
ከ 6 ሰአት በፊት
የ2034 የወንዶች ዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ሳዑዲ አረቢያ ያለተቀናቃኝ አገር ያቀረበችውን ጥያቄ ፊፋ ገምግሞ አጠናቋል።
የፊፋ ግምገማ ሳዑዲ በቀጣይ ወር በይፋ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ መሆኗ እንዲገለጽ በር ይከፍታል።
ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ ሳዑዲ ላይ ጥያቄዎች ቢነሱም አገሪቱ ለአዘጋጅነት ያቀረበችው ጥያቄ ከ5 ነጥብ 4.2 አግኝቷል። የትኛውም ውድድሩን ለማዘጋጀት የጠየቀ አገር ካገኘው ነጥብ ትልቁ ነው።
ፊፋ ሳዑዲ ለሰብአዊ መብት ‘ውስን’ አደጋ እንደምትሆን በመግለጽ አገሪቷን እንደ ጥሩ አዘጋጅ አገር እንደሚወስድ መግለጹ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን አላስደሰተም።
በዓለም ትልቁ የነዳጅ ማዘዋወሪያ ግንባታ በሳዑዲ የሚካሄድ ቢሆንም ሳዑዲ ለአካባቢ ጥበቃ የደቀነችው አደጋ ‘አነስተኛ ነው’ ብሏል ፊፋ። አገሪቱ ዘላቂነት ላለው የአካባቢ ጥበቃ ‘ቁርጠኛ’ መሆኗንም አክሏል።
የአገሪቱ ሙቀት ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ እንደሆነ በመግለጽ ይህም “መርሃ ግብሩ ይካሄድበታል ከተባለው ጊዜ የአየር ሁኔታ ጋር የሚጋጭ ነው” ሲል ፊፋ አስታውቋል።
ኳታር በ2022 እንዳደረገችው ቀዝቀዝ ባለ ወቅት ጨዋታዎችን ማካሄድ እንደሚቻል በመጥቀስም “ሳዑዲ በቅርበት አብራን የምትሠራ ይሆናል። መቼ ይጠናቀቅ በሚለው ላይ የተሻለ ጊዜ ይመረጣል” ብሏል ፊፋ።
በሌላ በኩል የ2030 የዓለም ዋንጫ በሦስት አህጉራት የሚካሄድ ሲሆን ይህም በአካባቢ ጥበቃ ላይ “አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ሲል ፊፋ አስታውቋል።
ውድድሩን የሚያዘጋጁት ስፔን፣ ፖርቹጋል እና ሞሮኮ ናቸው።
ሦስት የመክፈቻ ግጥሚያዎች በኡራጓይ፣ በአርጀንቲና እና በፓራጉዋይ ይካሄዳሉ።
- ሳዑዲ አረቢያ ለዓለም ዋንጫ ከምድር 350 ሜትር ከፍታ ላይ ስታዲየም ልትገነባ ነው14 ነሐሴ 2024
- ወደ ፈረንሳይ ደሴት ትጓዝ የነበረችው ሶማሊያዊት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቷ አለፈ1 ታህሳስ 2024
- የትራምፕ ታማኝ ባለሟል የሆኑት ግለሰብ ኤፍቢአይን እንዲመሩ ተመረጡ1 ታህሳስ 2024
ሳዑዲ ያወጣችው ከፍተኛ ገንዘብ
ሳዑዲ ወደ 5 ቢሊዮን ፓውንድ ገደማ ከ2021 ጀምሮ አውጥታለች።
ልዑል አልጋ ወራሹ የዓለም ዋንጫን የ‘ቪዥን 2030’ ዕቅዳቸው አካል አድርገውታል።
ከእግር ኳስ በተጨማሪ የፎርሙላ 1፣ የጎልፍ እና የቦክስ ውድድሮችን ሳዑዲ ታዘጋጃለች።
ሳዑዲ በስፖርት ላይ ከፍተኛ ገንዘብ የምታፈሰው እና ታላቅ ስም ያላቸው ውድድሮችን የምታስተናግደው በሰብአዊ መብት አያያዝ የጠለሸውን ስሟን ለማጥራት ነው ተብላ ትተቻለች።
የአውሮፓውያኑ 2018 የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ እንዲሁም በግዛቲቱ ያለው የሴቶች ጭቆና፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ የተጣለው ክልከላ፣ የየመን ጦርነት እና የንግግር መብት ገደብ ይጠቀሳሉ።
በ2024 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ቢያንስ 200 ሰዎች በመንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸውን የሚጠቁም ሪፖርት ወጥቷል። የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ሦስት አሥርታት ከታየው ከፍ ያለ ነው።
የነዳጅ ሃብቷ የተትረፈረፈው ሳዑዲ ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘም ትተቻለች።
ሳዑዲ በበኩሏ የስፖርት ኢንቨስትመንቷ ምጣኔ ሀብቷን እንደሚያነቃቃ እና ቱሪስቶችን እንደሚስብ ትናገራለች።
አገሪቱ እየዘመነች እና እየተለወጠች እንደሆነም ይነገራል።
ፊፋ ስለ ሳዑዲ ያወጣውን ባለ 110 ገጽ ሪፖርት በተመለከተ የሳዑዲ የስፖርት ሚኒስትር ልዑል አብዱላዚዝ ቢን ቱርክ አል ፈይሰል “ጨዋታው እንዲያድግ ያለንን ቁርጠኛነት የሚያሳይ ውጤት ነው በፊፋ የተሰጠው። መላው ዓለም የሚዝናናበትን ውድድር ለማዘጋጀት ፍላጎት አለን። የተሰጠን ውጤት ልፋታችንን ያሳያል” ብለዋል።

የሰብአዊ መብት ጥያቄ
ፊፋ እንዳለው አገራትን የሚመዝነው “በአጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዛቸው” ሳይሆን “ከውድድሩ ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ክፍተትን ለመሙላት በሚያደርጉት ጥረት” አማካኝነት ነው።
ፊፋ “በተለይም አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ማሻሻያ ለማድረግ ጥረት እና ጊዜ ያሻል” ሲልም አስታውቋል።
አያይዞም በአገሪቱ እና በባለድርሻ አካላት በኩል የታየው “ሥራ እና ቁርጠኛነት እንዲሁም ባለፉት 10 ዓመታት የታየው ለውጥ በቀጣይ ከቪዥን 2030 ጋር በተያያዘ ለሰብአዊ መብት መሻሻል ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ” ጠቅሷል።
“ከውድድሩ ጋር በተያያዘ የሠራተኞች እና የሕጻናትን መብት በማክበር እንዲሁም እኩልነትን በማስፈን በተያያዥም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር እና በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ መንግሥት ቁርጠኛ ነው” ሲልም አክሏል።
ብዝሃነትን ከማስጠበቅ እና ከእኩልነት አንጻር “በተለይም ከእስላማዊ ሕግ ጋር የሚጻረሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በተመለከተ ክፍተቶች ታይተዋል። ውድድሩ እኩልነት የሚታይበት፣ መድልዎ የማይኖረው እንደሚሆን፣ ሕጎች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ እና ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር አብሮ ለመሄድ መንግሥት ቁርጠኛነት እንዳለው ታይቷል” ብሏል ፊፋ።
የዓለም ዋንጫ ውድድር በአገሪቱ ለሚደረጉ አሁናዊ እና የወደፊት ለውጦች “አነሳሽ” እንደሆነም ፊፋ አስታውቋል።
“ከውድድሩ ባሻገር ለሳዑዲ ዜጎች እና ለቀጠናውም የሚተርፍ አወንታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ይላል የፊፋ ሪፖርት።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በሳዑዲ የሰብአዊ መብት አያያዝ ማሻሻያ ካልተደረገ ሳዑዲ ውድድሩን ማዘጋጀት እንደሌለባት ገልጿል።
ውድድሩን ማዘጋጀቷ ለተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚያጋልጥ ሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አስታውቋል።
ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከሠራተኞች መብት ተሟጋቾች ጋር በመሆን ሳዑዲ የስደተኛ ሠራተኞችን መብት መጣሷን በማጣቀስ ተቃውሞ አሰምተዋል።
ፊፋ እና ሳዑዲ ስለ ትችቱ ምላሽ አልሰጡም።
ፊፋ ያወጠውን ሪፖርት በተመለከት አምነስቲ “አገሪቱ የፈጸመችውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በአስገራሚ መልክ የካደ ነው። ሠራተኞች ላለመበዝበዛቸው፣ ሰዎች ላለመፈናቀላቸው እና የመብት ተሟጋቾች ላለመታሰራቸው ምንም ማረጋገጫ የለም” ብሏል።
“የሰብአዊ መብት ጥሰትን ፊፋ ችላ ማለቱ የመብት ጥሰት እንዲቀጥል በማድረግ ኃላፊነት እንዲወስድ ያደርገዋል። በሳዑዲ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት አያያዝ ለውጥ ያስፈልጋል። የ2034 የዓለም ዋንጫ በብዝበዛ፣ በጭቆና እና በመድልዎ ይበላሻል” ሲልም አክሏል።
ፌር ስኩዌር የተባለው ሰብአዊ መብት ተሟጋች ፊፋ “አዲስ ዝቅጠት ውስጥ ገብቷል” ብሏል።
ፊፋ በትችቱ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
የአካባቢ ጥበቃ
ሳዑዲ 15 አዲስ ስቴድየሞችን በአምስት ከተሞች ለመገንባት አቅዳለች። ስምንት አዳዲስ ሕንጻዎችም ይገነባሉ።
ፊፋ እንዳለው “ሳዑዲ ውድድሩ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመገንዘብ ተጽዕኖውን ለመቀነስ እርምጃ እየወሰደች” ትገኛለች።
“ግንባታው በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ጫና ያሳድራል። ሳዑዲ አሁን ያሉ ሕንጻዎችን ለመጠቀም ሐሳብ አቅርባለች” ብሏል።
የአየር ጉዞ ብክለት የሚፈጥር እንደሆነ እና ይህም ለአየር ሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነው የካርበን ልቀት እንደሚጨምር ፊፋ ገልጿል።
“በአገሪቱ የታሰበው የትራንስፖርት አቅርቦት ነጻ የሕዝብ መጓጓዣ ለተመልካቾች ማቅረብን የሚያካትት ስለሆነ አደጋውን ይቀንሰዋል” ሲልም አክሏል።
የ2030 የዓለም ዋንጫ በስድስት ከተሞች የሚካሄድ መሆኑ የአየር ጉዞ መጠንን በመጨመር አካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የጎላ እንደሚሆን ተገለጿል።
ፊፋ በበኩሉ አዘጋጅ አገራት “አካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት የተሻለ እና ዘላቂነት ያለው የትራንስፖርት አማራጭ በማቅረብ ጉዳቱን ለመቀነስ እንደሚሠሩ ገልጸዋል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በ2023 አንድ የስዊዘርላንድ ተቋም እንዳለው፣ ፊፋ የ2022 የዓለም ዋንጫን በተመለከተ በኳታር በአካባቢ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንደሚቀነስ ቢናገርም ይህ እውን አልሆነም።
አምነስቲ በበኩሉ፣ ሞሮኮ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን እንዴት አካባቢ ላይ የሚደርስ ብክለትን እንደሚቀንሱ፣ ተጫዋቾች እና ተመልካቾች እንዴት ከብዝበዛ እና ከመድልዎ እንደሚጠበቁ፣ ከፖሊስ ብዝበዛ እንዴት ጥበቃ እንደሚደረግ እንዲሁም የነዋሪዎች የቤት ባለቤትነት መብት እንዴት እንደሚከበር በግልጽ አላስረዱም ብሏል።