
December 1, 2024

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ጽሕፈት ቤት ሕንፃ
የብር የመግዛት አቅምን በእጥፍ ማዳከም ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገቱን በተለይ እ.ኤ.አ. በ2025 የመጀመሪያና የሁለተኛ ሩብ ዓመት በሦስት በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የተደረገ የፖሊሲ ጥናት ጠቆመ፡፡
ጥናቱ በማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ሁለት አማራጮችን ታሳቢ ማድረጉን፣ እነዚህም ቀስ በቀስ (Gradual Scenario) እና የማቀራረብ (Reunification Scenario) መሆናቸውን ያስረዳል፡፡
የማቀራረብ አማራጭ በሚለው የጥናቱ ክፍል የብር የመግዛት አቅም በመቶ እጥፍ ሲዳከም በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ በሚፈጥረው ጫና ምክንያት በጂዲፒው ዕድገት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ነው፡፡ ይህም በዋናነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችና የአገር ውስጥ አምራቾች የግብዓቶች ዋጋ መናር ከፍጆታና ከኢንቨስትመንት ጋር የተገናኘ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያን የንግድ ሚዛን ለማሻሻል ወደ ውጭ የሚላኩ ወሳኝ ምርቶች ዕድገት በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች አዝጋሚ ከመሆኑ ባሻገር፣ የኢኮኖሚውን ማገገም የሚያዘገይ እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል፡፡
በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠበቅባቸው፣ ይህም በአጭር ጊዜ ሲታይ ምርት እንደሚቀንስባቸው ተዳሷል፡፡
ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ የሆነው አምራች ኢንዱስትሪ የሚያስገባቸው ዕቃዎች ዋጋ መጨመር ብቻም ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች ዋጋ ማሻቀብ ምክንያት ዘርፉ አሁን ያለው ደካማ አፈጻጸም የበለጠ እንዲባባስ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
የፖሊሲ ጥናቱ ባቀረበው ድምዳሜ በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ሽግግር ማድረግ የአማራጭ ዘዴዎችን ጥቅምና ወጪ በማመዛዘን ሊደረግ የሚገባው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ብር ከሌሎች የውጭ አገር ገንዘቦች ጋር ያለውን ተመን ከዚህ በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ማዳከም የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ከማቀጨጭ በተጨማሪ የዋጋ ንረት ማሻቀብን ይፈጥራል ብሏል፡፡ ይህም የፍጆታ ወጪ የበለጠ እንዲቀንስና የንግድ ሚዛኑ እንዲባባስ እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ባሻገር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሌሎች ማነቆ የሆኑበት ጉዳዮች እንዳሉት፣ የቢዝነስ ማኅበረሰቡም ሆነ ዜጎች በተለይ መንግሥት እንዲፈታቸው የሚገልጿቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡
የሰላምና የፀጥታ ዕጦት፣ ደካማ የንግድ ሰንሰለት፣ የዋጋ ንረት፣ ዝቅተኛ የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ ረዥምና የተንዛዛ የአገልግሎት አሰጣጥ የሚሉት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡
በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪዎች የተደረገው የፖሊሲ ጥናት እንደሚያብራራው፣ በሌሎች አገሮች ያለው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት በገበያ እንዲመራ የማድረግ ውጤታማነት የሚለካው ወቅታዊ የምንዛሪ ተመንን ማዕከል አድርጎ ለሚመጣ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሲኖር ነው፡፡
የፖሊሲ ጥናቱ ምክረ ሐሳብ እንደሚያስረዳው እሴት የተጨመረባቸው የኤክስፖርት ምርቶች ማምረትና ማስተዋወቅ አንደኛው ጉዳይ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ጥራት ለማሻሻልና የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ከሀብት ልየታ እስከ ድጋፍ የሚደርስ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡
የመስኖ ግብርና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና ማሳደግ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ከማቅረብ ባሻገር ለአምራች ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
በተጨማሪም የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ገበያውን ክፍት ማድረግ ዋጋን ከማረጋጋት ባሻገር፣ ጤናማ የውድድር ከባቢ እንደሚፈጥርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንደሚስብ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡