ዳዊት ታዬ

December 1, 2024

ባንኮች የሚያቀርቡት ዓመታዊ የብድር መጠን ከ14 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ የሚጥለውና ከአንድ ዓመት በላይ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ሊሻሻል መሆኑ ተሰማ፡፡

ባንኮች በሚሰጡት ዓመታዊ ብድር ላይ የተጣለው ገደብ ሊሻሻል ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ሀብታሙ ወርቅነ

በበርካታ ባንኮች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገርለት የቆየው ይህ መመርያ፣ ገደቡን እስከ ማንሳት የሚያስችል ማሻሻያ የሚደረግበት ስለመሆኑ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሐሙስ ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ኢኮኖሚ ትንተናና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ወርቅነህ፣ መመርያውን ለማሻሻል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ማሻሻያውም ገደቡን እስከ ማንሳት ድረስ እንደሚዘልቅ ጠቁመዋል፡፡

የብድር ገደቡ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲያጋጥማቸው ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መቅረባቸው፣ ብሔራዊ ባንክ መመርያውን ለማሻሻል ገፊ ምክንያት እንደሆነበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተለይ ዓመታዊ የብድር ምጣኔያቸው አነስተኛ የሆኑ ባንኮች ‹‹በዚህ መመርያ እየተነገደ ነው›› በማለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቤት ቢሉም መልስ ሳያገኙ መቅረታቸውን ሲናገሩ ነበር፡፡ አሁን ብሔራዊ ባንክ የብድር ገደቡን የማንሳቱ መረጃ መልካም መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡

ሪፖርተር ባገኘው ተጨማሪ መረጃ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ሳምንታት በዚህ መመርያ ላይ ውሳኔውን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹መመርያው ለባንኮች የገንዘብ እጥረት ምክንያት ጭምር ሆኗል›› የሚል ትችት የሚቀርብበት ቢሆንም፣ ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ግን በዚህ እንደማይስማሙ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት ብሔራዊ ባንክ የጣለው 14 በመቶ የብድር ገደብ ለባንኮች የገንዘብ እጥረትም ሆነ የብድር አቅርቦት እክል ምክንያት አይደለም ብለዋል፡፡ በተለይ የ14 በመቶ የብድር ደገብን በቅርቡ ከተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በተለይም የውጭ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያ ጋር ማገናኘት ተገቢ እንዳልሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

የ14 በመቶ የብድር ገደብ መመርያ ሥራ ላይ የዋለው ከሪፎርሙ በፊት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ፣ ከባንኮች አካባቢ ብዙ ጊዜ ሲነሳ የሚሰማውም መመርያው ገዳቢ አለመሆኑን ነው ብለዋል፡፡ ባንኮች በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከነበራቸው የብድር ክምችት ተነስተው በ14 በመቶ ማሳደግ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን ከዚያ በላይ እንዳየልፉ ገደብ ተቀመጠ እንጂ የብድር ክልከላ አልተደረገም ብለዋል፡፡  

ችግሩ ያለው ከመመርያው ሳይሆን ከባንኮች የሊኪውዲቲ ማኔጅመንት (ከራሳቸው ጥሬ ገንዘብ አስተዳደር) ጋር የተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንቱ የሚደረገው የዳሰሳ ጥናት የሚያሳየው፣ ኢኮኖሚው የጥሬ ገንዘብ ችግር እንደሌለበት መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ዳይሬክተሩ፣ አለ የሚባለውን ችግር ከባንኮች የጥሬ ንዘብ አስተዳደርና ከብድር አሰጣጣቸው ጋር አያይዘውታል፡፡

የባንኮች የብድር አፈቃቀድ ሒደቶችና ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ማስባት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የብድር ገደቡ በብሔራዊ ባንክ ላይ ብዙ ጫና እያመጣ ስለሆነ እየታየ መሆኑን፣ በጉዳዩ ላይ ለውጥ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ግን፣ ከ14 በመቶው የብድር ገደብ በበለጠ ባንኮች የተቸገሩት የዓመታዊ ብድራቸውን 20 በመቶ በንድ እንዲገዙ በሚያስገድደው የብሔራዊ ባንክ መመርያ እንደሆነ በመጥቀስ ይህ መመርያ ቢነሳ የተሻለ ትርጉም እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ይህ ቢሆን በባንኮች አካባቢ የሚታየውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ለማስታገስ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አክለዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ኢኮኖሚ ውስጥ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አለመኖሩን፣ ብሔራዊ ባንክም በየጊዜው በሚያደርገው ክትትል ያለው መረጃ የሚያሳየው ችግር አለመኖሩን ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ በባንኮች ላይ የተጣለው አስገዳጁ የ20 በመቶ ቦንድ ግዥ እንደሚሳ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር ያደረገው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ያስረዳል፡፡