ፋትሂ
የምስሉ መግለጫ,ፋትሂ

ከ 9 ሰአት በፊት

ፋትሂ ሁሴን ወደ ፈረንሳዩዋ ማዮቴ ደሴት ለመጓዝ ገንዘብ ከከፈለቻቸው ሰው አዘዋዋሪዎች ጋር ሳትግባባ ትቀራለች።

ስደተኞችን የሚያዘዋውሩት ግለሰቦች ፋትሂን በአሰቃቂ ሁኔታ እንድትሞት አድርገዋል።

ፋትሂ በሶማሊያ ሞቃዲሹ የውበት ሳሎን ባለቤት ነበረች። ሞቷን የተረዱት ቤተሰቦቿ ሀዘን ተቀምጠዋል።

የፋትሂ ታላቅ የእንጀራ እህት ሰሚራ “ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደነገሩን የሞተችው በረሃብ ነው” ብላለች።

ፋትሂ በሕንድ ውቅያኖስ እየተጓዙ ከነበሩ ሁለት ትንንሽ ጀልባዎች በአንደኛው ላይ ከ14 ቀናት በፊት መሞቷን ቤተሰቦቿ ሰምተዋል።

ሰው አዘዋዋሪዎቹ ጥለዋት ከሄዱ በኋላ ነው ሕይወቷ ያለፈው።

“ጥሬ ዓሣ እየበሉና የውቅያኖስ ውሃ እየጠጡ ነበር። እሷም ይሄንን እምቢ አለች። ከጉዞው የተረፉ ሰዎች እንደነገሩን ከመሞቷ በፊት እያቃዣት ነበር። ከዚያም ውቅያኖስ ውስጥ አስክሬኗን ወረወሩት” ብላለች ሰሚራ።

በማዳጋስካር የባሕር ዳርቻ የሚኖሩ ዓሣ አስጋሪዎች የተቀሩትን ስደተኞች ሕይወት አድነዋል። አብረዋት ይጓዙ የነበሩ ሶማልያዊ ስደተኞች ለቤተሰቦቿ ስለአሟሟቷ ነግረዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም እንዳለው ሁለት ጀልባዎች ተገልብጠው 24 ስደተኞች ሲሞቱ 48ቱ ተርፈዋል። ጀልባውን የተሳፈሩት 70 ሰዎች ነበሩ።

በየዓመቱ ወደ ፈረንሳይ ደሴት የሚጓዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ይሞታሉ።

ፋትሂ በኅዳር መባቻ ከሞቃዲሹ ወደ ኬንያዋ ሞምባሳ አቀናች። ከዚያም ወደ ደሴቷ ጀልባ ተሳፈረች።

ጉዞው በሕንድ ውቅያኖስ 1,100 ኪሎሜትር ማቋረጥ ይጠይቃል።

ሰሚራ እንደምትለው ፋትሂ ስኬታማ የውበት ሳሎን ባለቤት ነበረች። ያቅሺድ በተባለው መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ትኖርም ነበር።

ፋትሂ ለምን ወደ ስደት እንደሄደች ሰሚራ ግራ ተጋብታለች።

ከታናሽ እህቷ ውጪ ለቤተሰቦቿ ስለ ጉዞው አልተናገረችም ነበር። ከውበት ሳሎኗ ባገኘችው ገንዘብ ሰው አዘዋዋሪዎቹን ከፍላቸው ነበር።

ስደተኞችን የሚያዘዋውሩት ግለሰቦች

“ውቅያኖስ በጣም ትጠላ ነበር። እንዴት እዛ ውሳኔ ላይ እንደደረሰች እንጃ። ባቅፋት ምንኛ ደስ ይለኝ ነበር” ብላለች ሰሚራ።

ከሞምባሳ ጀልባው ሲነሳ ብዙ ስደተኞች ጭኖ እንደነበር ከአደጋው የተረፉ ተናግረዋል። ሆኖም ግን ጀልባው ችግር ገጥሞታል በሚል ሰው አዘዋዋሪዎቹ እንደሚመለሱ ተናገሩ።

ወደ ኬንያ ከመድረሳቸው በፊት ስደተኞቹን በሁለት ትንንሽ ጀልባዎች አዘዋወሩ።

በሦስት ሰዓት ውስጥ ማዮቴ ደሴት እንደሚደርሱም ነገሯቸዋ።

ሆኖም ግን ጉዞው 14 ቀናት ወሰደ። በጉዞው ፋትሂን ጨምሮ ሌሎችም ስደተኞች ሕይወታቸው አልፏል።

ስደተኞቹ ገንዘብ ስለከፈሉ አዘዋዋሪዎቹ ውቅያኖስ መሀል ትተዋቸው መሄድን ከመጀመሪያውም እንዳሰቡበትና ወደ ፈረንሳይ ደሴት የመውሰድ ዕቅድ እንዳልነበራቸው ሰሚራ ትጠረጥራለች።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ሠራተኛ ፍራንትዝ ካሌስቲን እንደሚለው፣ ወደ ደሴቱ ለመድረስ ስደተኞች ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።

በቅርቡ በተመሳሳይ ጉዞ 25 ስደተኞች መሞታቸውን ገልጿል።

“በኮሞሮስና ማዳጋስካር ያልፋሉ። ዘንድሮ በዚህ መንገድ የሚጓዙ ስደተኞች በብዛት ሞተዋል” ይላል።

ወደ ደሴቱ የተጓዙ አምስት ስደተኞችን ቢቢሲ ያነጋገረ ሲሆን፣ ዋነኛ መንገዱ ከሶማሊያ ደሴት እንደሚነሳ ተናግረዋል።

የተወሰኑት ከሞምባሳ በኮሞሮስ ደሴት አድርገው ወደ ማዮቴ ይጓዛሉ። የተወሰነ ገንዘብ ያላቸው ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ በአውሮፕላን ተጉዘው ወደ ማዳጋስካር ይደርሳሉ።

ወደ ፈረንሳይና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት በዚህ ደሴት በኩል መሄድ ነው ዕቅዳቸው።

ከዚህ ቀደም ከስደት ጉዞው የተረፈው ከድር መሐመድ እንደሚለው ከማዳጋስካር ወደ ማዮቴ ለመድረስ ከፍተኛ እንግልት ውስጥ አልፏል።

ከድር ከ11 ወራት በፊት በደሴቱ ደርሷል።

“ማዳጋስካር ስደርስ የጀልባ ባለቤት ቤት ውስጥ ለ14 ቀናት እንድንቆይ ተደረገ። ሶማሌዎችና የማዳጋስካር ዜጎች አብረን ነበርን” ይላል።

70 ስደተኞች በጀልባ እንዲሄዱም ተደርጓል።

ከአል-ሸባብ በደረሰበት ማስፈራሪያ ምክንያት ነበር የተሰደደው።

“ለደኅንነቴ ስል አገሬን ጥዬ ወጣሁ። ነጋዴ ነበርኩ። በአል-ሸባብ ምክንያት ግን መሥራት አልቻልኩም” ይላል ከድር።

ከሞምባሳ ወደ ማዮቴ ለመጓዝ እስከ 6000 ዶላር እንደሚከፈል የሰደተኞች ቤተሰቦች ይናገራሉ።

በትልቅ ጀልባ ስደተኞች ወደ ፈረንሳይ ደሴት እንደሚወስዱ በቲክቶክ ላይ ማስታወቂያ የሚሠሩ ሰው አዘዋዋሪዎች ቁጥር ተበራክቷል። ጉዞው የሚካሄደው ግን ለአደጋ በሚያጋልጡ አነስተኛ ጀልባዎች ነው።

የፈረንሳይ መንግሥት በቅርቡ ስለደረሰው አደጋ ምንም አስተያየት አልሰጠም።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም ፊቂ እንዳሉት፣ ከአደጋው የተረፉ ስደተኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ ሥራ ተጀምሯል።

የፋትሂ ቤተሰቦች ልጃቸውን ያነጋገረችውን ሰው አዘዋዋሪ ለፖሊስ ጠቁመው ቢያስይዙም በዋስ መለቀቁን ተናግረዋል።

ሰሚራ እንደምትለው፣ ፋትሂ በመጨረሻዎቹ የሕይወቷ ደቂቃዎች ምን ስሜት ውስጥ እንደነበረች አለማወቅ ያሳዝናታል።

“ስለ ውሳኔዋ ብትነግረኝ ደስ ይለኝ ነበር። ብትሰናበተኝ ደስ ይለኝ ነበር። አሁን እንዴት ሞቷን መቀበል እንደምችል አላውቅም” ትላለች።