
December 1, 2024

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ
በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አማካይነት የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ፣ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ በሁሉም ባንኮች የነበረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከ3.1 ቢሊዮን ዶላር ወደ 5.9 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ማሞ ምሕረቱ ይህን ያስታወቁት፣ የአውሮፓ ቻምበር በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኩባንያ ሥራ አስኪያጆችጋር በሚያደርገው የኔትወርኪንግ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በነሐሴ 2016 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ቀድሞ ከነበረበት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ወደ 3.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
‹‹የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲተመን መደረጉን የምንኮራበት ውሳኔ ነው፤›› ያሉት ገዥው፣ በባንኮችና በትይዩ ገበያው መካከል መቶ ፐርሰንት ደርሶ የነበረው የምንዛሪ ተመን ልዩነት ወደ አምስት በመቶ ወርዷል ብለዋል፡፡
ባንኮች በየወሩ ቢያንስ 500 ሚሊዮን ዶላር ከገበያ እየገዙ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚሸጡ፣ ይህም የምንዛሪ ተመኑ በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ ወዲህ የታየ አፈጻጸም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በባንኮች መካከል የሚደረገው የእርስ በርስ የውጭ ምንዛሪ ግብይት 100 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን የገለጹት አቶ ማሞ፣ ሪፎርሙ ባንኮች ያላቸውን ትርፍ የውጭ ምንዛሪ እርስ በራሳቸው እንዲገበያዩ ዕድል መፍጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡ በዚህም ለበርካታ ዓመታት በእጥረት ይቸገር የነበረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት አሁን ግን ከበቂ በላይ ክምችት አለው ብለዋል፡፡
የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አበረታችና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚጨምር፣ ኢንቨስትመንትንና ኤክስፖርትን የበለጠ የሚያሻሽል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ 185 የአውሮፓ ኩባንያዎችን አቅም የያዘው የአውሮፓ ቻምበር በኢትዮጵያ ለመንግሥት ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ መሆኑን፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡
የቻምበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ቤን ዲፕሊቴሬ በኢትዮጵያ ለንግድና ለኢንቨስትመንት አመቺ ያልሆኑ ማነቆዎች መኖራቸውን፣ በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የጉምሩክ ሥርዓት ምቹ አለመሆን፣ የታክስ አጣጣልና አሠራር፣ እንዲሁም የመሬት አቅርቦት ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪው እየተሻሻለ ቢሆንም የአውሮፓ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ የብር እጥረት እያጋጠማቸው መሆኑን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡