ወጣት ዮናታን ሊዮ

ወጣት በሱስ የባከነ ሕይወት

የማነ ብርሃኑ

ቀን: December 1, 2024

ወጣትነት ትኩስነትና አፍለኝነት ነው፡፡ ይህ የዕድሜ ክልል በጥበብና በማስተዋል ካልታለፈ ወዳልተፈለጉና መልካም ወዳልሆኑ ነገሮች ሊያመራ ይችላል፡፡ ወጣትነት ኃይል፣ ጉልበትና አቅምም ነው፡፡ ይህ ኃይል፣ ጉልበትና አቅም የሚፈለገው ቦታ ላይ ካልዋለና የሚባክን ከሆነ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ወጣትነት ብዙ ፈተናና ፍላጎቶች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ጊዜ በትዕግሥት ለማለፍና ወደ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ ለመሻገር ፈተናዎችን በፅናት መወጣትን ይጠይቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን እየፈተኑና ሕይወታቸውን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመሩ ከሚገኙ ነገሮች መካከል አንዱ ሱስ ነው፡፡ ሲጋራ፣ ጫት፣ መጠጥ፣ ሀሺሽና ሌሎችም ሱሶች የብዙ ወጣቶችን ህልምና ተስፋ አጨንግፈዋል፣ ነጠቀዋልም፡፡ ለዚህም አንዱ ምስክራችን ወጣት ዮናታን ሊዩን ነው፡፡

ዮናታን ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው፡፡ ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ የሆነውና ለ22 ዓመታት በተለያዩ ሱሶች የነበረው ዮናታን፣ ሱስ የባከነ፣ የተዘበራረቀና የከሰረ ሕይወት እንዲመራ አድርጎታል፡፡ ከሞት ደጃፍም አድርሶ የመለሰው ጊዜ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡

‹‹በሱስ ምክንያት የሆንኩት ብዙ ነው፡፡ ከቤተሰብና ከሰው ጋር እንዳልስማማ ሆኛለሁ፡፡ እየሠራሁ የሰው እጅ እንድጠብቅ ሲያስገድደኝ ኖሯል፤›› የሚለው ወጣቱ፣ ሱስ በግላዊና ማኅበራዊ ሕይወቱ ላይ ያኖረው ጠባሳ ይህ ነው ተብሎ በቀላል የሚገለጽ እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡

እንደ ዮናታን፣ ሱስ ካሳደረበት ከፍተኛ የሥነ ልቦናና የጤና ጉዳት ለመውጣት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ከአንድም ሁለት ጊዜ ገብቷል፡፡

‹‹ሱስ የሚድንም፣ የሚያገረሽም በሽታ ነው›› የሚለው ወጣቱ በማዕከሉ የሦስተኛ ጊዜ ቆይታው ሙሉ በሙሉ አገግሞ መውጣት ችሏል፡፡ ከሱስ ከዳነና ካገገመ ስድስት ዓመት የሞላው መሆኑንም ይገልጻል፡፡

እንደ ወጣቱ፣ ሰው መዳን በሚችል በሽታ መሞት የለበትም፡፡ በመሆኑም እሱ ያለፈበት የሕይወት መንገድ ለሌሎች ወጣቶች ተሞክሮ ይሆን ዘንድ በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በግልና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ትምህርት እየሰጠና ልምዱን እያካፈለ ይገኛል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት፣ ‹‹ጉድ ላክ›› የሱስ ማገገሚያ የሥልጠና ማዕከል መክፈቱን፣ በዚህ ማዕከልም 305 ወጣቶች በሚደረግላቸው ድጋፍ ከሱስ መዳንና ማገገም መቻላቸውን ይናገራል፡፡ ‹‹ከሱስ ሞት እንጂ ሕይወት የለም፣ ከዚህ በመትረፌም ራሴን ዕድለኛ እንደሆንኩ አስባለሁ፡፡ በመሆኑም እንደ እኔ ከሱስ በሽታ የዳኑ ብዙ ዕድለኞችን ለማፍራት የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ፤›› ሲልም ያክላል፡፡

በሱስ ምክንያት ከሞት ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጠባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በነፃ ባገኘው ሕክምና አገግሞና ድኖ፣ ዛሬ ላይ ለብዙዎች ምስክር መሆን ችሏል፡፡

ሱስ በሽታ በመሆኑ የሚፈልገው የሥነ ልቦና ሕክምና እንደሆነ በመጠቆም፣ ወላጆች በሱስ የተጠቁ ልጆቻቸው ከሱስ እንዲወጡ ከቁጣ፣ በተግሳፅና ለሕግ አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ በሚያገኙበት መንገድ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡

እንደ ዮናታን፣ ሱስ አስከፊ በሽታ ነው፡፡ ተስፋ እንዲቆረጥና ራስ እንዲጠላ ያደርጋል፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል ራስን ለማጥፋት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ወጣቶች ባለፈ ሕይወት ከመቆጨት ዛሬን ቆም ብለው በማሰብ ካሉበት የሱስ ዓለም ለመውጣት መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡

ዮናታን እንደሚለው፣ አለቀ፣ ደቀቀ የሚባል ሕይወት የለም፡፡ አከተመ የሚባለውም ለሞተ ነገር ብቻ ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ በፍጹም አያስፈልግም፡፡ ለወጣቶች ችግር የመፍትሔ አካል መሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ ወጣቱ በሱስ የተዘፈቀ ነው ብሎ መደምደምም ለውጥ አያመጣም፡፡ ወጣቱ የዚህ አገር ዋነኛው የልማት ኃይል እንዲሆን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና መንግሥት በቅርብ ሆነው ሊያግዙትና ሊደግፉት ይገባል፡፡