
1 ታህሳስ 2024
ታሙና ሙሴሪድዜ የማደጎ ልጅ መሆኗን ከጠረጠረች ወዲህ እጅግ ስትጓጓለት የነበረውን የስልክ ጥሪ ለማድረግ ጓጉታለች።
ወላጅ እናቷ ሳትሆን አትቀርም የተባለችውን ሴት ለማግኘት ብዙ ሞክራለች። እናቷን ስታገኛት ሁሉም ነገር የሰመረ ሊሆን እንደማችይችል ልቦናዋ ነግሯታል።
ነገር ግን በስልኩ በዚያኛው ጫፍ ያለችው ሴት ቁጡ እና ምንም የማይመስላት ትሆናለች ብላ አልጠበቀችም።
“መጮህ ጀመረች። ‘እኔ ልጅ ወልጄ አላውቅም’ ማለት ጀመረች። ከእኔ ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት እንዲኖራት የፈለገች አትመስልም” ስትል በወቅቱ የነበረውን ታሙና ታስታውሳለች።
በሁኔታው ከመናደድ ይልቅ መገረምን መርጣለች።
“ለሁሉም ነገር ዝግጁ ነበርኩ። ነገር ግን እንዲህ ይሆናል ብዬ በፍፁም አልጠበቅኩም።”
ታሙና አሁን 40 ዓመቷ ነው። ባለፈው ነሐሴ ለእናቷ ስትደውል ወላጅ እናቷ ሳትሆን አትቀርም የተባለችው ሴት አልፈለገቻትም።
እንዴት በማደጎ ልትሰጥ እንደቻለች ማወቅ ትሻለች። ከወላጅ እናቷ ሌላ ማወቅ የፈለገችው አንድ ነገር አለ። የወላጅ አባቷን ስም።

ታሙና ወላጆቿን ማፈላለግ የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር። የሟች እናቷን ቤት ስታፀዳ ነው አንድ ወረቀት ላይ ዓይኗ ያረፈው። ወረቀቱ የልደት የምስክር ወረቀት ነው።
እዚህ ወረቀት ላይ የሰፈረው የልደት ቀኗ እሷ ከምታከብረው የተለየ ነው። ይሄኔ ነው ምናልባት በማድጎ ይሆናል ያደግኩት ብላ መጠርጠር የጀመረችው።
ወላጆቿን ለማፈላለግ በሚል ፌስቡክ ላይ ‘ቬድዜብ’ አሊያም ፍለጋ የተባለ ቡድን መሠረተች።
ምንም እንኳ ዓላማዋ ወላጆቿን ማፈላለግ ቢሆንም በፌስቡክ አማካይነት ሕፃናትን በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውር ቡድን ገጠማት። ይህ ቡድን በርካታ ሺህ ቤተሰቦችን ነክቷል።
ወላጆች ልጆቻቸው እንደሞቱ ይነገራቸዋል። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ልጆቹ ተሸጥው እንጂ ሞተው አልነበረም። ይህ ለአስርታት የዘለቀ ሒደት ነው።
ታሙና ጋዜጠኛ ናት። በሥራዋ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላጆች እና ልጆቻቸውን አገናኝታለች። ነገር ግን የራሷን ሕይወት ምሥጢር መፍታት አልቻለችም። በልጅነቷ ተሰርቄ ይሆን? የሚለው ሐሳብ ያንገበግባታል።
ወላጆቿን ፍለጋ በተለመከተ ትልቅ ዜና ያገኘችው ባለፈው ክረምት ነው። በፌስቡክ አማካኝነት የውስጥ መልዕክት ደረሳት። መልዕክቱን የላኩት በጆርጂያ ገጠራማ ክፍል የሚኖሩ ግለሰብ ናቸው። መልዕክቱ እንደሚለው ከሆነ አንዲት ሴት እርግዝናዋን ደብቃ ቆይታ በአውሮፓውያኑ 1984 መስከረም ወር ወደ ዋና ከተማዋ ቲቢሊሲ አቅንታ ወልዳለች።
ጊዜው ከታሙና የልደት ቀን ጋር ተመሳሳይነት አለው። መቼ እንደተወለደች ለፌስቡክ ተከታዮቿ አጋርታለች።
መልዕክቱ የታሙና ወላጅ እናት ልትሆን ትችላለች የተባለች ሴት ስምን ይጠቅሳል። ታሙና የሴትየዋን ስም ፍለጋ ወደ ኢንተርኔት አመራች። ግን ምንም ሊቀናት አልቻለም። ቀጥላ ለፌስቡክ ወዳጆቿ አጋራች።
አንዲት ሴት መልዕክት ላከች። እርግዝናዋን ደብቃ ወደ ዋና ከተማ ሄዳ የወለደችው ሴት አክስቴ ናት ይላል ፅሑፉ። ታሙና የፃፈችውን ከፌስቡክ እንድታጠፋው ጠይቃ፤ ነገር ግን የዘረ-መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን አሳወቀች።
- በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ ያለው ኤችአይቪ በግብፅ እና በሳዑዲ አረቢያ እየተስፋፋ ነው30 ህዳር 2024
- ቤልጂየም በወሲብ ንግድ ለሚተዳደሩ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ እና ጡረታ እንዲያገኙ ፈቀደች30 ህዳር 2024
- የላጤዎች ጉባኤ በቦሌ16 ህዳር 2024
ከዲኤንኤ ምርመራ በኋላ ውጤቱን እየተጠባበቀች ሳለ ነው ታሙና ወላጅ እናቷ ወደተባለችው ሴት ስልክ የመታችው።
የዲኤንኤው ውጤት ከአንድ ሳምንት በኋላ መጣ። በውጤቱ መሠረት ታሙና እና በፌስቡክ ያገኘቻት ሴት ዝምድና አላቸው። ይህን ይዛ ነው ታሙና ወላጅ እናቷን በመከራ በማሳመን የአባቷን ስም እንድትነግራት ያደረገቻት። ወላጅ አባቷ የተባለው ሰው ስሙ ጉረጌን ኾራቫ ነው።
“የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት በጣም አስደናጋጭ ነበሩ። እየሆነ ያለውን ነገር ማመን አዳገተኝ። ወላጆቼን ማግኘቴን ማመን አቃተኝ” ስትል ታስታውሳለች።
ታሙና የወላጅ አባቷን ስም ካወቀች በኋላ አፈላልጋ ፌስቡክ ላይ አገኘችው። አባት የታሙናን ታሪክ በማኅበራዊ ሚድያ ሲከታተል ኖሯል። የተጠፋፉ ወላጆች እና ልጆችን በማገናኘት በጆርጂያ እውቅና አትርፋለች።
አባት የታሙና “ሦስት ዓመት ሙሉ የፌስቡክ ጓደኛዋ ነበር”፤ ነገር ግን ልጁ መሆኗን ፍፁም አያውቅም ነበር።
“ወላጅ እናቴ እርጉዝ መሆኗን እንኳ አያውቅም ነበር” ትላለች ታሙና “በጣም ገርሞት” እንደነበር በማውሳት።
አባት እና ልጅ በፌስቡክ ከተዋወቁ በኋላ እሱ በሚኖርበት ምዕርብ ጆርጂያ ዙጊዲ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ። ሥፍራው እሷ ከምትኖርበት ቲቢሊሲ 260 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው።

አሁን ስታስታውሰው ቢገርማትም አባቷን ባገኘች ወቅት ፍፁም ተረጋግታ ነበር። ምናልባት ድንጋጤው በዝቶ ይሆናል ያረጋጋት።
የ72 ዓመቱ ወላጅ አባቷ እና ታሙና ተቃቀፉ። ቆም ብለው ለደቂቃዎች ያህል ተያዩ። ድጋሚ ተቃቀፉ። ፈገግታቸው ሊገደብ አልቻለም።
“ግራ አጋቢ ነው። ልክ ገና እንዳየኝ ነው ልጁ መሆኔን ያወቀው። ነገሮች ሁሉ ተደበላልቀውብኝ ነበር” በማለት የነበረውን ሁኔታ ታወሳለች።
ብዙ ጥያቄዎች አሏት። ከየት እንደምትጀምር አታውቅም። “በቃ ቁጭ ብለን እየተያየን የሆነ አንድ የሚያደርገን ነገር ማፈላለግ ጀመርን” ትላለች ታሙና ።
ወሬ ማውራት ሲጀምሩ ብዙ የሚጋሯቸው ነገሮች እንዳሉ መገለጥ ጀመረ። ጉርገን በአንድ ወቅት እጅግ የታወቀ ዳንሰኛ ነበር። የልጅ ልጆቹ ማለትም የታሙና ልጆችም ዳንሰኛ ናቸው። ይህን ሲሰማ ደስ አለው።
“ልጆቼ ዳንስ ይወዳሉ። ባሌም እንዲሁ ዳንስ ይወዳል” ትላለች በፈገግታ።

ጉርገን ቤተሰቡን በሙሉ ጠርቶ ታሙናን እንዲተዋወቁ አደረገ። በአንድ ጊዜ ዘመደ ብዙ ሆነች። በአባት የሚገናኙ እህት እና ወንድሞች፣ የአክትስ እና የአጎት ልጆች፣ አክስቶች እና አጎቶች።
ሁሉም ዘመዶቿ ይመጡና አባትሽን ትመስያለሽ ይሏታል። እሷም “ከልጆቹ ሁሉ እሱን የምመስለው እኔ ነኝ” ትላለች በልበ-ሙሉነት።
አመሻሹን ሲጫወቱ ቆዩ። የጆርጂያ ባሕላዊ ምግብ ቀረበ። ተበላ፤ ተጠጣ። ዘመድ አዝማድ ሲዘፍን ጉርገን አኮርዲዮን በመጫወት ሲያጅባቸው አመሸ።
ታሙና አባቷን አገኘችው። ነገር ግን አሁንም የሚቆረቁራት ነገር አለ። ልክ በሺዎች እንደሚቆጠሩ ጆርጂያውያን እኔም ከእናቴ እቅፍ ተነጥቄ ተሽጬ ይሆን? የሚል።
ያሳደጓት ወላጆችን እንዳትጠይቃቸው በሕይወት የሉም።
በስተመጨረሻ ባለፈው ጥቅምት ወላጅ እናቷን ይህን ጥያቄ መጠየቅ ቻለች። አንድ የፖላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ በታሙና ሕይወት ዙሪያ ዘጋቢ ፊልም እየሠራ ስለነበር ከእናቷ ጋር እንዲገናኙ አደረገ። ወላጅ እናቷ ይህን ጥያቄ ካሜራ ፊት ሳይሆን በድብቅ ልትመልስላት ቃል ገባች።
ታሙና በርካታ ተሽጠው ወላጆቻቸውን ሳያውቁ ያደጉ ልጆችን ከቤተሰቦቻች ብታጣምርም የእሷ ታሪክ ግን ይለያል። እሷ ተሽጣ ሳይሆን ወላጅ እናቷ በድብቅ ወልዳ ለማደጓ ከሰጠቻት በኋላ ጉዳዩን ለ40 ዓመታት ለማንም ትንፍሽ ሳትል ደብቃው ኖሯል።

ወላጅ እናቷ እና አባቷ ግንኙነት አልነበራቸውም። አንድ ምሽት ተገናኝተው ነው ታሙና የተፀነሰችው። ወላጅ እናቷ በፍርሃት እርግዝናውን ደብቃ ይዛ ቆይታ በ1984 ለቀዶ ህክምና ቲቢሊሲ መሄዷን ተናግራ ነው ወደ ዋና ከተማዋ መጥታ የወለደቻት። ታሙና በማደጎ የምታድግበት ቤተሰብ ካገኘችላት በኋላ ነው ጥላት ወደ ገጠራማው ክፍል የተመለሰችው።
“ከማደጎው በፊት ከእሷ ጋር ለ10 ቀናት ማሳለፌን ሰማሁ። ስለእሱ ማሰብ አልፈልግም” ትላለች ታሙና።
ታሙና እንደምትለው ወላጅ እናቷ ተሽጣ እንደሆነ እንድትዋሽ ጠይቃታለች። “ተሽጫለሁ ካላልሽ የእኔ እና ያንቺ ነገር እዚህ ላይ ያበቃል አለችኝ። እኔ ግን በፍፁም አይሆንም አልኳት።”
ታሙና ይህን ያደረገችው በልጅነታቸው ተሽጠው ካደጉ በኋላ ወላጆቻቸውን ለሚያገኙ ልጆች ፍትሐዊ አይደለም በሚል ነው። “እኔ ከዋሸሁ ከዚህ በኋላ ማንም ሰው አያምነኝም።”
ታሙና እንደማትስማማ ስትነግራት ወላጅ እናቷ ቤቱን ጥላ እንድትወጣ ነገረቻት። ከዚያን ጊዜ በኋላ ወላጅ እናቷን አግኝታት አታውቅም።