

ዜና የጎረቤት አገሮች ዜጎች የኢትዮጵያን ፓስፖርት ያገኙበት የአሠራር ክፍተት እንዲዘጋ ፓርላማው አሳሰበ
ቀን: December 1, 2024
የጎረቤት አገሮች ዜጎች የኢትዮጵያን ፓስፖርት ማውጣት ያስቻላቸውን የአሠራር ክፍተት፣ የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ተቋም በፍጥነት እንዲዘጋ ፓርላማው አሳሰበ።
ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባካሄደው ክዋኔ ኦዲት የተለዩ ግኝቶችን ሲገመግም ነው።
የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በሰጠው ምላሽ ፓስፖርት ለማውጣት የሚጠይቁ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው በተሟላ መንገድ ለመለየትና ለማረጋገጥ የሚያስችል አገር አቀፍ ሥርዓት በበቂ ሁኔታ የተገነባ ባለመሆኑ፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር በቆዳ ቀለምና በቋንቋ የሚመሳሰሉ የጎረቤት አገር ዜጎች ባልተገባ መንገድ የኢትዮጵያን ፓስፖርት (ዜግነት) ያገኙበት ሁኔታ መኖሩን አምኗል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቢቂላ መዝገቡ በሰጡት ምላሽ፣ የጎረቤት አገሮች ዜጎች የኢትዮጵያን ፓስፖርት በእጅጉ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። አብዛኞቹ የጎረቤት አገሮች ዜጎች ከኢትዮጵያውያን ጋር በመልክም መመሳሰላቸውና ተመሳሳይ ቋንቋም የሚናገሩ መሆኑ ዜግነት የማጣራት ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል። ዜግነታቸውን ለማጣራት የሚረዱ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ማቅረብ የማይችሉባቸውን የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር፣ በተጓደሉ መረጃዎች ፓስፖርት ያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።
‹‹ዛሬ ግን አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኑን ለማረጋገጥ የእናት ወይም የአባት መረጃና ማስረጃ እንዲያቀርብ የሚጠየቅ በመሆኑ ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል፤›› ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የእናት ወይም የአባት መረጃና ማስረጃ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ለምን እንጠየቃለን የሚሉ ቅሬታዎችን ያሰሙ በማሰማት አገልግሎቱን ያገኙ እንደነበር የገለጹት አቶ ቢቂላ፣ አሁን ግን ኮሚቴ በማዋቀር እንደዚህ ዓይነት ቅሬታ የሚያሰሙ አካላት ላይ ጥልቅ ምርመራ ማድረግ ሲጀመር አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ዜግነት የሌላቸው ሆነው እንደተገኙ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊዎች ወደ ተቋሙ ሲመጡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው መሆኑን ለማጣራት የሚያስችል ማንዋል መዘጋጀቱን፣ ከሶማሌ ክልል ለሚመጡት አገልግሎት ፈላጊዎች ደግሞ ከክልሉ ጋር በመቀናጀት በተቋቋመ ኮሚቴ የአካባቢው ተወላጆች መሆናቸው እንዲጣራ፣ እንዱሁም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከክልሉ ሕግ አስከባሪ ተቋም ይዘው እንዲቀርቡ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ይቀርፋሉ ተብሎ የሚታሰቡት ዲጂታል የቤተሰብና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓትና ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም መሆናቸውን ጠቁመዋል። በሁለቱ ፕሮግራሞች የሚገኙ ዲጂታል መረጃዎችን ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሲስተም ጋር እንዲናበብ በማድረግ አገልግሎት የሚጠይቁ ሰዎችን ዜግነት በቀላሉ ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በሪፎርም ሒደት ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም የሚሰጠው አገልግሎት የአገርን ደኅንነትና ሰላም ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው ከመሆኑ አንፃር የዜግነት መገለጫ የሆነው ፓስፖርት በሕገወጦች እጅ እንዳይገባ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል።
ተቋሙ ይህንን ችግር ለመፍታት እየተከተለ ያለውን ማንዋል አሠራር በማዘመን በመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት ከአገሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ጭምር፣ ክፍተቱን ሊደፍን እንደሚገባም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ አሳስበዋል።