ዜና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በቆየው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ ላይ ከፍተኛ…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: December 1, 2024

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ያስከተለ ደንብ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ ደንብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ተወያይቶበት፣ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡

በፓርላማ በፀደቀው ደንብ እንደተገለጸው እስከ 20 ሺሕ ብር ለሚገመት ሀብት ሁለት ሺሕ ብር፣ ከ100 እስከ 200 መቶ ሺሕ ብር ለሚገመት ሀብት አሥር ሺሕ ብር፣ ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት 82 ሺሕ ብር፣ ከከዘጠኝ ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት እስከ አሥር ሚሊዮን 330 ሺሕ ብር የዳኝነት ክፍያ እንዲከፈል ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም ከሃያ ሚሊዮን እስከ 30 ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት 840 ሺሕ ብር፣ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት አንድ ሚሊዮን ብር፣ ከ50 ሚሊዮን እስከ 60 ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት 1.5 ሚሊዮን ብር፣ ከ90 ሚሊዮን  ብር እስከ 100 ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት 2.1 ሚሊዮን ብር፣ ከ100 ሚሊዮን እስከ 200 ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት 3.8 ሚሊዮን ብር፣ ከ500 ሚሊዮን እስከ 600 ሚሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር፣ ከ900 ሚሊዮን እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ለሚገመት ሀብት 11 ሚሊዮን ብር የዳኝነት ክፍያ እንዲከፈል ይደነግጋል፡፡

የዳኝነት ክፍያው ለክስ፣ ለተከሳሽነት ክስ፣ ለይግባኝ አቤቱታ፣ ለመስቀለኛ ይግባኝ፣ ለመስቀለኛ መቃወሚያ ወይም ለሰበር አቤቱታ፣ በመንግሥት ተቋማት የሚቀርቡ ማናቸውም ክስና አቤቱታዎችን ጨምሮ በደንቡ ተደንግጓል፡፡

የዳኝነት ክፍያ የሚፈጸመው ፍርድ ቤቱ አመቺ ነው ብሎ ባመነበት በጥሬ ገንዘብ፣ በባንክ በኩል በክሬዲት፣ በዴቢት ካርድ ወይም በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ዘዴ ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

ከሳሽ የሆነ ወገን የዳኝነት ክፍያውን ፈጽሞ መዝገቡ ቀጠሮ ከመያዙ በፊት፣ ወይም ቀጠሮ እንደተሰጠው ወይም መጥሪያ ወጪ ከመሆኑ በፊት ክሱን ለማቋረጥ ቢወስን ለዳኝነት ከከፈለው ገንዘብ ላይ አምስት በመቶ ተቀንሶ ቀሪው ይመለስለታል፡፡ ክስ ከመስማት በፊት ክስ ቢያቋርጥ ደግሞ ከተከፈለው የዳኝነት ክፍያ 15 በመቶ ተቀንሶ ቀሪው ይሰጠዋል፡፡

በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ ክርክር፣ የቀለብ ክፍያና የልጅ አስተዳደግን አስመልክቶ የሚቀርብ አቤቱታ፣ በሕግ አግባብ በደሃ ደንብ እንዲከራከር በፍርድ ቤት የተወሰነለት ሰው የዳኝነት ክፍያው አይመለከተውም፡፡

የዳኝነት ክፍያ የሚፈጸመው የፍርድ ቤት መዝገብ ከመከፈቱና ቁጥር ከመሰጠቱ በፊት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በፓርላማ የፀደቀውን ደንብ በተመለከተ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ የክፍያው መሻሻል የዘገየ ቢሆንም፣ የቀረበው የክፍያ ምጣኔ ግን ፍትሕን የመግዛት ያህል ተደርጎ የቀረበ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች ለዳኝነት መክፈል ምናልባት በንግድና በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሀብታሞች ምንም ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን መክፍል የማይችሉና የደሃ ደንብን የማያውቁ ዜጎች ፍትሕን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በደሃ ደንብ ፍትሕ ለማግኘት የሚመጣውን ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህ ክፍያ ደንብ ሲዘጋጅ ረቂቁን በማዘጋጀት ከተሳተፉት የሕግ ባለሙያዎች መካከል አንዱ አቶ ታፈሰ ገብረ መድኅን እንደሚሉት፣ ማሻሻያው የዘገየና ነባሩ ክፍያ ለፍርድ ቤት አገልግሎት ያልተመቸ ነበር ይላሉ፡፡ አዲሱ ደንብ ከተለያዩ አገሮች ልምድ የተቀዳና ብዙ ውይይት የተደረገበት በመሆኑ የተጋነነ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤት ራሱን የቻለ የፋይናንስ ነፃነት እንዲኖረውና በቂ ዕውቀት ያላቸው ዳኞች ሥራ ላይ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ረቂቁ ይፋ ሲደረግ የጠበቆች ማኅበርና አባላት በየግላቸው በደንቡ ውስጥ የተደነገገው የገንዘብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሰው እንዲስተካከል አሳስበው ነበር፡፡

የቀድሞ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ወቅት የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ቀድሞ ሥራ ላይ የነበረው የክፍያ ምጣኔ ዕርከን ስድስት ብቻ ነበር፣ ነገር ግን አሁን የመጣው ከ42 በላይ በመሆኑ የከፍያ መጠኑን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ በተሻሻለው ደንብ የክፍያ ምጣኔው ዕርከኑን ዝቅ በማድረግ የክፍያ ጣሪያውን ከፍ ማድረግ ይቻል ነበር ያሉት አቶ ታምራት፣ ከጅምሩ ደንቡ ሲዘጋጅ ሥሌቱን የሠሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በአገሪቱ ውስጥ ምን ያህል የዕውቀት ችግር እንዳለ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

ወደፊት ለዳኝነት የሚፈጸመው ክፍያ ለአርሶ አደሩ አይነኬ እንደሚሆንበት ጠቅሰው፣ ዜጎች ለዘመናዊ ፍትሕ አዋጪነት የሚኖራቸው እምነት እየጠፋ ወደ ባህላዊ ሽምግልናና የዳኝነት ሥርዓት እንዲሄዱ ከዚም ሲያልፍ ደግሞ ከሕግ ውጪ ባሉ ሕገወጥ ተግበራት በራሳቸው መንገድ እንዲጓዙ ደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ዜጎች መብታቸውን ተቀምተው እንዲቀመጡና በደሃ ሕግ አስረድቶ ፍትሕን ለማግኘት ማስረዳት ባለመቻል ለፍትሕ ዕጦት ይዳረጋሉ ሲሉም አክለዋል፡፡

ደንቡ በሕዝብ ተወካየች ምክር ቤት በፀደቀበት ወቅት አስተያየት የሰጡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ‹‹ይህንን ደንብ ማፅደቅ ካለብን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የዚህ ክፍያ መሻሻል አንፃራዊ ለውጥ ያመጣል ከሚል ተስፋ ካልሆነ በስተቀር፣ አሁን ባሉበት ደረጃ ሥራቸው አጥጋቢ ነው ብዬ አላምንም፤›› የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

አክለውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚከፍለው ልክ ገለልተኛና ተገማች ፍትሐዊ የዳኝነት አገልግሎት ሊያገኝ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋ ባንጉ የተባሉ ሌኛው የምክር ቤት አባል ክፍያው በእጥፍና ከዚያም በላይ መጨመሩን ገልጸው፣ በዚህ ሁኔታ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊከፍል ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ በመሆኑም አንድ ደሃ 4,000 ብር ወይም 3,000 ብር ባይኖረው ፍትሕን እንዲያጣ ስለሚያደርገው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ እንዲሆን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ አወቀ አምዛየ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ የሚነሳው ችግር ሳይፈታ ክፍያ በማሻሻልና ገንዘብ በመሰብሰብ ብቻ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ትክክለኛ መንገድ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥት በሰጡት ምላሽ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፍትሕ ዘርፍ የተሻሻሉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ የቀረበው የክፍያ ተመን ጥንቃቄ ተደርጎበትና የጎረቤት አገሮች ልምድ ተወስዶ መሠራቱንና በብዙ ጥንቃቄ ጊዜ ተወስዶ የተዘጋጀ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በብዙ መመዘኛ ተገምግሞ ጉዳት እንዳያደርስ ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ተዘጋጅቶ የቀረበ የክፍያ ደንብ ነው ብለዋል፡፡