ታንክ ላይ የቆመ ታጣቂ - ሶሪያ

ከ 6 ሰአት በፊት

በእርስ በርስ ጦርነት በታመሰችው ሶሪያ አማፂያን ለዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የመንግሥት ወታደሮች ላይ ዘመቻ የከፈቱት ባለፈው ረቡዕ ነው።

ቅዳሜ ዕለት የሶሪያ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ የምትባለውን የአሌፖን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠራቸው ተነግሯል።

አማፂያን የመንግሥት ኃይሎች ባልጠበቁበት ሁኔታ በከፈቱት ጥቃት ምክንያት የሶሪያ ጦር ሠራዊት ከተማዋን ለቆ ሲወጣ፣ የሩሲያ ጦር ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 2016 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሌፖ ላይ የአየር ድብደባ ፈፅሟል።

ጥቃቱን የመራው እስላማዊው ቡድን ሀያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የተባለው ሚሊሻ ሲሆን፣ ለበርካታ ዓመታት ሶሪያ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የቆየ ነው።

ሀያት ታህሪር አል-ሻም ማነው?

ኤችቲኤስ በተባለ ምሕፃረ-ቃሉ የሚታወቀው ይህ ቡድን በአውሮፓውያኑ 2011 ሲቋቋም መጠሪያው ጃብሃት አል-ኑስራ ነበር። ነገር ግን ቡድኑ የአል-ቃኢዳ ክንፍ ሆኖ ነው የተቋቋመው።

የኢስላሚክ ስቴት መሪ የነበረው አቡ ባካር አል-ባግዳዲ ይህ ቡድን ሲቋቋም አስተዋፅዖ እንደነበረው ይነገራል።

ፕሬዝደንት ባሻር አል አሳድን ተቃውመው ጠመንጃ ካነሱ ታጣቂ ቡድኖች መካከል እጅግ ኃያሉ እና አደገኛው እንደሆነ ይነገርለታል።

ነገር ግን ከአብዮታዊነት ይልቅ ወደ ጂሃዳዊ መርሆቹ ያደላል እየተባለ የሚወቀሰው ይህ ቡድን ፍሪ ሲሪያ ከተባለው ዋነኛው የአማፂያን ኃይል ኅብረት ጋር ግጭት ውስጥ ይገባ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2016 የቡድኑ መሪ አቡ ሞሐመድ አል-ጃውላኒ በይፋ ከአል-ቃኢዳ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ተናግረው ጃብሃት አል-ኑስራ መፍረሱን አሳወቁ። አቡ ሞሐመድ በቀድሞው ቡድን ፈንታ አዲስ ድርጅት ማቋቋመችውን ተናገሩ።

አዲሱ ቡድን በተቋቋመ በአንድ ዓመቱ ሌሎች በርካታ አማፂ ቡድኖችን በማጣመር ሃያት ታህሪር አል-ሻም የሚል ስያሜ አገኘ።

ሶሪያን የሚቆጣጠራት ማነው?

ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረው የሶሪያ እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፉት አራት ዓመታት ያበቃ መስሎ ነበር።

የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች በፕሬዝደንት ባሻር አል-አሳድ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ሲሆኑ፣ በሌሎች የሶሪያ አካባቢዎች ላይ ግን አሁንም አማፂያን ተንሰራፍተው ይገኛሉ።

በተለይ በምሥራቁ ክፍል የሚገኙ በአብዛኛው ኩርዶች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ከእርስ በርስ ጦርነቱ መጀመር በኋላ ራሳቸውን ከሩሲያ መንግሥት ቁጥጥር ነፃ አውጥተዋል።

በ2011 በአሳድ መንግሥት ላይ የተነሳው አመፅ መነሻ በሆነው የደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል አልፎ አልፎ አለመረጋጋት ቢኖርም ከቁጥጥር ውጪ ግን ሆኖ አያውቅም።

በሶሪያ በረሀ በኩል ራሱን ኢስላሚክ ስቴት ብሎ የሚጠራው ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ያደርሳል። በተለይ ደግሞ የአደን ወቅት በሚሆን ጊዜ ሶሪያዊያን ትራፍል የተባለውን ውድ ምግብ ለማምጣት ሲሄዱ ጥቃት ይደርስባቸዋል።

በሰሜን ምዕራብ የምትገኘው ኢድሊብ ግዛት በጦርነቱ ጊዜ ብቅ ብቅ ባሉ ጂሃዲስቶች እና አማፂያን ቁጥጥር ሥር ናት።

ኢድሊብን የሚቆጣጠረው አማፂ ቡድን ነው ባለፈው ረቡዕ አሌፖ ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት በማድረስ የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች ሥፍራውን ለቀው እንዲሸሹ ያስገደደው።

መራራ ግጭት

የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች ኢድሊብን ከአማፂያን ቁጥጥር ለማስለቀቅ ለዓመታት መራር የሚባል ጦርነት አካሂደዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 የአሳድ መንግሥት የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው ሩሲያ እና የአማፂያኑ ደጋፊ የሆነችው ቱርክ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረሰ።

አራት ሚሊዮን ገደማ ሶሪያውያን ኢድሊብ ይኖራሉ። አብዛኞቹ የአሳድ ኃይሎች ከአማፂያን ጋር በሚያደርገው ከባድ ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ ከተሞች ሸሽተው የመጡ ናቸው።

አሌፖ እጅግ አስከፊ የሚባል ጦርነት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አንዷ ናት። የሶሪያ አማፂያን ትልቅ የሚባል ኪሳራ የደረሰባቸው አሌፖ በተደረገው ጦርነት ነው።

ፕሬዝደንት ባሽር አል-አሳድ ይህን ጦርነት ያሸነፉት ከሩሲያ አየር ኃይል በተደረገላቸው ድጋፍ እና ከኢራን በሚያገኙት የጦር መሣሪያ ምክንያት ነው። በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎች ከሶሪያ መንግሥት ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል።

ከእነዚህ መካከል አንደኛው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ አንዱ ነው።

በቅርቡ እስራኤል በሊባኖሱ ቡድን ላይ የወሰድችው እርምጃ እንዲሁ ሶሪያ በሚገኙ ኢራናውያን የጦር አዛዦች ላይ የፈፀመችው ጥቃት የኢድሊብ አማፂያን አሌፖ ላይ ያልጠተበቀ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ምክንያት ሆኗል ብለው የሚጠራጠሩ አሉ።

ታንክ ላይ የቆሙ ሶስት የወታደር ልብስ የለበሱ ሰዎችና መሬት ያለ ግለሰብ
የምስሉ መግለጫ,አማፂው ቡድን አሳድን ለመገዳደር ቆርጦ የተነሳ ይመስላል

ሃያት ታህሪር አል-ሻም የተባለው አማፂ ቡድን መቀመጫውን ኢድሊብ አድርጎ አካባቢውን እያስተዳደረ ይገኛል። ነገር ግን ቡድኑ በአካካቢው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፅማል የሚል ወቀሳ ስለሚቀርብበት ተቀባይነት እንዳያገኝ አድርጎታል።

አልፎም ከሌሎች አማፂያን ጋር ከባድ የሚባል ግጭት ውስጥ መግባቱ ይነገራል።

ቡድኑ ከኢድሊብ ባለፈ ዓላማው ምንድነው የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ከአል-ቃኢዳ ጋር ከተለያየበት ጊዜ ጀምሮ በሶሪያ እስላማዊ አገዛዝ ለመመሥረት ሲሞክር ይታያል። ቡድኑ የአሳድ መንግሥትን በመገርሰስ የሶሪያን ጦርነት ለማፋፋም ዕቅድ ያለው አይመስልም ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች የተቀየሩ ይመስላሉ።