ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ብት በቀረበበት ወቅት ክርክር ተደርጎ ነበር

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

December 1, 2024

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ በመጣባቸው የታሪክ ምዕራፎች ወቅት የሚዲያ ነፃነትም ሆነ የሐሳብ ገበያ ሰፋ ብሎ የመታየቱ አጋጣሚ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ አንጋፋው የጋዜጠኝነት መምህር አቶ ማዕረጉ በዛብህ በአንድ ወቅት ባቀረቡት የሚዲያ ምኅዳር የመስፋትና የመጥበብ ታሪክ ቅደም ተከተልን በሚያትት ጥናት ላይ፣ የንጉሡ ዘመን ተገርስሶ ደርግ ወደ ሥልጣን ለመውጣት የተንደረደረበት ዘመንን የሐሳብ ገበያ ሰፍቶ የታየበት ወቅት ነበር ይሉታል፡፡

በአብዮተኞችና በለውጥ ናፋቂዎች ብዙ የሚጻፍበትና ምሁራዊ ክርክሮች በየጋዜጦቹ ይደረግበት የነበረው ያ ሥልጣን ከዘውዳዊ ሥርዓት እጅ ወጥቶ ወደ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር የተሸጋገረበት ዘመን፣ ‹‹ቦግ ብሎ የጠፋ የሚዲያ ነፃነት ብቅ ያለበት›› እንደነበር አቶ ማዕረጉ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ግን ብዙም ሳይቀጥል ደርግ ወደ አምባገነንነት ሲሻገርና ሥልጣን በፍጹም የበላይነት መጠቅለል ሲጀምር ከሰመ ይሉታል፡፡

ከዚያ ወዲህም ቢሆን ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ በቦታው ሲመጣ የሐሳብ ገበያ ከእስር የተፈታ መሰለ ይላሉ፡፡ የሚዲያ ነፃነትን ያረጋገጠ የፕሬስ አዋጅ በወቅቱ መታወጁና የግል ሚዲያ ማቋቋም መፈቀዱ የፕሬስ ውጤቶች እንዲበራከቱ ማድረጉንም ያመላክታሉ፡፡

ይሁን እንጂ መረን የወጣና ፈር የለቀቀ አበቃቀልና ዕድገትን ነው የግል ሚዲያው ዘርፍ የተከተለው በሚል በየጊዜው አዳዲስ የሕግና አሠራር ማሻሻያዎችን መንግሥት መውሰድ ጀመረ፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ድረስ በነበረው ወቅት የሚዲያው ዘርፍ በሰፊው ወለል ብሎ ከተከፈተ የሐሳብ ገበያ ተጠቃሚ ነበር ቢባልም እንኳን፣ የወቅቱ መንግሥት ኢሕአዴግ እንደሚለው ከሆነ ግን የግል ፕሬሱ ፍፁም ነፃ በመውጣቱ ራሱን በራሱ ወደ ማጥፋት ድርጊት ውስጥ የገባበት ዘመንም ነበር በሚል ሲጠቀስ ይሰማል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ግን የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ የተለየ አቅጣጫ መያዙን ነው አቶ ማዕረጉ በጥናታቸው የሚገልጹት፡፡ የሐሳብ ገበያ ምኅዳሩ በተለያዩ አፋኝ ሕጎች እንዲጠብ መደረጉንም ይጠቅሳሉ፡፡

መንግሥት ከ1997 በኋላ የተከተለው የሐሳብ ነፃነትንም ሆነ የሚዲያ ምኅዳሩን ፍፁም የማጥበብ ፖሊሲ በበርካታ ምሁራን፣ በበርካታ ጥናቶችና በበርካታ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ብዙ ዓይነት ፍረጃና ብይን ሲሰጠው የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ አፋኝ የሆኑ አዳዲስ የፕሬስ አዋጅ፣ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች አዋጅ ከማውጣት በዘለለ የፀረ ሽብር ሕጉ በዘርፉ ላይ ከባድ አደጋን መጋረጡ ይነገራል፡፡ መንግሥት ሕጎችና አሠራሮችን እንደ ማጥቂያ መሣሪያነት በመጠቀም ነፃ ሚዲያዎችን መዝጋትና ማዳከምን ሥራው አድርጎታል በሚል ብዙ ሲወቀስ ቆይቷል፡፡ በጊዜው መንግሥት የሐሳብ ነፃነትን መክፈትና ማረጋገጥ ቀርቶ መሠረታዊ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶችንም ይደፈጥጣል የሚለው ክስ ጎልቶ ይሰማም ነበር፡፡

በአጠቃላይ በአገሪቱ ፍፁም አምባገነናዊና የአፈና ሥርዓት መገንባቱ ሲነሳ ነው የቆየው፡፡ ኢሕአዴግ በስተመጨረሻ ግን በሕዝብ አመፅ ሥልጣኑን ለመልቀቅ ተገደደ፡፡ በኢሕአዴግ ቦታ የተተካውና የለውጡ አመራር ሲባል የቆየው አዲሱ መንግሥትም ይህን እንደሚቀይር ቃል ሲገባ ታየ፡፡ ከኢሕአዴግ ወደ ብልፅግና አስተዳደር አገሪቱ በተሸጋገረችበት በዚያ የለውጥ ሰሞን የሚዲያውን ምኅዳርም ሆነ፣ የሐሳብ ነፃነትን የሚያሰፉ ብዙ ቃሎች ሲገቡ ይታይ ነበር፡፡

በወቅቱ ይገቡ የነበሩ ቃሎች የፀረ ሽብር አዋጅን ጨምሮ፣ የፕሬስና የሲቪክ ማኅበራት አዋጆች እንደሚሻሻሉ የሚጠቁሙ ነበሩ፡፡ አፋኝ የሆኑ ሕጎች ላይ ማሻሻያ እናደርጋለን የሚለው የመንግሥት ቃል ለሚዲያ ምኅዳሩም ሆነ፣ ለሐሳብ ገበያው መስፋት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ አሳድሮ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ለውጡ ከመጣ ገና በስድስተኛ ዓመቱ የሐሳብ ነፃነትን የሚጋፋ፣ የሲቪክና የሚዲያ ምኅዳሩን የሚያጠብ አዳዲስ አሠራሮችና አዋጆችን መንግሥት ይዞ መምጣቱ ከፍተኛ ክርክር እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ በ2011 ዓ.ም. ተረቆ የፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ በኢሕአዴግ ዘመን ብዙ አቤቱታ ሲቀርብበት የቆየውን የሚዲያ ምኅዳርና የሐሳብ ነፃነትን የተመለከተውን አቤቱታና ብሶት እንደሚፈታ ታምኖበት ነበር፡፡ በሒደት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚታወጁ ሕጎችና አሠራሮች ግን ዘርፉን እንዲያውም ወደኋላ የሚጎትቱ እየሆኑ ነው ተብሎ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡

በቅርቡ የቀረበው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ከሁሉም በጎላ ሁኔታ ከባድ ውዝግብ አስነስቷል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ሥልጣን ወሰንን በእጅጉ እንዲያሰፋ ተደርጎ የተረቀቀ ነው የተባለው ማሻሻያ አዋጁ፣ የባለሥልጣኑ ተቆጣጣሪ ቦርድን የማቋቋም ሒደትም በተመለከተ በርካቶችን አላግባብ ያወዛገበ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ መንግሥት በቅርቡ ሦስት የሲቪክ ማኅበራትን ማገዱ፣ እንዲሁ የሲቪክ ምኅዳሩ ወዴት እያመራ ነው የሚል ጥያቄ ፈጥሯል፡፡ በየጊዜው ማስጠንቀቂያ የሚወጣባቸው መገናኛ ብዙኃንና የሲቪክ ማኅበራት ቁጥር ከመበራከቱ በተጨማሪ፣ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ሥራቸውን እየተው መሰደዳቸው በሒደት ወደ ሲቪክ ማኅበራት መንደርም መሸጋገሩ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡

በርካታ የመብት ተሟጋች ቡድኖችና ተቆርቋሪዎች የሐሳብ ገበያው እየጠበበ ነው፣ የሚዲያ ምኅዳሩም ወደ ቀደሙ ሁኔታዎች እየተመለሰ ነው የሚል ስሞታ እያቀረቡ ይገኛል፡፡ በለውጡ ማግሥት በዘርፉ የፈነጠቀው ተስፋ እየጠወለገ ወደ አሥጊ መንገድ እየተጓዘ ነው የሚል ሙግትም ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነሳ ነው፡፡

ይህ ከምን የመነጨ ነው ለሚለው ማብራሪያ የሰጠው የሕግ ባለሙያውና ጋዜጠኛው አቶ ሰለሞን ጎሹ፣ የማሻሻያ አዋጁ የፈጠረው ግርታና ውዝግብ ዋና ማጠንጠኛ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በለውጡ ማግሥት የሕግ ማዕቀፎችን ሪፎርም የማድረጉ ተነሳሽነት የትም አገር ባልታየ ሁኔታ ከራሱ ከመንግሥት እንደመነጨ ይናገራል፡፡ ይህን ተከትሎም በበጎ ፈቃድ በርካታ ሕግ አዋቂዎች በተሳተፉበት ሁኔታ ብዙ አፋኝና ጎታች የሚባሉ ሕጎችን የማሻሻል ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ይጠቅሳል፡፡ አሁን እየተሠራበት ያለው የብዙ አገሮች ልምድና ምርጥ አሠራርን የቀመረ አዋጅ በዚህ መንገድ ተረቆ ወደ ተግባር መገባቱንም ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን ይህ ከሆነ ከጥቂት ዓመት በኋላ አዋጁ ፈጥሮ  የቆየውን አዲስ ዕድልና በጎ ለውጥ በሚቀለብስ መንገድ አሁን የሕግ ማሻሻያ በሚል አደናቃፊ የማሻሻያ ሐሳቦች መቅረባቸውን ይናገራል፡፡

‹‹ማሻሻያው ሰሞኑን በተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ሲደረግበት እንደታየውም አወዛጋቢ ጭብጦችን ይዞ የቀረበ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአዋጁ በኅብረተሰቡ ጥቆማ የሚዲያ ተቋማት ተቆጣጣሪ ቦርዱ አመራሮች ይመረጣሉ ተብሎ ተቀምጦ ነበር፡፡ አሁን ግን በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የቦርዱም ሆነ የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካላት አመራሮች እንዲመረጡ የሚል ማሻሻያ ነው የቀረበው፡፡ ከዚህ ቀደም በአዋጁ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎች የቦርዱ ተቆጣጣሪ አባል መሆን አይችሉም ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ እንዲቀር ተብሏል፡፡ የተቆጣጣሪ ቦርዱ ሥልጣን ተብለው የተቀመጡ ነገሮች አሁን ወደ ባለሥልጣኑ እንዲዛወሩ የሚያደርጉ ማሻሻያዎችም ቀርበዋል፡፡ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች በውይይት መድረኩ ተቋሙ ባለሥልጣን ቢባልም ሥልጣን ያነሰው ስለመሆኑ ተከራክረዋል፡፡ ሥልጣን አንሶናል ይጨመርልን ነው ነገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ አካላት በፓርላማው ቀርበው ድምፃቸውን ማሰማታቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ የሕግ ማሻሻያው የሚዲያ አዋጁ አምጥቶታል ተብሎ የሚገመተውን የምኅዳር መስፋት መልሶ የሚያጠብ እንደሆነ ከየአቅጣጫው ሥጋታቸውን አሰምተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ ነው፤›› በማለት ነው አቶ ሰለሞን ሰፊ ገለጻ ያደረገው፡፡

የሚዲያ ምኅዳሩን የተመለከቱ ሕጎች በትንሹ ከ30 በላይ በሆኑ አዋጆች ውስጥ ከሌሎች ሕጎች ጋር ተሰባጥረው እንደተቀመጡ የሚያወሳው አቶ ሰለሞን፣ ይህን ሁሉ በአንድ ያሰባሰበ ጥራት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ብዙ ልፋት ጠይቆ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ ከመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ ከዲጂታል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አዋጅ፣ የማስታወቂያ አዋጅ፣ ከሰብዓዊ መብት፣ ከምርጫ፣ ከሽብር አዋጅና ከሌሎችም ሕጎች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠት ለሦስት ዓመታት ከ130 በላይ የሕግ አዋቂዎች ተሳትፈውበት በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ ሰለሞን ያስታውሳል፡፡

‹‹አሁን ያለው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅም በዚህ መሰሉ መንገድ ተዘጋጅቶ ራሱ መንግሥት ጭምር ያዋጣል ብሎ ተቀብሎት ነው ሕግ የሆነው፡፡ በአተገባበር ሒደት ግን ሕጉ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይሄድም ተባለ፡፡ ሕግ ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይሄድም በሚል ብቻ ሳይሆን፣ ለሕጉ መተግበር የሚያመች ሁኔታ ፈጥረናል ወይ በሚል መንገድም መታየት አለበት፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራትና ሕጉ የሚያስቀምጠው ደረጃ መድረስም አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አልሄድ አለኝ በሚል ብቻ አይቀየርም፡፡ ለምን ማሻሻያው ተደረገ የሚለውን ራሱ መንግሥት ነው የሚያውቀው፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ያዋጣል፣ ይበጃል ተብሎ እንደተገባበት ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ ማሻሻያው ሲቀርብ ተጨባጭ ሁኔታ እየተባሉ የቀረቡ ጉዳዮች በአብዛኛው ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ማሻሻያው በዋናነት ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር ተያይዞ ይቅረብ እንጂ፣ በዚህ አያያዝ በሌሎች ሕጎችም በየተራ የማይመጣበት ሁኔታ አይታየኝም፤›› በማለት ነው ማብራሪያውን ያጠቃለለው፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ሲሆኑ፣ የነገሩ ጥንስስ የጀመረው በኢትዮጵያ ግጭቶች እየተበራከቱ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ በሚዲያው ወይም በሐሳብ ገበያው ትርክትን በበላይነት የመቆጣጠሩ ጥያቄ ሲያከራክር መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከሉዓላዊነት፣ ከአገር ጥቅም፣ እንዲሁም ከብሔራዊ ደኅንነት ማስጠበቅ ጋር በተያያዘ በርካታ ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆኑ የሲቪክ ማኅበራትም ጫና ያጋጥማቸው የጀመረው ከጦርነቱ ወዲህ ነው፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች የመታሰር፣ ታፍኖ የመሰወርና ሌላም ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር ከፖለቲካ ለውጡ ወዲህ መከፈት ጀመረ ተብሎ ብዙ ሲደነቅ ቆይቷል፡፡ በዘርፉ የተፈጠረው ለውጥ በዓለም ደረጃ ሲወደስም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ግጭቶች መበርከት ሲጀምሩ መንግሥት ግጭቶቹ እንዳይፈጠሩ ያደረገው ጥረትም ሆነ ግጭቶቹን ለመፍታት የተከተለው መንገድ መተቸት ሲጀመር፣ የሚዲያ ምኅዳሩ ሰፍቶ እንዲቀጥል መፍቀድ አደገኛ ነው ወደ ሚል ድምዳሜ ባለሥልጣናቱን ሳይከት አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ ዓውዱ ጤና ማጣት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ነው የሲቪክም ሆነ የሚዲያ ምኅዳሩ የመጥበብ አዝማሚያ የጀመረው፤›› በማለት ነው አቶ ያሬድ ያብራሩት፡፡

በለውጡ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚዲያም ሆነ የሲቪክ ምኅዳሩ ደግሞ ወደ መጥበብ ችግር እንደማይገባ ቃል ገብተው ነበር፡፡ በቀድሞው መንግሥት ጋዜጠኞችንም ሆነ የመብት ተሟጋቾችን በፀረ ሽብር አዋጁና በሌሎችም ሕጎች አሳቦ ማሳደዱና ማዋከቡ ራሱ መንግሥትን እንደ አሸባሪ እንዲታይ የሚያደርግ ነው በማለት ጭምር ለሐሳብ ገበያው ነፃነት መከበር ትልቅ ተስፋ የፈጠረ ቃል ተገብቶ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ የለውጡ ዘመን የፖለቲካ ጫጉላ ካለፈ በኋላ ግን ነገሮች ቀስ በቀስ ወደ መጥበብ መግባታቸውን አቶ ያሬድ ያክላሉ፡፡

ከዚህ በመነሳትም፣ ‹‹አሁን በሽብርተኝነት ወንጀል ጭምር፣ ግጭት በማነሳሳት፣ ጥላቻ በመቀስቀስና በሌላም እየተባለ የሚዲያ ባለሙያዎች እየተከሰሱ ነው፡፡ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሽብር ሰበብ የተወነጀሉና የታሰሩ ሳይሆኑ እኛ ነን አሸባሪዎች ሲሉ ከገለጹት ከቀደመው ሥርዓት ሕግን በማጥቂያ መሣሪያነት ከመጠቀም አሠራር ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የሐሳብ ገበያውም ሆነ የሚዲያ ምኅዳሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀደመው ሁኔታ እየተመለሰ መሄዱን አመልካች ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ግን ይህን የሚዲያ ምኅዳር ጠቧል፣ የሐሳብ ገበያው አደጋ ላይ ወድቋል የሚለውን ሥጋት ሲጋራው አይታይም፡፡ የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት ምሥረታ በማስመልከት ሰፊ መግለጫ ያወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የመገናኛ ብዙኃን ሰፍቶ ከሞላው የሚዲያና የሐሳብ ምኅዳር ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡ ለውጡ የሚዲያ ነፃነት እንዲከበርና ሚዲያዎችም በሕግ የሚመሩ የብዝኃ ሐሳቦች ማስተናገጃ መድረክ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡