አርተር አሼ

1 ታህሳስ 2024

ኤድስ ከሞት በላይ በሚፈራበት ዘመን፣ ስሙ ሲጠራ በርካቶች በፍርሃት የሚሸበሩበትን ሁኔታ ለማስወገድ ነበር ከ36 ዓመታት በፊት የዓለም የኤድስ ቀን መታሰብ የጀመረው።

በመላው ዓለም የተነዛው ፍርሃት የሚጠራበትን እና ስለህመሙ ግንዛቤ ለመፍጠርም በሚል የኤድስ ቀን መከበር ጀመረ።

በዚያ ጊዜ አሜሪካዊው የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና አርተር አሽ ተመርምሮ በሽታው እንዳለበት የተረዳበት ወቅት ነበር።

ነገር ግን በወቅቱ ከሸታው ጋር ተያይዞ በነበረው አድልዎ እና መገለል በተለይም ኤድስ ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ጋር በመያያዙ አርተር ለዓመታት ያህል የጤናውን ሁኔታ ምሥጢራዊ አደረገ።

ከዓመታት በኋላ ስለበሽታው ከተናገረ በኋላ በፈር ቀዳጅነት ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያየ ትግል አድርጎ ነበር።

ከ32 ዓመታት በፊት ሚያዝያ ወር ላይ አርተር የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በተገኙበት አዳራሽ ገባ።

ሁሉም ካሜራቸውን ደግነው ነበር።

በዚህች ወቅት በአሜሪካ ዴቪስ ካፕ ለተሰኘው ሽልማት የተመረጠ የመጀመሪያው ጥቁር መሆን ስለነበረው ሚና፣ ወይም በታላላቆቹ ዌምበልደን፣ ዩኤስ ኦፕን እና አውስትራሊያ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ውድድሮች ፈር ቀዳጅ ጥቁር አሸናፊ ስለመሆኑ አልነበረም።

በወንዶች የነጠላ ሻምፒዮና ውድድር የመጀመሪያ ጥቁር ሆኖ በታሪክ የተመዘገበው አርተር በልብ ህመም ምክንያት በርካታ ቀዶ ህክምናዎች አድርጎ ነበር።

እነዚህን ቀዶ ህክምናዎች ተከትሎ በ36 ዓመቱ ነበር ከስፖርቱ ራሱን ያገለለው።

ይህም በዚህ አዳራሽ ከመገኘቱ ከ12 ዓመታት በፊት።

አርተር በግርማ ሞገሱ፣ በርቱዕ አንደበቱ፣ በጉብዝናው እና በስፖርታዊ ጨዋነቱ በውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም ተወዳጅ ነበር።

ኤድስ ገዳይ መሆኑ እና በበርካቶች ዘንድ እንደ ሞት መልዕክተኛ በሚታይበት በዚያ ወቅት ሚዲያው ስለአርተር ጤና ጭምጭምታዎችን ሰምቷል።

የአርተር የልጅነት ባልንጀራ እና የዩኤስኤ ቱደይ ጋዜጠኛ ዳግ ስሚዝ ስለሰማው ጭምጭምታ ፊት ለፊት አፋጠጠው።

አርተር በማግስቱ ከአውሮፓውያኑ 1988 ጀምሮ እሱ እና የቅርብ ወዳጆቹ ብቻ የሚያውቁትን ምሥጢር በይፋ ተናገረው። በኤድስ ተይዣለሁ አለ።

ህመሙ የያዘው በአውሮፓውያኑ 1983 በቀዶ ህክምና ወቅት በተለገሰው በቫይረሱ በተበከለ ደም እንደሆነ ያምናል።

አሜሪካ በልገሳ የሚሰጥ ደምን መመርመር የጀመረችው አርተር ከተያዘ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 1985 ነው።

አርተር የተናገረው አስደንጋጭ ዜና አገሪቱን ሁሉ ከፍተኛ መሸበር ውስጥ የከተተ ነበር።

ከህመሙ በተጨማሪ ሌላ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ የግል መረጃን እና የሰዎችን መረጃ የማጋለጥ የፕሬስ ሥነ ምግባርን የተከተለ ነው የሚለው ነበር።

አርተር በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንድገባ መደረጌ በጣም የሚያበሳጭ ነው። የግል መረጃዬን ለመጠበቅ እንድዋሽ ልደረግ ነበር” ሲልም ተቸ።

“የእኔን የጤና ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አስገዳጅ የሆነ የህክምናም ሆነ አካላዊ ሁኔታ አልነበረም” ሲል ተናግሯል።

አርተር በኋላ ላይ ‘ደይስ ኦፍ ግሬስ’ በሚል ርዕስ ባሳተመው ማስታወሻ ‘ግላዊ መብቱ መከበር ነበረበት በሚል ከ700 በላይ ደብዳቤዎች ለዩኤስኤ ቱደይ መድረሱን አስፍሯል። በተጨማሪ 95 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጋዜጣው የአርተርን ህመም ያጋለጠበትን አቋም አጥብቀው ተቃውመዋል።

ሆኖም አንዳንድ የኤድስ ተሟጋቾች አርተር ህመሙን መደበቁን ተችተውታል። በተለይም ህመሙ ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች (ኤልጂቢቲ) ብቻ ጋር በመያያዙ እንደሱ ያሉ ስመ ጥር አትሌቶች በሽታው ማንኛውንም ሰው እንደሚያጠቃ ግንዛቤን መፍጠር ይችላል ብለው ያምኑ ነበር።

እንደእሱ ያሉ ሴት ያገቡ ባለትዳሮች በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ እመርታ ማሳየት ይችሉ ነበር ሲሉ ተችተውታል።

አርተር ስለበሽታው ይፋ ከማድረጉ ከአምስት ወራት በፊት የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለ ያሳወቀው ታዋቂው አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማጂክ ጆንሰንን ከተነሳበት ጥያቄዎች መከላከል ይችል እንደነበር ያሰፈረ ደብዳቤ ለጋዜጣው ተልኳል።

በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ በኤችአይቪ መያዙን በተረዳበት ወቅት ለምን በይፋ እንዳልተናገረ በተጠየቀበት ወቅት ስጋቱን ገልጾ ነበር።

“መልሱ ቀላል ነው። በዚያ ጊዜ በኤችአይቪ መያዜን ይፋ ማድረግ በጣም ከባድ ነበር። ከባለቤቴ ጋር የቤተሰባችንን ግላዊ መብት በዘላቂነት ይጎዳዋል በሚል በምሥጢር ለመያዝ ወሰንን” ብሏል።

በዚሁ መግለጫ ስለበሽታው ለአምስት ዓመት ልጁ ካማራ እንባ ስለተናነቀው መናገር አልቻለም። ባለቤቱ ጂኒ እሱን ወክላ አነበበች።

አርተር አሼ

የግል መረጃን የመጠበቅ መብት እስከምን ድረስ?

የዩኤስ ኤ ቱደይ የስፖርት አርታኢ ጄን ፖሊሲንሲኪ የአርተርን በኤችአይቪ መያዝ ይፋ ያደረገው ጽሁፍ እንዲታተም ያሳለፈው ውሳኔ የሚፀፀትበት ጉዳይ አይደለም።

“አርተር በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተከሰቱ ታላላቅ አትሌቶች አንዱ ነው። በዓለም ዘንድ ስመ ጥር ነው። በወቅቱ ለሞት በሚዳርግ ህመም መያዙ ታወቀ። ለ25 ዓመታት ጋዜጣን እንደ መምራቴ ይህ ዜና ነው” ሲል ለቢቢሲ በቅርቡ ተናግሯል።

የፀፀት ስሜት ተሰምቶት እንደሆነ ሲጠየቅም “በጭራሽ አይሰማኝም። የፀፀት ስሜት ተሰማኝ ማለት በወቅቱ ውሳኔዬ የተሳሳተ ነበር ማለት ነው። ስህተት አልነበረም” ብሏል።

አርተር ኤድስ እንዳለበት ለዓለም ከገለጸ ኮስት ወራት በኋላ በለንደን ተገኝቶ ነበር።

በዚያን ወቅት ‘ፋይቲንግ ባክ’ ለተሰኘው የቢቢሲ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቃለ መጠይቅ በተደረገለት ወቅት “የሆነ ወቅት ላይ ለሕዝብ ይፋ እንደማደርግ አውቅ ነበር። ቫይረሱ በተገኘብኝ ወቅት ጤናዬ ጥሩ ስለነበር በዚህ ሳልረበሽ ሥራዬን ለመቀጠል ወሰንኩ። በዚያን ጊዜ አደባባይ መውጣት ማለት የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አልነበረም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

አርተር የግላዊ መረጃን የመጠበቅ መብትን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጋዜጠኞችን ሞግቷል።

በአንድ ወቅትም “የግል መረጃን የመጠበቅ መብት መለኪያዎች ምንድን ናቸው? ማን ይወስናቸዋል። በማንስ ሥልጣን ይጣሳሉ። ለእኔም ሆነ ለየትኛውም አሜሪካዊ የማይጣስ እና የተከበረ ምንድን ነው?” ሲልም ጥያቄዎችን ለጋዜጠኞች አቅርቦ ነበር።

ስመ ጥሩው ጥቁሩ አትሌት ሕይወቱን ሙሉ የተለያዩ ማኅበራዊ ጭቆናዎችን ሲታገል እና ለፍትህ ሲሠራ ቆይቷል።

በአውሮፓውያኑ 1943 በሪችመንድ ቨርጂኒያ የተወለደው አርተር ገና እናቱ በስድስት ዓመቱ ማለፏን ተከትሎ ነበር ስፖርት እና መጻህፍትን መሸሸጊያ ያደረገው።

“ለእኔ ከሁሉም በላይ ለሕይወቴ አዛዥ እና በቁጥጥሬ ስር መሆኗን ማወቄ መሠረታዊ ነገር ነው” ሲል በአንድ ወቅት ከአንድ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሮ ነበር።

አክሎም “በ40ዎቹ እና 50ዎቹ ጥቁር ሆኖ በአሜሪካ ውስጥ ማደግ በሕይወትህ አዛዥ እንዳልሆንክ ያሳይሃል። ዘረኛው የነጮች ሕግ የት ትምህርት ቤት መሄድ እንዳለብህ፣ በየትኛው አውቶብስ መሳፈር እንደምትችል፣ መሄድ የምትችልበት ቦታን ይነግርሃል። ሙሉ ሕይወትህ በክልከላ የተሞላ ነው” ብሎ ነበር።

ታዋቂ በሆነበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ስሙን ተጠቅሞ ሌሎች የሲቪል መብቶችን እንዲታገል ጥሪ ቢደረግለትም እሱ ግን ቴኒስ ላይ ማተኮር በመምረጡ የዘር ጭቆና ተባባሪ የሚል ክሶች እንዲነሱበት ምክንያት ሆኗል።

ሆኖም በራሱ መንገድ መሄድን የመረጠው አርተር ወደ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የአትሌትነት እውቅና በመጠቀም ለተለያዩ ጉዳዮች ዘመቻን አካሂዷል።

በስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት የደቡብ አፍሪካውን ጨቋኝ እና አናሳ የነጮች አገዛዝ የሆነውን አፓርታይድን አውግዟል። ከዓለም የመገናኛ ብዙኃን ዓይን ርቆም በደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ ለሚገኝ የጥቁሮች የቴኒስ ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

አርተር ስፖርት ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት የሚል እምነት ነበረው። በአውሮፓውያኑ 1969 የሃብታም ልጆች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዘር እና መደብ ያቀፈ የታዳጊዎች የቴኒስ ሊግ ለመመሥረት ችሏል።

አርተር ወደ በኋላ በአሜሪካ ውስጥ ለፍትህ እና ለእኩልነት በሚደረገው ትግል ከፍተኛ ተሰሚነት ካላቸው አንዱ መሆን ችሏል።

ሲትዝን አሽ በተሰኘው ጥናታዊ ፊልም ላይ ሜክሲኮ በነበረው ኦሊምፒክስ አሸናፊ ከነበሩት ውስጥ አንዱ እና የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር የጥቁሮችን ጭቆና በመቃወም ተቃውሞውን እጁን ጨብጦ ወደላይ ያነሳው ዶክተር ሃሪ ኤድዋርድስ ስለ አርተር “ኃያል ታጋይ” ሲል መስክሯል።

በርካታ ጊዜ የልብ ህመም ያጋጠመው አርተር የአሜሪካ የልብ ማኅበር ቦርድን ተቀላቅሎ ነበር። በኤድስ መያዙን ከገለጸ በኋላ ዘመቻውን መቀላቀሉ የሚያስደንቅ አልነበረም። ስለ በሽታው የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን ውድቅ ለማድረግ በርካታ ጊዜ ሚዲያዎች ላይ ይቀርብ ነበር። በሽታውን ለመታገል የአርተር አሽ ፋውንዴሽንን አቋቁሞ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1992 የዓለም ኤድስ ቀን በተከበረበት ዕለት በዓለም የጤና ድርጅት ላይ ተገኝቶ ንግግር አድርጓል።

አርተር በሽታውን ይፋ ካደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ ከኤድስ ጋር በተያያዘ የሳምባ ምች በሽታ ሕይወቱ አለፈ። እሱ ካለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ፀረ ኤችአይቪ ህክምና ተገኘ።

ከመሞቱ በፊት ሬድግሬቭ ከተባለ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቆይታ “መሞትን አልፈራም። ሁልጊዜም ተስፋ አለ። ሕይወታችሁን መኖር ያለባችሁ ተስፋ እንዳለ ወይም እንደሚኖር በማመን ነው። ተስፋ ከራስ ወዳድነት መመንጨት የለበትም። ምናልባት በእኔ ዘመን ለኤድስ መድኃኒት ላይኖር ይችላል። ስለዚህ ለእኔ ተስፋዬ ለመጪው ትውልድ በእርግጠኝነት ይኖራል የሚል ነው” ብሎ ነበር።