ኤልያስ ተገኝ

December 1, 2024

የፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ የሚገቡ የንግድ ሸቀጦች የሚስተናገዱበት የጂቡቲ ወደብ

ከጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በፊት የንግድ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ግዥ ፈጽመው ሰነዳቸው የተረጋገጠላቸው አስመጪዎች፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የንግድ ሸቀጦቻቸውን አጠቃለው ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ የጉምሩክ ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በውጤታማነት ተግባራዊ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግና በአጭር የሽግግር ጊዜ ሊፈጠር ይችል ነበረውን ዋጋ ንረት ለማስቀረት፣ ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው የንግድ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት አሠራር ከጥቅምት 28 ቀን ጀምሮ መሰረዙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በፍራንኮ ቫሉታ ግዥ የተፈጸመባቸው የንግድ ሸቀጦች ካሉ ከጥቅምት 28 ቀን ጀምሮ በሁለት የሥራ ሳምንታት ውስጥ ሕጋዊ ሰነዶች ለጉምሩክ  ኮሚሽን ቀርበው፣ ተቀባይነት በማግኘት፣ የጉምሩክ ፎርማሊቲ አሟልተው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የገንዘብ ሚኒስቴር ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና በጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ የተፈረመው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ከላይ ከተገለጸው ቀን በፊት የንግድ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ግዥ የፈጸሙ አስመጪዎች ሰነዳቸውን በሚስተናገዱባቸው የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ቀርበው ማስመዝገብ አለባቸው፡፡

በተጨማሪም ሰነዳቸው ለኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ተልኮ ተቀባይነት ስለማግኘቱ በደብዳቤ ለጉምሩክ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲገለጽ፣ አስመጪዎቹ አስፈላጊውን የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ፈጽመው የንግድ ሸቀጦችን ወደ አገር እንዲያስገቡ እንዲደረግ አቅጣጫ መስጠቱን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ በዚህም መሠረት ከየቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ የተላኩ ሰነዶች በዋና መሥሪያ ቤት በኩል ተረጋግጠው አገልግሎቱ እንዲሰጥ መገለጹን ጠቅሰዋል፡፡

ከላይ የተገለጹትን የአሠራር ቅድመ ሁኔታዎች የተከተሉና በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አስመዝግበው ሰነዳቸው የተረጋገጠና የተፈቀደላቸው አስመጪዎች፣ ከኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ገደብ ውስጥ የንግድ ሸቀጦቻቸውን አጠቃለው ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ አቶ ደበሌ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ የቃሊቲና የሞጆ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም የጂቡቲና የታጁራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የንግድ ሸቀጦቹ ተጠቃለው የማስገባቱን ተግባር እንዲያስፈጽሙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

‹‹በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ይቻላል›› በማለት፣ መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን በመጠቀም ሸቀጦች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ከዚህ ቀደም መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጭምር ይፋ እንዳደረጉት፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ከተወሰኑና አብረው ከማይሄዱ ውሳኔዎች አንዱ ፍራንኮ ቫሉታ ነው፡፡ ውሳኔው ማስተካከያ እንደሚደረግበት ካስታወቁ በኋላ፣ አስመጪዎች ከኢትዮጵያ ውጪ ያላቸውን የውጭ ምንዛሪ ተጠቅመው ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ የሚፈቅደው አሠራር መቅረቱ አይዘነጋም፡፡