የመንግሥት ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ኢስላማዊው ሚሊሻ ሀያት ታህሪር አል-ሻም
የምስሉ መግለጫ,የመንግሥት ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ኢስላማዊው ሚሊሻ ሀያት ታህሪር አል-ሻም እና በቱርክ መንግሥት የሚደገፉ አማፂያን ናቸው

ከ 9 ሰአት በፊት

የፕሬዝደንት ባሻር አል-አሳድ አገዛዝን የሚቃወሙ አማፂያን ወደ አሌፖ መቃረባቸውን ተከትሎ የሶሪያ መንግሥት ኃይሎች ከተማዋን ጥለው መሸሻቸው ተሰምቷል።

አማፅያኑ የከተማዋን “አብዛኛውን ክፍል” መቆጣጠራቸውን ጦር ሠራዊቱ ያመነ ቢሆንም በሶሪያ ሁለተኛዋ ትልቋ የሆነችውን ከተማ በመልሶ ማጥቃት እንደሚረከብ ቃል ገብቷል።

የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የአሁኑ ጥቃት በተለይ በቅርብ ዓመታት ትልቁ የሚባል ነው።

ባለፈው ረቡዕ በተቀሰቀሰው አመፅ ምክንያት 20 ሰላማዊ ዜጎችን ጨምሮ 300 ሰዎች መገደላቸውን አንድ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ታዛቢ ተቋም አስታውቋል።

ቅዳሜ ዕለት ንግግር ያሰሙት ፕዴዝደንት አሳድ “የሶሪያን እርጋታ ለማስጠበቅ እና የግዛት አንድነቷን ከአሸባሪዎች እና ከደጋፊዎቻቸው ለመከላከል” ቃል ገብተዋል።

“ከአጋሮቻችን እና ከጓደኞቻችን ጋር በመተባበር እንደምናሸንፋቸው እናውቃለን። አሸባሪዎቹ የፈለገ የተጠናከሩ ቢሆኑ እናጠፋቸዋለን” ማለታቸውን ቢሯቸው ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

በአውሮፓውያኑ 2011 የተቀሰቀሰው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ቢያንስ የግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ጦርነቱ የተቀሰቀው የአሳድ መንግሥት ዲሞክራሲ ይስፈን ብለው በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ በወሰደው ጠንካራ እርምጃ ምክንያት ነው።

በ2020 በአማፂያን እና በመንግሥት መካከል ከተገባው የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ግጭቶች ረገብ ቢሉም ታጣቂዎች ኢድሊብ ከተማን ጨምሮ አብዛኛውን የሰሜን-ምዕራብ ክፍል ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።

አሌፓ፤ ሶሪያ

ኢድሊብ ከአሌፖ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው። በአማፂያን ቁጥጥር ሥር የነበረችው አሌፓ በመንግሥት ኃይሎች እጅ የወደቀችው በ2016 ነበር።

አሁን የመንግሥት ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ኢስላማዊው ሚሊሻ ሀያት ታህሪር አል-ሻም እና በቱርክ መንግሥት የሚደገፉ አማፂያን ናቸው።

የዩኬው ድርጅት እንደሚለው አማፂያኑ የአሌፓን አየር ማረፊያ እና ቀረብ ያሉ አነስተኛ ከተማዎችን ተቆጣጥረው፤ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 11፡00 የሚጀምር ሰዓት እላፊ ጥለዋል።

ከአሌፖ በተጨማሪ የሶሪያ አራተኛዋ ትልቋ ከተማ የሆነችው ሀማ በአማፂያኑ እጅ መውደቋን እንዲሁም የመንግሥት ኃይሎች ከአካባቢው ጥለው መውጣታቸውን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል። ነገር ግን የሶሪያ መንግሥት ሚድያ የጦር ሠራዊቱን ውስጥ አዋቂዎችን ዋቢ አድርጎ ይህን ዜና አስተባብሏል።

የሶሪያ መንግሥት ኃይል አማፂያን በአሌፖ እና ኢድሊብ አካባቢዎች ጥቃት መክፈታቸውን አሳውቆ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደሮቹ መገደላቸውን ገልጿል።

በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት አሳድ ሥልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ ድጋፍ ያደረገው የሩሲያ አየር ኃይል ቅዳሜ ዕለት በአሌፖ የአየር ድብደባ ማድረጉ ተሰምቷል።

መቀመጫው ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ታዛቢ ድርጅት እንደሚለው ቀዳሜ ዕለት የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች በኢድሊብ ጥቃት አድርሰዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ቃል አቀባይ ሶሪያ “በሩሲያ እና ኢራን ላይ ጥገኛ መሆኗ” እንዲሁም በ2015 የረቀቀውን የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ስምምነት አልቀበልም ማለቷ “አሁን ለተፈጠረው ሁኔታ” ምክንያት ነው ብለዋል።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለቀቁ ምስሎች እንደሚያሳዩት ከአሌፓ የሚያስወጡ መንገዶች ከተማዋን ለቀው በሚወጡ ነዋሪዎች ተጨናንቀዋል፤ ከተማዋም ጭስ በጭስ ሆናለች።