታክስ ከፋይ  ከተመዘገበበት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተገቢውን መረጃ ለማግኘት የሚያስችል አሠራር እስኪዘረጋ ድረስ፣ በጉዳዩ ላይ የሚከናወን ኦዲት ከውሳኔ በፊት ኦዲት በተደረጉ ዲክላራሲዮኖች ተመዝግበው የገቡ ዕቃዎች ላይ የቅድመ ግብር ክፍያን በተመለከተ ግብር ከፋዩ ከሚከፍልበት መሥሪያ ቤት ማስረጃዎች ተሟልተው እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚገባ ተብራርቷል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን አክሎም በጉምሩክ በኩል የተሰበሰበ ክፍያ ግብር ለሚከፍሉበት መሥሪያ ቤት ማሳወቅ የሚገባ መሆኑን አሳስቧል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ጠቅሶ እንዳብራራው የድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት በጉምሩክ የሥነ ሥርዓት ሒደት ሊከፈል ሲገባው ሳይከፈል የቀረን ቀረጥና ታክስ ሳይከፈል ከቀረበት ቀን ጀምሮ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማስከፈል መቻሉ ተደንግጓል፡፡

በሌላ በኩል ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሦስት በመቶ የንግድ ሥራ ገቢ ግብር በቅድሚያ ለባለሥልጣኑ እንደሚከፈልና ቅድመ ግብሩ በግብር ዘመኑ የንግድ ሥራ ትርፍ ግብር ጋር የሚካካስ ስለመሆኑ፣ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 እንደሚጠቅስ በአስረጂነት ተመላክቷል፡፡