ዜና የፌዴራል ዋና ኦዲተር በኃላፊዎች መልካም ፈቃድ የሚደረግ የፓስፖርት አሰጣጥ ሊቆም ይገባል አለ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: December 1, 2024

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኢሚግሬሽንና ዜግነትና አገልግሎት በኃላፊዎች መልካም ፈቃድ የሚደረግ የፓስፖርት አሰጣጥ ሊቆም ይገባል አለ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አሰጣጥ ውጤታማነት፣ የክዋኔና ፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ላይ ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት ሲደረግ ነው ይህ የተባለው፡፡

በኦዲት ሪፖርት ግምገማው ወቅት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት አለመገኘታቸው ቋሚ ኮሚቴውን ያስቆጣ ሲሆን፣ የጥሪ ደብዳቤው ከአሥር ቀናት በፊት የተላከላቸው ቢሆንም በውይይቱ ወቅት ከአገር መውጣታቸው ተገልዷል፡፡ ድርጊቱ አግባብ ባለመሆኑ እንዳይደገም ሲል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

በኦዲት ውይይቱ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ ተቋሙ ግልጽ አሠራር ባለማስቀመጡ አስቸኳይ ፓስፖርት ፈላጊዎች ሲኖሩ በኃላፊዎች ደብዳቤ እየተመራ ፓስፖርት ይሰጥ እንደነበር በኦዲት ምርመራ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹አሠራሩ በግልጽ በተቀመጠ መመርያ ሊመለስ ይገባል እንጂ፣ በኃላፊዎች መልካም ፈቃድ የሚሰጥ የፓስፖርት አሰጣጥ ሊቆም ይገባዋል ሲሉ፤›› ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል፡፡

‹‹በመመርያ የማይመለስ ከሆነ አሁንም ቢሆን ኃላፊዎችን ማግኘት የሚችል ፓስፖርት ቢያገኝ፣ ኃላፊዎችን ማግኘት የማይችል ደግሞ የዕድሉ ተጠቃሚ ላይሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም አስቸኳይ አገልግሎት የሚፈልግ አካል በአሠራር መሠረት እንዲያገኝ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

ለፓስፖርት ተመዝግበው ጊዜው ያለፈባቸው ዜጎች ምንም ዓይነት መመርያ ሳይኖር በቅጣት ከተመዘገቡ በኋላ፣ የተሰበሰበው ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና አለመግባቱን ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ መሠረት በተጨማሪ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ስድስት ዓመት ያለፈው ቢሆንም፣ ይህ ተቋም አሁንም ሪፎርም ላይ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ክፍተቶቹን ሊሞላ እንዳልቻለ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር መፅደቅ የነበረበትን መመርያ ተቋሙ በራሱ አፅድቆ ወደ ሥራ ማስገባቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋሙ የግድ ቅንጅታዊ አሠራርን ሊተገብር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ላይ የተሠራው የኦዲት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከኤሌክትሮኒክስ ቪዛ ገቢ ተሰብስቦ ወደ አገልግሎቱ በትክክል መግባቱ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

በተቋሙ የፋይናንስና የበጀት ዳይሬክቶሬት ተሰበሰበ ተብሎ የቀረበው፣ በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከቀረበው የተመዝጋቢ ሰነድ ጋር የማይገናኝ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡

በሰኔ 2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ተሰብሳቢ ተብሎ የተመዘገበ 4.1 ሚሊዮን ብር ከማን እንደሚሰበሰብ ማስረጃ እንዲቀርብ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም፣ አገልግሎቱ ሊያቀርብ አለመቻሉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡

ከ508 ሺሕ ብር በላይ ተከፋይ ተብሎ የተመዘገበ ነገር ግን ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅ መሆኑን፣ ከውጭ አገር ኩባንያ ላምኔት ለማስመጣት ከመመርያ ውጪ  ያለ ውድድር በቀጥታ ግዥ 89.3 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ተቋሙ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ አፅድቆ ወደ ሥራ አለመግባቱ፣ የሥራ መዘርዘር (Job Description) የሌለው መሆኑ፣ አጠራጣሪ የሆኑ ተገልጋዮች ሲያጋጥሙና ዜግነትን የሚያጣራው በተቋሙ ሠራተኞች መልካም ፈቃድ መሆኑን፣ ፓስፖርት ፈላጊዎች በመመርያና በስታንዳርድ መሠረት አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ የተቀመጠ የጊዜ ሰሌዳ እንደሌለ የኦዲት ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የፓስፖርት ቀጠሮ ያለፈባቸው ግለሰቦች የሚስተናገዱበት አሠራር አለመኖሩን፣ ቀጠሮ ያለፈባቸውን ግለሰቦች በቅጣት ለማስተናገድ የቅጣት መመርያ ሳያዘጋጅ በግለሰቦች ስም የባንክ አካውንት ተከፍቶ የቅጣት ክፍያ የሚቀበል መሆኑን፣ የሠራተኞች የሥነ ምግባር መመርያ ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የሚያስችል እንዳልሆነ፣ በተቋሙ ላይ ተገልጋዮች ቅሬታ የሚያቀርቡበት አሠራር የሌለው መሆኑንም የኦዲት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት ግዥ የውል ስምምነት ማስረጃዎችን አደራጅቶ እንደማይዝ፣ የፓስፖርት መረጃ ጥራትና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሠራር ሥርዓት አለመኖር የሚሉና በርካታ ክፍተቶች ቀርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ኢንስፔክሽን ክፍል ኃላፊ ዓባይነሽ ተሾመ በቀረበው የኦዲት ክፍተት ላይ በሰጡት ምላሽ ተቋሙ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ጠቅሰው፣ የድርጊት መርሐ ግብርና ግብረ መልስ የማያቀርብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ የኦዲት ግኝትን መነሻ በማድረግ ዕርምጃ ተወስዶ ግብረ መልስ እንዲያጣ ቢጠየቅም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ እንደማይሰጥም አክለው ገልጸዋል፡፡

የተቋሙ ተሰብሳቢ ሒሳብ 189 ሚሊዮን ብር ተከፋይ ሒሳቡ ደግሞ 33 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገልጸው፣ ገንዘቡ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ በሰጡት ምላሽ፣ የተፈጠሩት ክፍተቶች አንዳንዶቹ ከቸልተኝነትና ሕግን በመጣስ ምንም አይመጣም በሚል የተፈጸሙ እንደሆኑ፣ አንዳንዶቹ ከመረጃ መዛነፍ ጋር የተፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ብልሹ አሠራርና የሥነ ምግባር መጓደል ሲኖር አስቸጋሪ ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን ደንብና መመርያ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁንና ቀሪው ተግባር ከፍትሕ ሚኒስቴር ተቀብሎ የማፅደቅ ሥራ ይሆናል ብለዋል፡፡ ‹‹ከሕግ ውጪ ይፈጸሙ የነበሩ የግዥ ክፍተቶችን አሁን በመተው ከሚመለከተው አካል በማስፈቀድ እየገዛን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በኃላፊዎች ፊርማ አማካይነት ለውስን ሰዎች ፓስፖርት ይሰጥ እንደነበር ገልጸው አሁን ግን በመመርያው መሠረት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የፓስፖርት እጥረት ስለሌለበት አስቸኳይ ፓስፖርት ለሚፈልጉ ዜጎች ማሟላት ያለባቸውን ካሟሉ ለሁሉም በተፈለገው ጊዜ ይሰጣል ብለዋል፡፡

 ዜግነትን ለማጣራት በኮሚቴ አማካይነት ሲከናወን የነበረው ሥራ፣ በርካታ የጎረቤት አገሮች ዜጎች ወደ ተቋሙ እየመጡ ችግር ስለነበረው ነው ብለዋል፡፡  

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አሬሬ ሞሲሳ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋም በአመራሮች በጎ ፍላጎት እንጂ በአሠራር እየተመራ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ አግባብ ባለመሆኑ እንዲስተካከልና ተቋሙ ከዘመቻ ሥራ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ተቋሙ በሕዝቡ ዘንድ የሚነሳበት ቅሬታ በርካታ መሆኑንና አመራሮቹ ይህን በመረዳት የተቋሙን ስም መቀየር የሚቻለው በወሬ ሳይሆን በሥራ በመሆኑ፣ ትናንት የነበረውን ጥሩ ያልሆነ ስም ለመቀየር በትጋት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡