

ዜና ቶታል ኢትዮጵያ ወለድና መቀጫን ጨምሮ 507.8 ሚሊዮን ብር ግብር እንዲከፍል ተወሰነበት
ቀን: December 1, 2024
ቶታል ኢትዮጵያ አክሲዮን ማኅበር አሳውቆ ባልከፈለው ፍሬ ግብር ላይ ወለድና ቅጣትን ጨምሮ 507.8 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወሰነበት።
ቶታል ኢትዮጵያ አክሲዮን ማኅበር ገቢዎች ሚኒስቴር እንዲከፍል በጠየቀው የግብር መጠን ላይ ባለመስማማት አቤቱታውን ለፌዴራል የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ያቀረበ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ በኅዳር 2014 ዓ.ም. ቅሬታውን ውድቅ በማድረግ የተጣለበትን ግብር እንዲከፍል ውሳኔ አሳልፎበት ነበር።
ይሁን እንጂ ኩባንያው ቶታል ኢትዮጵያ በይግባኝ ሰሚ ኮሚሽኑ ውሳኔ ባለመስማማት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አቅርቧል። ነገር ግን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑን ውሳኔ በማፅናት፣ ቶታል ኢትዮጵያ የተጣለበትን ግብር እንዲከፍል ወስኖበታል።
ቶታል ኢትዮጵያ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቶበታል። በውሳኔውም የሥር ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የታክስ ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽኑ በየደረጃቸው የሰጡት ውሳኔ የሚነቀፍ አይደለም ሲል አፅንቶታል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም. የግብር ዘመን ፍሬ ግብር፣ ወለድና መቀጫን ጨምሮ 507,860,637.73 ብር እንዲከፍል በተሰጠ ውሳኔ ላይ ሲሆን፣ ይግባኝ ባይ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን፣ ከዚያም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቅሬታውን አቅርቦ የመልስ ሰጪን ውሳኔ አፅንቷል፡፡
ያልተገለጹ የውጭ አገር ግዥ የተገኘን ገቢ በተመለከተ ይግባኝ ባይ ያለ ምንም ምክንያት ክርክሩ ውድቅ ተደርጎብኛል ያለውን በተመለከተ ከውጭ የገባውን ቅባትና ዘይት ዋጋ መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ቶታል ኢትዮጵያ የሚከራከረው ዋጋው መሠላት ያለበት ዕቃዎቹ በተገዙበት ክፍያ በተፈጸመበት ቀን ባለው የባንክ ምንዛሪ ተመን መሆን ሲገባው፣ ዕቃዎቹ በገቡበት ቀን ባለው የጉምሩክ ግምታዊ የውጭ ምንዛሪ ተመን መሠላቱ ያልተገለጸ ገቢ ተብሎ እንዲከፍሉ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ነው፡፡
አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 15 ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች እሴት በሚል የሚጣልባቸው ቀረጥና ታክስን ጨምሮ በጉምሩክ ሕግ መሠረት የዕቃዎች ዋጋ ሲሆን፣ ተጨማሪ እሴት ታክስና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚከፈለውን የገቢ ግብር ቅድሚያ ክፍያ እንደማይጨምር ይደነግጋል፡፡
በዚህ መሠረት ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች የታክስ መጠን ዋጋ ተደርጎ የሚወሰደው ጉምሩክ የሚወስነው ዋጋ እንደሆነ፣ ይህንን መሠረት በማድረግ የተሰጠው ውሳኔ በአግባቡ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ በጉምሩክ አዋጅ አንቀጽ 101 መሠረት ወደ አገር የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ዕቃዎች ዲክላረሲዮን የቀረጥና የታክስ ማስከፈያ ዋጋ የሚወሰነው በተመዘገበው ቀን ብሔራዊ ባንክ የምንዛሪ ሥሌት ልክ የሚደነገግ እንደሆነ፣ ቶታል ኢትዮጵያ በምንዛሪ መሠረት ሳይሆን ዕቃው በተገዛበት ጊዜ ነው የሚለውን ጉዳይ በሕጉ መሠረት ውድቅ ተደርጎበታል፡፡
በ2015 ዓ.ም. ያልተገለጸ ገቢን በተመለከተ ሒሳቡ የተሠራው ትክክለኛ በሳፕ የተመዘገበ መረጃ መሠረት የተያዘ መረጃ ለማቅረብ ጊዜ የሚወስድ ስለሆነ ማስረጃ ለማቅረብ ጊዜ የተጠየቀ ቢሆንም፣ በቂ ጊዜ እንዳልተሰጠውና የመሰማት መብቱ ሳይከበር በተዛባ አሠራር ተጨማሪ ግዥ እንደፈጸመ፣ በድብቅ ሽያጭ እንዳከናወነ ተደርጎ ግብር እንደተወሰነበት የገለጸው ቶታል ኢትዮጵያ፣ ይህንን ፍሐዊ እንዳልሆነና በመረጃው መሠረት በቀረቡ ቅሬታ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቢደረግም ያቀረበው ማስረጃ ተቀባይነት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡
በዋጋ ማስተካከያ የተገኘ ተጨማሪ ገቢንና በድርድር የሚወሰን ዋጋን በተመለከተ ለነዳጅ፣ ቅባትና ዘይት አከፋዮች የሚሰጥ ቅናሽ በሥር ፍርድ ቤቶች ከፖሊሲው አኳያ ከቅናሽና በድርድር የተሰጡ ከተባሉ ምርቶች አንፃር ታይተው ውሳኔ ያገኙ እንጂ የታለፉ ስላልሆኑ፣ ቶታል ኢትዮጵያ ታልፎብኛል በማለት ያቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
በዚህ መሠረት ቶታል ኢትዮጵያ አክሲዮን ማኅበር አሳውቆ ባልከፈለው ፍሬ ግብር ላይ ወለድና ቅጣትን ጨምሮ እንዲከፍል፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስኖበታል፡፡