

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግር ደጋግመን እንድናነሳ ግድ የሚሉ ሁኔታዎችን እየተመለከትን ነው፡፡ በትራንስፖርት አገልግሎት የሚስተዋሉ ችግሮች አሁንም ሁነኛ መፍትሔ ያልተገኘላቸው ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ያሻሽላሉ የተባሉ አንዳንድ ዕርምጃዎች ጭራሽ ችግሩን የሚያባብሱ በመሆናቸው መፍትሔውን ልንነጋገርበት ይገባል፡፡ መነጋገር ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ያለ የሚለው ድምፃችን ጆሮ እንዲያገኝም እንፈልጋለን፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ብሎም ለማዘመን የሚደረጉ ጥረቶች አሉ ቢባልም መሬት ላይ የወረደ ነገር አለ ለማለት ያስቸገራል፡፡ ጭራሽ አንዳንድ መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ዕርምጃዎች ችግሩን እያባባሱት ስለመሆኑ በተለይ ከሰሞኑ የምናያቸው እውነታዎች ይህንኑ ያረጋግጡልናል፡፡
የከረሙ ችግሮችን ትተን ከሰሞኑ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር እያባባሱ ያሉና ብዙዎችን ብዥታ ውስጥ የከተቱ በተለያዩ የጉዞ መስመሮች ላይ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በአስገዳጅነት በአውቶቡስና ቅጥቅጥ በመባል በሚታወቁ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲጠቀሙ መደረጋቸው ነው፡፡
በዚሁ አስገዳጅ ሆኖ በመጣው አሠራር ምክንያት በአንዳንድ መስመሮች ላይ ታክሲዎች እንዳይጭኑ እየተደረጉ ነው፡፡ ይህም ተገልጋዮች በታክሲ እንዳይጠቀሙ ክልከላ እየተደረገባቸው መሆኑ ወትሮም በችግር ውስጥ የነበረውን አገልግሎት የባሰ መልክ እንዲያጣ አድርጎታል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተወሰዱ ናቸው የሚባሉት አዳዲስ ዕርምጃዎች በአግባቡ ጥናት ተደርጎባቸው የተተገበሩ መሆናቸውን እንድንጠራጠር እያደረጉንም ነው፡፡
የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት በአውቶብሶችና በመለስተኛ አውቶቡሶች ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት በዋናነት ተገልጋዩ በቶሎ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚያስችል አልሆነም፡፡
ቀድሞ የታክሲ ስምሪት ይሰጣቸው የነበሩ የጉዞ መስመሮች ታጥፈው ተገልጋዩ በአውቶቡሶች ብቻ እንዲጠቀም አስገዳጅ አሠራር መተግበሩ ካስገኘው ፋይዳ ይልቅ ተገልግዩ ጫና ውስጥ የሚከትና አማራጭ ያሳጣ ነው፡፡ ተገልጋዩ የሥራ ሰዓቱን አክብሮ በሥራ ቦታው እንዳይገኝ እያደረገ ነው፡፡ ሠልፍ ይዞም ቢሆን በታክሲ እንዳይጓጓዝ በአንዳንድ መስመሮች ላይ የታክሲ ስምሪት ተከልክሏሏ መባሉ ተገልጋዩንም የታክሲ ባለንብረቶችንም ግራ ያጋባ ነገር ሆኗል፡፡
ለምሳሌ ከጀሞ አንድ ወደ መገናኛና ሜክሲኮ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ታክሲዎች ከሰሞኑ መጫን አትችሉም ተብለናል በሚል ተሳፋሪዎችን የሚጭኑት ከትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ተሸሽገው ነው፡፡ ከተያዙ ደግሞ ይቀጣሉ፡፡ በሌሎች መስመሮች ላይም እንዲህ ያሉ ችግሮች እየታዩ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የተዘበራረቀ አሠራር የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ከድጡ ወደ ማጡ እያስገባው ነው፡፡ በአውቶቡሶችና በቅጥቅጥ ተሽከርካሪዎች ብቻ ተጠቀሙ የሚለው ቀጭን ትዕዛዝ ተገልጋዩን ወደ ባሰ መጉላላት ከመደረጉ በላይ የሌቦች ሲሳይም እያደረገ ነው፡፡
በአውቶቡሶችና በቅጥቅጥ ተሽከርካሪዎች መጓዝን ማላመድ ተፈልጎ ከሆነ በቂ ተሽከርካሪዎች ማቅረብ ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በአማራጭነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ታክሲዎች በአንዳንድ መስመሮች ላይ እንዳይሠሩ መከልከሉ በምንም ሁኔታ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ሊባል አይችልም፡፡
አሁንም በጀሞ አካባቢ የታዘብኩትን ሰሞኛ ምሳሌ ላድርግና በአውቶቡስና በቅጥቅጥ ተጠቀሙ የሚለው አስገዳጅ ሁኔታ ተገልጋዩን ላልተገባ ወጪ እያደረገ መሆኑን በተጨባጭ እንመልከት፡፡ ተገልጋዮች ታክሲ ባለማግኘታቸውና አውቶቡስ በመጠበቅ የሚያቃጥሉትን ጊዜ ከግምት በማስገባት የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ እየተገደዱ ነው፡፡ ይህንንም ቢሆን ትንሽ አቅም ያላቸው የሚገለገሉበት ነው፡፡ የሰሞኑ ክልከላ ደግሞ የሜትር ታክሲዎች ገበያ እንዲደራ በር ከፍቷል፡፡ ለምሳሌ በሜትር ታክሲዎች አንድ ተጓዥ ከጀሞ አንድ ሜክሲኮ ለመጓዝ የሚጠየቀው 120 ብር ነው፡፡ የተቸገረ ከፍሎ ይሄዳል፡፡ ከጀሞ መገናኛ ለአንድ ሰው 150 ብር ያስከፍላሉ፡፡ በመደበኛ ታክሲዎች ሲጓዝ ከጀሞ እስከ መገናኛ 45 ብር በመክፈል ይጓጓዝ የነበረ ተገልጋይ ለእነዚህ የሜትር ታክሲዎች ተጨማሪ 105 ብር ከፍሎ እንዲጓዝ ከጀሞ ሜክሲኮ ለመጓዝ በሜትር ታክሲዎቹ የሚሳፈሩ አራቱ ተጓዦች በድምር 480 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመደበኛ ታክሲዎች ባይከለከሉ ተጓዡ የሚከፍለው 25 ብር ብቻ እንደነበር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በአማራጭነት እያገለገሉ የነበሩት እነዚህ ሚኒባስ ታክሲዎች እንዲህ ባሉ መስመሮች ላይ እንዳይሠሩ መከልከሉ ተገልጋዮች አማራጭ እንዳይኖራቸው ከማድረጉም በላይ ላልተገባ ወጪ እንደዳረጋቸው ስለመሆኑ ይህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ለከርሞ ምን እንደታሰበ ባይታወቅም ከሰሞኑ እያየነው ያለው አሠራር የአገልግሎት አሰጣጥ ሕገወጥ ተግባራትንም እያስፋፋ የሚሄድ ስለመሆኑም ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ የሜትር ታክሲዎች የራሳቸውን ተመን አውጥተው ለአገልግሎታቸው ከተሰጣቸው ዲጂታል የጉዞ መተግበሪያውም እንዲሠሩ ዕድል የሰጣቸው መሆን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡
የትራንስፖርት እጥረት ባለባቸው ወይም የሚኒባስ ታክሲዎች ክልከላ እየተደረገባቸው ባሉ መስመሮች ላይ አማራጭ ያጣ ተሳፋሪ ደግሞ የግዱን እነዚህን ሜትር ታክሲዎች ሲጠቀም በዲጂታል መተግበሪያው እንዲጠቀም ዕድል አይሰጠውም፡፡ ዋጋው ትክክል አይደለም ለማለትም አይችልም፡፡
የሜትር ታክሲዎቹን አሁናዊ አሠራር ሕገወጥ የሚያደርገው ደግሞ ተጓጓዦችን ሊያስተናግዱ የሚገባቸውና ለአገልግሎቱን እንዲሰጡ ፈቃድ የተሰጣቸው ለአገልግሎቱ የበለፀገውን ዲጂታል የጉዞ ማስተግበሪያ በመጠቀም ቢሆንም ይህ የገቡበት ውል ተጥሶ በራሳቸው የዋጋ ተመን በመሥራታቸው ነው፡፡
ከእያንዱ ሜትር ታክሲ ኩባንያ የተሰጣቸውን መተግበሪያ ያለመጠቀማቸው ፈቃድ ከወሰዱበት አሠራር ውጪ በመሥራት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም እንዲያገኙ በር ከፍቷል፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ደግሞ የሚቆጣጠር ስለሌለ ያሻቸውን ዋጋ ተምነው እንዲሠሩ እያደረጋቸው ነው፡፡ በአንዳንድ መስመሮች ላይ ብዙ ተገልጋዮች ያሉ በመሆኑ መተግበሪያውን ሳይጠቀሙ በራሳቸው መንገድ በተመኑት ዋጋ መሥራታቸውም ቢሆን ሕገወጥ ነው፡፡
የሜትር ታክሲዎች ያለመተግበሪያ እየሰጡ ያሉት አገልግሎት ተገልጋዩን ተገቢ ያልሆነ ወጪ እንዲያወጣ እያደረገው ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በመተግበሪያው ቢጠቀሙ ተገልጋዩ በአነስተኛ ወጪ አገልግሎት ማግኘት ይችል ነበር፡፡ ለምሳሌ ከጀሞ ሜክሲኮ መተግበሪያውን በመጠቀም የሚደረግ ጉዞ ከ300 ብር ያልበለጠ ዋጋ ያለው ነው፡፡ አራቱ ተሳፋሪዎች 480 ብር ይከፍላሉ፡፡ ከጀሞ መገናኛ በዲጂታል መተግበሪያው ቢበዛ 450 ብር ቢፈጅ ነው፡፡ ነገር ግን አራት ሰዎች የሚይዙ ሜትር ታክሲዎች 600 ብር ያስከፍላሉ፣ ስድስት የሚይዙት ደግሞ 900 ብር ያስከፍላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባሉ መስመሮች አገልግሎት ከሰጡ ቢያንስ በመተግበሪያው ቢጠቀሙ የተገልጋዩን ወጪ ሊቀንሱለት ይችሉ ነበር፡፡ ያለመተግበሪያ የሚጠቀሙ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች በተፈጠረላቸው አጋጣሚ ያልተገባ ጥቅም እያገኙበት ነው የሚባልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ በዚህ ዓይነት መንገድ የሚሠሩት ሥራ ታክስ የማይከፈልበት መሆኑ ነው፡፡ የሜትር ታክሲ ኩባንያዎቹም በዚህ መንገድ ከሚሠሩ ተሽከርኮሪዎች ቤሳቤስቲን አያገኙም፡፡
ስለዚህ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግርና እጥረትን ተከትሎ እየወሰዱ ያለው እንዲህ ያሉ ያልተገቡ ተግባራትን እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑን ልብ ሊወው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት በተመለከተ ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ የሌለው መሆንም የችግሩ አካል ነው፡፡ በአንዳንድ መስመሮች በአውቶቡስና ቅጥቅጥ ብቻ እንዲጠቀም የሚገደደው ለምንድነው? በአማራጭነት ታክሲዎች ካሉ በዚያ መጠቀም የሚከለከልበትስ ምክንያት በራሱ ግልጽ ስላልሆነ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመመልከት ማስተካከያዎች ሊደረጉ ይገባል፡፡ በተለይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በተደረገ በተጨባጭ የተለወጠ ነገር ካለም ለኅብረተሰቡ በቂ መረጃ መሰጠት አለበት፡፡
የተሻለ ነገር ለማምጣት ተብለው የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሌላ ችግር ላለማስከተላቸው ማረጋገጥም ይገባል፡፡ ካልሆነ ችግሩ ማባባስ ይሆናልና ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል፡፡