
1 ታህሳስ 2024, 08:19 EAT
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው አማካሪያቸው ካሽ ፓቴል የፌዴራል ምራመራ ቢሮን እንዲያስተዳድሩ መረጡ።
በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር የመከላከያ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ኃላፊ የነበሩት ፓቴል የትራምፕ ታማኝ ባለሟል እና ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው።
ፓቴል የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆነው የሚሾሙት የአሁኑ ኃላፊ ክሪስቶፈር ሬይ ሥራ ከለቀቁ አሊያም ከተባረሩ ነው። ትራምፕ ሹመታቸውን በገፁበት ደብዳቤ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ያሉት ነገር የለም።
በሌላ የሹመት ዜና ዶናልድ ትራምፕ የፍሎሪዳዋ ሂልስቦሮው ክፍለ-ግዛት የፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ቻድ ክሮኒስተር የመድኃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ የተባለውን ድርጅት እንዲመሩ መርጠዋል።
ቅዳሜ ዕለት ሹመት ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል ሌላኛው ቻርልስ ኩሽነር ሲሆኑ በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር ተደርገው ተሹመዋል።
ቻርልስ ኩሽነር የትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ባል ጃሬድ ኩሽነር አባት ናቸው። ሰውዬው በፖለቲካ ልምዳቸው ሳይሆን በሪል-ስቴት ሙያ ባካበቱት ልምድ ነው እውቅና ያገኙት።
ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ለዘመድ አዝማድ ሥልጣን ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያው ነው።
የትራምፕ ተሿሚዎች ሥልጣናቸው እንዲፀድቅ የሴኔቱን ድምፅ ማግኘት አለባቸው።
- መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች እና የፈጠሩት ስጋት29 ህዳር 2024
- ወላጆቿን ስታፈላልግ ከርማ አባቷ የፌስቡክ ጓደኛዋ ሆኖ ያገኘችው ጋዜጠኛ1 ታህሳስ 2024
- ኤድስ እንደያዘው ከ32 ዓመታት በፊት ለዓለም የተናገረው አሜሪካዊው የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮን1 ታህሳስ 2024
“ካሽ [ፓቴል] ማለት ሕግ አዋቂ፣ መርማሪ እና ‘ቅድሚያ ለአሜሪካ’ የሚል፤ ዕድሜውን በሙሉ ሙስናን በመታገል፣ ፍትሕን በመመከት እና አሜሪካዊያንን በመጠበቅ የኖረ ሰው ነው” ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚድያቸው ፅፈዋል።
ካሽ ፓቴል ከዚህ ቀደም ኤፍቢአይን ማስተካከል በሚል ባቀረቡት ሐሳብ ቢሮው ኃላፊነቱ “እንዲገደብ” እና “ዋና ዋና ሰዎች እንዲባረሩ” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የወቅቱ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአውሮፓውያኑ 2017 ሲሆን የተሾሙት ሹመታቸው ለ10 ዓመታት የሚዘልቅ ነው።
ነገር ግን ሰውዬው ከትራምፕ ጋር ቁርሾ ውስጥ የገቡት ምስጢራዊ መረጃዎችን ያለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ምክንያት ነው።
ከህንዳዊያን ስደተኛ ወላጆች የተገኘው ካሽ ፓቴል ጠበቃ እና የፌዴራል አቃቤ ሕግ ሆኖ አገልግሏል። በ2017 የሕዝብ እንደሴዎች ምክር ቤት የደኅንነት ኮሚቲ ሳለ ነው በትራምፕ ዓይን ውስጥ የገባው።
በአውሮፓውያኑ 2019 የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆኖ በትራምፕ ሲሾም ከዓመት በኋላ ደግሞ የፔንታገን ፅ/ቤት ኃላፊ [ቺፍ ኦፍ ስታፍ] ሆነ።
‘ገቨርንመንት ጋንግስተርስ’ በተሰኘ ርዕስ ያወጣው የግለ-ሕይወት መፅሕፍ በተጨማሪ ሁለት ትራምፕን የሚያወድሱ የሕፃናት መፃሕፍት አሳትሟል።
መገናኛ ብዙኃን “አሜሪካ እስከዛሬ ካየቻቸው ፈርጣማ ጠላቶች መካከል አንዱ ነው” ሲል ይናገራል። የትራምፕ የሚድያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ የቦርድ አባልም ነው።