
Saturday,30 November 2024 – Addis Admas
Written by Administrator
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ ሚና ያላቸውን ተፋላሚ ወገኖች ለማደራደር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማሰብ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶችና የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል በጋራ ባቀረቡት የሰላም ጥሪ ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንፁሃን ላይ ያነጣጠሩ የግድያ፣ የጥቃት፣ የእገታ፣ የመፈናቀል እና የዘረፋ ተግባራት መፈጸማቸውን አውስተዋል። መግለጫቸውም፤ “የተፈፀሙት ተግባራት በየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ የሚወገዙ ፍፁም ወንጀል ድርጊቶች ሲሆኑ የአንዳንዶቹ ተግባራት አፈፃፀምም በጭካኔና በአረመኔነት የተሞሉ እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡” ብለዋል።
በቅርቡ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደራ ወረዳ፣ ሰላሌ አካባቢ የተፈፀመው አሰቃቂና ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ድርጊት ችግሩ የደረሰበትን ደረጃ በተጨባጭ ማስረጃ እንደሚያሳይ የገለጹት የጉባዔው የበላይ ጠባቂዎች፣ በአጠቃላይ ይህንን እና ከአሁን ቀደም የተፈፀሙ መሰል ድርጊቶችን ሁሉ በጽኑ እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል። በማያያዝም፣ የመንግስት ቀዳሚ አጀንዳ የአገር ሰላምና የዜጎች ደህንነት የመጠበቅ ጉዳይ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
እንደ አገር የምንገኝበት ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ያነሱት የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመስራት አዳጋች እንደሆነባቸውና የአገር አቋራጭና ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሁነው እየሰሩ እንደሚገኙ በተለያየ ጊዜ ከሚወጡ መግለጫዎች ለመረዳት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶች በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ካለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሕዝቦች ከባድ ፈተና መፍጠሩን በማንሳት፣ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ንግግርና ድርድር እንዲመጡ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። በትክክል ቀኑን ይፋ ባያደርጉም፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን በግጭቶች ውስጥ ያሉ ተፋላሚ ወግኖችን ለማቀራረብ፣ ለማደራደርና ለማስታረቅ ቁርጠኛና ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተያያዘ በነገው ዕለት ዕሁድ ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ አገራዊ የሰላም እና የጸሎት መርሃ ግብር በመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እንደሚከናወን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስታውቀዋል። አያይዘውም፣ ከዚህ ቀደም የሐይማኖት አባቶች በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን በማስታወስ፣ አሁንም ይህንኑ ጥሪ እያቀረቡ መሆናቸውን ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ዙሪያ በቤተ ዕምነቶች እና የሃይማኖት አባቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ጉባዔው “እንዴት ይመለከታቸዋል?” የሚል ጥያቄ አዲስ አድማስ ለቀሲስ ታጋይ አቅርቦ ነበር። ቀሲስ ታጋይ በምላሻቸው፣
“የመግለጫው አንድ አካል ነው። በአገሪቱ የትም ክልል ለተገደሉ ወገኖች ውግዘት አድርገናል። ማንም ይሁን ምን ተግባሩ የሚወገዝ ነው፤ ለሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር እንዲመጡ ጥሪ መቅረቡን ገልጸዋል።