የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ
የምስሉ መግለጫ,የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ከ 8 ሰአት በፊት

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቅዳሜ ምሽት በመንግሥታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ስለወቅታዊ ጉዳዮች ቃለ-ምልልስ ሰጥተዋል።

ፕሬዝደንቱ ሶማሊያ፣ ግብፅ እና ሀገራቸው ኤርትራ ስለገቡት ስምምነት፣ በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ እንዲሁም ስለአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቱ በቀጣናው ስላለው ሁኔታ ከሰጡት አስተያት በተጨማሪ በሀገራቸው በውሀ መሠረተ ልማት፣ ኢነርጂ፣ የመኖሪያ መንደር ግንባታን በተለመከተ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

በኢትዮጵያ ስላለው ጉዳይ እና ስለህወሓት

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንደ ሁልጊዜው “አሁን በኢትዮጵያ ያለው ግጭት እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት አለመስማማት የመነጨው በአውሮፓውያኑ 1994 ተግባራዊ በሆነው ሕገ-መንግሥት ነው” ብለዋል።

“[ሕገ-መንግሥቱ] ለውጥረት መንስዔ ከመሆኑም ባሻገር ሀገር ግንባታን የሚያስፋፋ አይደለም። ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር ሰላም ካልፈጠረች ቀጣናው ለሚያስፈልገው መረጋጋት፣ ትብብር እና መቻቻል አዎንታዊ አስተዋፅዖ አይኖራትም” ሲሉ በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ተናግረዋል።

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንዲሁም ለ20 ዓመታት ያክል በባድመ ምክንያት በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰፍኖ የቆየው ውጥረት “የዚህ ፖሊሲ ውጤት ነው” ብለዋል። አክለው በሁለቱ ሀገራት መካከል ለነበረው የድንበር ግጭት የውጭ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

ፕሬዝደንቱ በቀጣናው እንዲሁም በመላው የአፍሪካ ቀንድ ግጭት እያስፋፉ ነው ያሏቸው የውጭ ኃይሎችን ማንነት በስም አልጠቀሱም።

ኢሳያስ በኢትዮጵያ አዲስ አስተዳደር [የዐቢይ አሕመድ መንግሥት] ከመጣ በኋላ “የተቀሰቀሰውም ጦርነት በዚህ አግባብ ሊታይ ይገባል” ብለዋል።

“ህወሓት በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ አልቀበልም ብሎ ጦርነት ውስጥ በመግባት ኤርትራ ውስጥ ከ70 በላይ ዒላማዎችን በረዥም ርቀት ሮኬት መትቷል” ሲሉ የከሰሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የኤርትራ መንግሥት ህወሓት ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ያቀረበው ጥሪ ሰሚ አለማግኘቱን ተናግረዋል።

ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላም በአማራ ክልል ግጭት መከሰቱን ያነሱት ፕሬዝደንቱ መንግሥታቸው ላይ የሚነሳውን ወቀሳ እንደማይቀበሉት እና ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ከመግባት ሁሌም እንደሚቆጠቡ አሳውቀዋል።

በጠቅላላው የመንግሥታቸው ዓላማ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን መሆኑን ተናግረው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ እንዲገቡ ክፍተት ላለመፈጠር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ሠራዊታቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፎ መሳተፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ጦርነቱን ካስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ግን በሁለቱ መንግሥታት መካከል የነበረው ግንኙነት መቀዛቀዝ ተስተውሎበታል።

የኤርትራው፣ የሶማሊያ እና የግብፅ ፕሬዝደንቶች እጅ ለእጅ ተጨባብጠው

የኤርትራ፣ የግብፅ እና ሶማሊያ ስምምነት

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የማግኘት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ጋር አለመግባባት ውስጥ እንዳለች ይታወቃል።

በተለይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ መተላለፊያ እንዲሁም ሚና እንዲኖራት ያላትን ፍላጎት ይፋ ካደረገች በኋላ በቀጥታም ባይሆን ኤርትራ ደስተኛ አለመሆኗን ስታሳይ ነበር። በዚህም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኤርትራ ከሦስት ጊዜ በላይ ጉብኝት አድርገዋል።

በተጨማሪም ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ አሥመራ ላይ የተፈረመው የሶስትዮሽ ስምምነት ከኢትዮጵያ አንጻር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ይህንን አስተባብለዋል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ “የውጭ ኃይሎች እና አቀንቃኞች በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሠራጩት የተዛባ መረጃ እና ዘመቻ በቀጣናው ግጭት ያባብሳል” ሲሉ ኮንነዋል።

“ይህ [በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠራጨው] የመነጨው ከልብ ለኢትየጵያ ከማሰብ አይደለም” ያሉት ፕሬዝደንቱ በሦስቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት “ዋና ዓላማው በቀጣናው መረጋጋትን ማስፈን” እንደሆነ ተናግረዋል።

የኤርትራ ዋና ፍላጎት “በመላው የአፍሪካ ቀንድ፣ በአባይ ተፋሰስ እና በቀይ ባሕር አጎራባች ሀገራት መረጋጋት እና ትብብር እንዲኖር ነው” ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

“ኤርትራ በፍፁም ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የማየት ፍላጎት የላትም” ያሉት ኢሳያስ፣ በቀጣናው ሀገራት መካከል የሚደረሱ ስምምነቶች ያለመተማመንን እንዲሚቀርፉ እና ፍሬያማ እንደሆኑ አስምረዋል።

በሱዳን ጉዳይ

ፕሬዝደንት ኢሳያስ በጎረቤት ሀገር ሱዳን ስላለው የእርስ በርስ ጦርነትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እሳቸው እንደሚሉት በ2019 በሱዳን የተቀሰቀው አመፅ ሃይማኖታዊ አጀንዳዎች እና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ተባብረው ያመጡት ነው ይላሉ።

የሱዳን ግጭት የሚፈታው በሱዳናውያን ነው የሚሉት ፕሬዝደንቱ ነገር ግን ኤርትራ እና ሱዳን ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አንፃር እንዲሁም “ደኅነንቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ ቀጣና ለማረጋገጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል።

የሱዳን ግጭት እንዲፈታ ሀገራቸው ኤርትራ በአውሮፓውያኑ 2022 አጋማሽ “አከራካሪ ያልሆነ እና በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ” የሰላም ማዕቀፍ ማቅረቧን አወስተዋል።

“ጦርነቱ ሊቀስቀስ ባይገባውም የቀጠለው በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ነው” የሚሉት ኢሳያስ የሱዳን የእርስ በርስ ግጭት በአስቸኳይ እንዲቋጭ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የጦር ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል አል ቡርሃን የሚመሩት የአገሪቱ ሠራዊት እና በጄኔራል ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የበላይነት ለመያዝ እየተፈላሙ ነው።

ባለፈው ሳምንት ጄኔራል አል ቡርሃን በኤርትራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

ፕሬዝደንት ኢሳያስ ተመራጩን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ‘ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌን’ የሚለው ሐሳብ “አሜሪካ በዓለም ዙሪያ ያላት ተፅዕኖ እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል” ብለዋል።

አሜሪካ በምጣኔ ሀብት፣ በወታደራዊ መስኮች እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በሌሎች መስኮች ተፅዕኖዋ ባለፉት ሦስት አስርታት እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ ቻይና በምጣኔ ሀብቱ እና በቴክኖሎጂው መስክ የፈጠረችው ተፅዕኖ እና ሩሲያን ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አሜሪካን እየተገዳደረ ነው ብለዋል።

አክለውም አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር የሚቀርፀው ፖሊሲ ለውጥ ያመጣ ይሆን ወይ? የሚለው አጠራጣሪ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የኤርትራው ፕሬዝደንት፤ ትራምፕ የሚቀርጿቸው ፖሊሲዎች ለውጥ ያመጡ ይሆን የሚለውን ለመተንበይ ጊዜው ገና ነው ብለዋል ሲሉ ተናግረዋል።

አክለው “የቤት ሥራችንን እየሠራን ገንቢ የሆነ ግንኙነት ለመመሥረት ዝግጁ መሆን አለብን” ብለዋል።

ኤርትራ ሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ተቀዛቅዞ የቆየ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያትም ፕሬዝደንት ኢሳያስ በሀገራቸው እንዲሁም በቀጣናው ለሚፈጠረው ቀውስ አሜሪካንን ተጠያቂ በማድግ በተደጋጋሚ ሲከሱ ቆይተዋል።