ተሟገት የሕግ የበላይነት የመጨረሻው ምሽጋችን ይሁን

ቀን: December 1, 2024

በገነት ዓለሙ

የሕግ የበላይነት ማለት ዛሬ ጭምር አልገባን እያለ የሚያስጨንቀንን ያህል አዲስና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲስኩር ውስጥ ለረዥም ጊዜ ለይስሙላም ይሁን ለስም ጌጥ ያህል ሲነሳ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ የአገራችን የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት በተሰጠበት ወቅት፣ በ1924 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱን ለሕዝብ ያስተዋውቁት በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ባደረጉ ንግግር፣ ‹‹ንጉሡ ባለሙሉ ሥልጣን ሆኖ በአገሩ ምንም የተለየ ልማድ ወይም ደንብ ሳይኖርበት፣ ዕብሪቱ ብቻ በየቀኑ የመራውን ሐሳብ እንደፈቀደውና እንደ ባህሪው ድንገተኛ መለዋወጥ እየለዋወጠ ያደርጋል፣ ያለ ፍርድ ይቀጣል፣ ይገድላል፣ ይሰቅላል፡፡›

‹‹ንጉሡ ባለሙሉ ሥልጣን ሆኖ በትክክል ተለይቶ የተጻፈ ሕግ ሳይኖረው ከትውልድ እየተሸጋገረ በቆየው ልማድ ይሠራል፣ ቅጣትም ምሕረትም ለማድረግ፣ ለመሾምና ለመሻርም በአደባባይ በጉባዔ እያስፈረደ፣ በክብር እየሸለመ፣ በገሃድ እያሳወጀ ነው፡፡ ድንገትም በደል ነገር ቢሠራ ማገጃ አልተደረገለትም›› ያሉት መግለጫ ሁሉ ስለሕግ የበላይነት ‹‹አስፈላጊነት›› የሚናገር ነበር፡፡

አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር የባላገሮች አድማ ቀውስ ውስጥ የፊታውራሪ መሸሻ የርስት የጉልት አስተዳደርና ነገረ ፈጅ ቀኛዝማች አካሉ አለቃቸውን፣ ሿሚያቸውን የሚከሱትና የሚያወግዙት ከሌሎች መካከል ‹‹በዳኝነት ወንበር ቢያስቀምጡም በሕግ ፋንታ ፈቃድዎን ሕግ አድርገው ልፍረድ አሉ…›› ብለው ነው፡፡

የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በተሻሻለው የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በተተካ ጊዜ፣ ለምሳሌ የዚህ ሕገ መንግሥት አንደኛ ዓመትና 16ኛው ዓመት የሚያዝያ 27 የድል በዓል ሲከበር የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት የተናገሩትን እንመልከት፡፡ ‹‹… የአገርዎን የነፃነት ፋና ለሕዝብዎ ይዘው ከመጡ በኋላ እግዚአብሔር ለሠራልዎ ከፍ ያለ ሥራ ይህ ብቻ አይበቃም በማለት ሕግ የበላይ ገዥ እንዲሆን ሕገ መንግሥትዎን አሻሽለው እውነተኛውን የዴሞክራት ሕገ መንግሥት ለሕዝብዎ ሰጡ፡፡

በዚህ ከፍ ባለ አስተያየት የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ የሰውን ልጅ የተፈጥሮ መብት ስላገኘ ፍፁም ነፃነት ያለው ሕዝብ ሆነ›› እና በሕግ አምላክ ስንል የምንማጠነው ሕግ ከበላዩ ሌላ ጌታ የሌለበት፣ አለሁላችሁ የሚለን፣ ሁሉንም፣ መንግሥትንም ሕግ አውጪውን፣ ሕግ አስፈጻሚውን፣ ሕግ ተርጓሚውን (የዳኝነት አካሉን) ራሱን የበላይ ሆኖ የሚገዛ ሕግ ማለታችን ነው፡፡

ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የሕጉ የበላይነት ከአወጣጡ፣ ከአመነጫጨቱና ከአፀናነሱ ጀምሮ አፈጻጸሙ፣ አተረጓጎሙ ድረስ፣ ድንገትም ሆነ ሆን ተብሎ አመመኝ ቢል፣ መፍዘዝ መደንዘዝ ቢታይበት ለሕጉ ጥበቃ የሚያደርግለት እውነተኛ ጥበቃና መተማመኛ የሚሰጠው ዴሞክራሲ ማደላደልና ተቋም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሕግ የበላይ ገዥ እንዲሆን…››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር ነፃነት ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ የተፈጥሮ መብት…›› ጭምር እንዲጎናፀፍ (የጠቅላይ ሚኒስትር መኮንን እንዳልካቸው የ1949 ዓ.ም. ቃል ነው) ተቋማት ገለልተኛ፣ ለየትኛውም ቡድን ወይም ወገን የሚያዳሉ፣ የማያጋድሉ፣ የማይወግኑ፣ አጋ የማይለዩ ሆነው መታነፅ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን በተለይም የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግል ለዘመናት ያጎደለውም፣  የጎደለውም ይህ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ማደላደልና ማቋቋም ማለት፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወይም የትኛውም አካል ተፅዕኖ፣ ጥገኝነት ወይም ባለቤትነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታና ጥበቃ ያስፈልጋል ሲባል ሲቪል ሰርቪሱ፣ መከላከያው፣ ፖሊሱ፣ ደኅንነቱ፣ ምርጫ አስፈጻሚው ተቋም ከየትኛውም ወገን፣ ፓርቲ፣ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ኃይል ነፃ ሆኖ መደራጀት፣ ነፃ ሆኖ በራሱ የሚያዝ ሆኖ መሥራት አለበት ማለት ነው፡፡ የዚህ ትርጉምና ተፈጻሚነት ‹‹ፓርቲ›››ን ብቻ ዘመነ ፓርቲን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ተቋማትን፣ የመንግሥት አውታራትን፣ ዓምደ መንግሥቶችን ታማኝ አገልጋይና መጠቀሚያ የማድረግ ጉዳይ የመንግሥት ሥልጣንን የዘረፋ ጥቅማችንና የግል የብቻ ጉዳያችን ባሉ ፓርቲያዊም በሆኑ፣ ፓርቲያዊም ባልሆኑ ቡድኖች፣ በግለሰቦችም ዙሪያ ሊደራጅ ይችላል፡፡

በሕግ ረገድ ነፃና ገለልተኛ ማለት ለአገርም፣ ለሕጉም፣ ለራሱም አዲስ ብርቅና ድንቅ ነገር አይደለም፡፡ ‹‹ዳኞች የዳኝነት ሥራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ፣ ከሕግ በቀር በሌላ ሥልጣን አይመሩም›› ብሎ ነገር ሕገ መንግታዊ ድንጋጌ መሆን ዛሬ ወይም ትናንትና ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ድረስ መላ ያልተበጀለት፣ ፓርቲና ፖለቲካን አለማደባለቅ፣ አለማቀላቀል ማለት ገና ጨርሶ አልገባህ ያለው ሲቪል ሰርቪሱ ወይም የመንግሥት አገልግሎቱ፣ በእርግጠኛና በእቅጭ ስሙ የሕዝብ እሽክርና ነው በሕግ ራሱን ችሎ አስተያየትና ውሳኔ ለመስጠት፣ እንዲሁም ዕርምጃ ለመውሰድ ሰፊ ሥልጣን የተሰጠው ተብሎ ከተቋቋመ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ጊዜ ያለውን ያህል ዕድሜ አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም››፣ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ››፣ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ››፣ ወዘተ እየተባለ መዓት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ሀብትና ንብረት ተከስክሷል፡፡

የኢትዮጵያን ምርጫ አስፈጻሚ አካል በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከነበረው ከአገር ግዛት ሚኒስቴር ማዕቀፍ ውጪ ለብቻው ነፃና ገለልተኛ አድርጎ አዲስ ያቋቋመው የኢፌዴሪ መንግሥት ሥራ ትርጉም ያጣው የለውጥ ሥራ፣ የተቋማት ግንባታ ማለት የግንጥል ጌጥ ለውጥ ጉዳይ ባለመሆኑ ነው፡፡ መላውን የኢትዮጵያን የአገዛዝ ሥርዓት፣ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ አፍርሶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አፍርሶ የመሥራቱም ሥራ ለተፅዕኖ የማይበገር መከታ/መከላከያ ማበጀትን የመሰለ ግንባታ ይሻል፡፡

ነፃና ገለልተኛ ተቋም ማለት ከአስፈጻሚው የመንግሥት የሥልጣን አካል ውጪ የሆኑ ፍርድ ቤቶችን፣ ምርጫ ቦርድንና የመሳሰሉ ተቋማትን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ነፃነትና ገለልተኛነት ራሱ አስፈጻሚው አካል ግቢና ክልል ውስጥ የተቋቋሙ ተቋማትም አላቸው፡፡ ትልቁና ግዙፉ ምሳሌ ሲቪል ሰርቪሱ ነው፡፡ ለምሳሌ ሌላው እዚያው አስፈጻሚው ውስጥ፣ ለዚያውም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ‹‹ነፃና ገለልተኛ›› ሆኖ በሕግ የተቋቋመው የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን ነው፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ብቻ ሳይሆን፣ የዘርፉ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ የኤኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዚያው አዋጅ መሠረት የኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት የሚኖረውን ጠቀሜታ ለማረጋገጥ አጠቃላይ የዘርፉ ፖሊሲ የማዘጋጀት ተግባርና ኃላፊነት አለው ማለትን የመሰለ ድንጋጌ አለ፡፡ በዚህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ነው የኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን እኔ እስከማውቀው ድረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃና ገልተኛ ተብሎ የተቋቋመው፡፡

በዚህ ሕግ መሠረት ነፃና ገለልተኛ ማለት በአሠራር ተለይቶ የተቋቋመ፣ አዋጅ ተለይቶ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ከማንኛውም ወገን ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚፈጽምና ውሳኔ የሚሰጥ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ በዚያው በተልዕኮው ውስጥ ‹‹ቆይ ጠይቄ ልምጣ›› የሚለው፣ ብሎ የማያማክረው፣ እንዳይቆጣኝ ብሎ የሚፈራው፣ ‹‹የትብብር ደብዳቤ የሚጽፍለት፣ እየጻፈ ላስፈራራ ወይም ዋ! የሚለው ሰው/ባለሥልጣን የለም፣ ቢኖርም ዋጋ የለውም ማለት ነው፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጠቅላይ ሚኒስትርነት (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 74) አይቀንስም፡፡ ወይም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በአጠቃላይ በኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ያለውን ሥልጣንና ተግባር አያውቀውም፡፡ እዚህ የገለጽኩት ምሳሌ ውስጥ የምናየውን ዓይነት በሕግ ተለይቶና ተቆርጦ የተወሰነ ግንኙነት እንዴት እንኖረዋለን? እንዴትስ አድርገን መኗኗሪያ እናደርገዋለን? ሕግ ማውጣትና ተቋም ማደራጀት ብቻ ሳይሆን፣ የዚህ ሶፍትዌርም እንዲኖረንና እንዲጣባን በሠራ አካላችን ውስጥ እንዲሠራጭ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ውጪ ሲሆን በሕግ ከተቋቋመው፣ ሕግ አቋቁሜያለሁ/ይቋቋማል ከሚለው አሠራርና መንገድ ውጪ ወለም ዘለም ሲባል ‹‹የሚቆጣ›› ሰውነት፣ የሚታመም አካል ያስፈልጋል፡፡ መቆጣትም፣ መታመምም ሕግም ዓላማም አለው፡፡ ሰውነታችን ሲያኮርፍ፣ ሲቆጣ፣ ሲከፋውና ሲያገምጥ ሐኪም የሚያውቀው ሕግ ስላለው ነው፡፡ ዓላማውም ችግር ተፈጥሯልና መላ ፈልጉ፣ መድኅን አምጡ ነው፡፡ ቁጣውንና ሕመሙ ምን ማጀቡ፣ ማስተጋባቱ፣ መድኅን ብቻ ሳይሆን የችግሩን ምንጭ ፍለጋ መቆርቆሩ፣ ይህንንም ማስተጋባቱ ግን በዕውቀትና በእውነት ላይ መመሥረት አለበት፡፡ የሕግ የበላይነትን የምናግዘው፣ ይልቁንም ለሕጉ ጥበቃ የምናደርግለት ራሳችንም ሕግ ስናከብርና ለሕግ ስንገዛ ነው፡፡

ይህንን የምለውንና የማወራለትን የሕግ የበላይነት፣ ከበላዩ ሌላ ጌታ የሌለበትን የሕግ አገዛዝ ጭብጥ ለማስረዳት በምሳሌነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለዚያም የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ በአጠቃላይ ያጋጠመውን ተሞክሮ እንመልከት፡፡ የዚህ የማነሳው ጉዳይ የጀርባ ታሪክ የፕሪቶሪያው ስምምነት ያስቆመው ጦርነት ነው፡፡ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከእነ ስሙ/ስያሜው እንደሚያስረዳው፣ በኢፌዴሪ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ግጭትን በማቆም አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት ይባላል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ፣ ማለትም በዚህ ምክንያትና ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን ታኅሳስ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በተሰጠ ውሳኔ የፓርቲውን መሰረዝ ወይም መፍረስ በውጤትነት ያስከተለ ውሳኔ ሰጠ፡፡

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ደግሞ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕወሓት ህልውናዬ ይመለስ ብሎ ጠየቀ፡፡ የቦርዱ የግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ውሳኔ የሕወሓትን ጥያቄ ውድቅ አደረገ፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በውሳኔው አዋጅ ቁጥር 1162/2011 (የምርጫና የፓርቲ ምዝገባ ሕግን) መሠረት አድርጎ፣ ለጥያቄው መልስ የሚሰጥ ድንጋጌ አለ? የለም? የሚል ጭብጥ አዋቅሮ፣ በዚህ ሕግ ውስጥ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላገኘሁም፣ የለምም ብሎ ወሰነ፡፡ ሕውሓት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መንቀሳቀስ የሚችለው በአዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት እንደገና የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብና የምርጫ ቦርድም ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑን፣ ከመወሰን ጋር ጥያቄ አቅራቢው ውሳኔው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በውሳኔው ላይ ይግባኝ የማለት/የማቅረብ መብት ያለው መሆኑን ጭምር አሳወቀ፡፡

ጉዳዩ ከሞላ ጎደል ከአንድ ዓመት በኋላ ሲንቀሳቀስ ያየነው ግንቦት 2016 ዓ.ም. መጨረሻ ውስጥ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ ፀድቆ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ (ከግንቦት 23 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ) ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1332/2016 ሆኖ ፀደቀ፡፡

አጭር ዝርዝሩና የነገሩ አመጣጥ ቅደም ተከተል በመጠኑ በቀረበው በዚህ ጉዳይ መነሻነት የሚነሳው፣ የግድ የምናነሳው ለሕግ የመገዛት፣ ከሕግ በታች የመሆን ነገር ሕግ የሚያድገው፣ የሚጎለብተውና የሚበለፅገው እንዲህ ነው ወይ? በሌላ ቀጥተኛ፣ ግልጽና ምናልባትም ‹‹ደፋር›› አባባል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን አስተዳደራዊ ዳኝነት ጠይቆ የቀረበውና ‹‹ለጥያቄው መልስ የሚሰጥ ወይም መልስ የሚሰጡ ድንጋጌዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚተዳደሩበት በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ውስጥ አለ ወይ…? (ይህ የተወሰደው ሕወሓት ‹‹…የሕግ ሰውነት ማጣት ላይ የተወሰዱትን ዕርምጃዎች የሚያሳይ አጭር መግለጫ›› ከሚለው ከራሱ ከቦርዱ መግለጫ ነው) የሚለው ጥያቄ የሚመለሰው፣ ውሳኔ የሚያገኘው ሕግ በማውጣት ነው ወይ? የሕጎች ተፈጥሯዊና ባህርያዊ ዕድገት የሚረጋገጠው እንዲህ ያለ ‹‹ችግር›› በመጣ ቁጥር ሕጉን በመጣፍ፣ በመደረት ነው? ወይስ የዳኝነት አካልና የዳኝነት ሥልጣን አካላቱ ሕጉ ምን ይላል? ብለው የእነሱን ዳኝነት የሚጠይቀውን ጭብጥ አዋቅረው ራሳቸው ሲመልሱት ነው? መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ አስቸጋሪና ቀውጢ የርብርብ ጊዜን ከተረጋጋ ወይም በአንፃራዊነት ከተረጋጋ መደበኛ የኑሮ ሁኔታ ለይቶ ማየትን፣ በዚህም መሠረት ጥያቄንና ቅያሜን መግራትን የግድ የሚያደርግና ልብ አድርጉልኝ የሚል ጉዳይ ስላለ እንጂ፣ እዚህም ላይ ሕግ አወጣጥ ሥርዓታችን የተከተለው መንገድና ‹‹አማራጭ›› የሕግ ገዥነትን የሚያግዝ አይደለም፡፡ ይህ ከዚህ በላይና እጅግ ሰፊ የሕግ ‹‹ብይን›› ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የዚህ ጉዳይ ችግር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላም ነገር አለ፡፡ የማሻሻያው አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1332/2016 ሆኖ ከፀደቀ በኋላ (የዚህ መረጃ ምንጭ በተለይም የፀደቀው ሕግ አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መባሉ ዋቢ የግንቦት 2016 ፓርላማ ዜና መጽሔት ነው) የፍትሕ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚኒስትሩ ፊርማ የጻፈውን ደብዳቤ ይዘት ወሬ ሰማን፡፡ ደብዳቤው ‹‹ጉዳዩ››ን በልዩ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባን ይመለከታል ብሎ ይነሳና ‹‹…ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕውሓት) ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባር ውስጥ በመሳተፉ ምክንያት፣ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት የተሰረዘ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ሆኖም ፓርቲ ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባሩን በማቆም ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር (ማሻሻያ) አዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል በቦርዱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡›› ይላል፡፡

በግልባጭም የሰላም ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ እንዲሁም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያውቁት ያደርጋል፡፡

በአዋጁ ‹‹የፖለቲከ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል›› እንግሊዝኛው ‹‹Through a Special Procedure›› ይላል የሚለውን፣ በሕግ የደነገገውን፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ለምን በደብዳቤ ትብብር ጠየቀበት? ለምን የደብዳቤ አደራ መጻፍ አስፈለገ? ግፋ ቢል ‹‹የአዋጁን በጆሮ›› የሚባል ነገር ያህል ትርጉም የለሽ አይደለም፡፡ ወይም በዚህ ላይ መንሰፍሰፍ ከቁንጫ ሌጦ ማውጣት ዓይነት ከንቱ ልፋት አይባልም፡፡ የዚህ ምክንያት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው፣ በተጠናወተንና ተፈጥሯችን ሆኖ በቆየው ገና ያልተላቀቅነው፣ ያላራገፍነው ያልሻርነው ሕመም መሠረት እነዚህና እንዲህ ያሉ ነገሮች ማስፈራሪያዎች፣ ማስጠንቀቂያዎች፣ ወዘተ ናቸው/ነበሩና፡፡  በተለይ ‹‹ትብብር ስለመጠየቅ››፣ ‹‹አደራ ጥንቃቄ አድርጉ›› ማለት፣ ወይም ይህንን ጉዳይ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ የሚከታተለው ነው ብሎ ነገር የማያሻማ፣ የማያጠራጥር መልዕክት ሲያስተላልፉ የቆዩ የሥራ ቋንቋችን አካል ሆነው የኖሩ ‹ዲኤንኤ›ያችን የሚያውቃቸው ናቸው፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የቦርዱን ትብብር ለመጠየቅ ደብዳቤ የጻፈበት በቀላሉ ከቁጥር የማይወጣ፣ ዝም ብሎ በመጀመሪያ ዕይታ ውድቅ የማይደረግበት አንድ ምክንያት የፖለቲካ ቡድኑ በአዲሱ የማሻሻያ ሕግ መሠረት በልዩ ሁኔታ ሊመዘገብ የሚችለው የተሰረዘበትን በአመፅ ተግባር ውስጥ መሳተፉን፣ ማቆሙንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ የሚለው የሕጉ ድንጋጌ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን በአዋጁ አንቀጽ 68 ንዑስ አንቀጽ 10 እንደተደነገገው ‹‹በሰላማዊና ሕጋዊ አግባብ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚመጣውን ማረጋገጫ መነሻ በማድረግ›› የሚያመለክተው የፖለቲካ ቡድን ራሱ እንጂ፣ የሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ‹‹አደራ›› ባይነት ላይ የተመሠረተ አሠራር የተቋማትን ነፃነትና ገለልተኛነት በስስትና በቀናዒነት ከመጠበቅ አዲስ ባህል ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ የዚህ ምክንያት ሕግ ገዥ ወደ ሆነበት፣ ከፖለቲካ ወገንተኛነት ይልቅ ለእውነት፣ ለሚዛናዊነትና ለነባራዊነት ታማኝ የሆኑ፣ በዚህ ምግባርና ባህሪ አማካይነትም ብልሽቶችንና ጉድለቶችን የማስወገድ ትግል የሚያደርጉ ነፃና ገለልተኛ አውታራት ወደ ተገነቡበት ምዕራፍ ሽግግር እናደርጋለን፣ ለውጥ እናመጣለን ስለምንል ነው፡፡

ይህንን ወደ መሰለ ምዕራፍ እንመጣለን፣ ወደ እዚህ ለውጥ እንሻገራለን የምንለው ደግሞ ከሕግና ከደንብ በላይ መሆን፣ በሥውር ተንኮሎች ማጥቃት፣ መሠሪነትና ሥውር ሴራ፣ ወዘተ አጠቃላይ የሥርዓቱ ሥልት ከሆነበት፣ ተዘፍቀንበት ከኖርነው የድሮው ዓለም ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ንገርልኝ፣ አስታውስልኝ፣ አደራ በልልኝ፣ ወዘተ ማለት ዛሬም አብዮት የተካሄደባቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ ገና ከሕግ በላይ ለመሆን በማያመች ጥልቅና ሥር የያዘ ለውጥ ውስጥ አልገባንም፡፡ የሕገ መንግሥቱን መብቶችና ኃላፊነቶች በተግባር ኑሮ ውስጥ የሚዳስሱና ከማንም በጎ ፈቃድ፣ ቁጠኝነትና መሃላ ውጪ የሚኖሩ አላደረግንም፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸው ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙም፣ ለምን ተብለው ሲጠይቁምና ዕርም እንዲባሉ ሲጠየቁም ደንገጥ ብለን፣ የሠራ አካላችንን ‹‹አስቆጥተን›› የጤና ጥበቃችን፣ የበሽታ መከላከያችን አካልና አምሳል ማድረግ አለብን፡፡

እነዚህ ሁሉ ምላሾች፣ ቁጣችን፣ ድንጋጤያችን ግን ራሳቸው ሕጋዊ መሆን አለባቸው፡፡ በሕግ አምላክ መባል ያለባቸው ለሕግ ተገዙ የሚባሉ ናቸው፡፡ የመንግሥት ሕግ የማውጣትም ሆነ ሕግ የማስከበር ሥልጣን በአጠቃላይ እንዳይማገጥበት፣ እንዳይባለግበት፣ በተለይም ደግሞ የፖለቲካ ጠላትም ሆነ ወዳጅ ማጥቂያና መጥቀሚያ እንዳይደረግ መታገል ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ ለሌላ አሳልፈው የማይሰጡት የሕዝብ ሥራ ነው፡፡ እደግመዋለሁ እነዚህ ትግሎች ግን በዕውቀትና በእውነት ላይ መመሥረት፣ ሕጋዊነትንና የሕግ የበላይነትን መኩሪያቸውና መታፈሪያቸው ማድረግ አለባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡