ኬይ ካማራ ከ40 ዓመቱ በኋላም ብሔራዊ ቡድኑን በማገልገል ላይ ይገኛል

ከ 1 ሰአት በፊት

ኬይ ካማራ ባለፈው ሳምንት ለብሔራዊ ቡድኑ በመጫወት 40 ዓመታቸውን ካከበሩ በኋላ ለአገራቸው አገልግሎታቸውን ከሰጡ አፍሪካዊያን አንዱ ለመሆን በቅቷል።

አጥቂው ለሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን በአሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከርም በምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሰንጠረዥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ብሔራዊ ቡድኑን ለሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ለማገዝ ጫማውን ከሰቀለበት ተመልሶ ቢጫወትም ውጥኑ ከግብ አልደረሰም።

በዚህም በ41 ዓመቱ በአፍሪካ ዋንጫ አገሩን እንዳይወክል ሆኗል። በርካታ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ግን 40 ዓመት ካለፋቸው በኋላም ብሔራዊ ቡድናቸውን ማገልገል ችለዋል። አንደኛው ደግሞ ካማራ ጫማውን ከሰቀለበት እንዲያወርድ ምክንያት ሆኖታል።

ከ40 ዓመታቸው በኋላ ውጤታማ መሆኑን የቻሉ የተወሰኑ አፍሪካዊያን ተጫዋቾችን ቢቢሲ እንደሚከተለው ቃኝቷቸዋል።

ሮጀር ሚላ (ካሜሮን)

ሮጀር ሚላ የዓለም ዋንጫ በዕድሜ ትልቁ ጎል አስቆጣሪ ነው

በዚህ ዝርዝር ውስጥ ቀድሞ የሚጠቀሰው ሮጀር ሚላ ነው። ሚላ ከዕድሜው ባሻገር በዓለም ዋንጫ ላይ ጎል በማስቆጠር የማዕዘን መምቻው ላይ በሚያሳየው የደስታ አገላለጽ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።

ተጫዋቹ ጫማውን ከሰቀለበት ወደ ሜዳ የተመለሰው በ38 ዓመቱ ነበር። በጣሊያን የዓለም ዋንጫ እንዲሳተፍ በማለት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ ነበሩ ውሳኔውን እንዲቀለብስ የጠየቁት።

በምድብ ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ሮማንያ ላይ ሁለት ጎሎችን አስቆጠረ።

በሁለተኛው ዙርም በተመሳሳይ ኮሎምቢያ ላይ ሁለት ጎሎችን አስቆጠረ። ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ በመድረስ የመጀመሪያው አፍሪካ ቡድን ቢሆንም በእንግሊዝ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆነ።

ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ለመሳም የበቃው ሚላ አሁንም ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን አገለለ። በድጋሚ ደግሞ ለአሜሪካው የዓለም ዋንጫ አገሩን ለማገልገል ብቅ አለ።

ከውድድሩ በፊት በሦስት ወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ተሰለፈ።

በውድድሩ ላይ ከብራዚል ጋር ተሰልፎ ለመጫወት በቃ።

ካሜሮን በሩስያ 6 ለ 1 ስትሸነፍ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ሚላ በ42 ዓመት ከ39 ቀናት ጎል በማስቆጠር በዕድሜ ትልቁ የዓለም ዋንጫ ጎል አስቆጣሪ ለመሆን በቃ።

ከግብ ጠባቂ ውጭ በዕድሜ ትልቁ በዓለም ዋንጫ ላይ የተሰለፈ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። ግብ ጠባቂዎችንም ካጠቃለልን ግን ክብረ ወሰኑ በሌላ አፍሪካዊ እጅ ይገኛል።

ኤሳም ኤል-ሃዳሪ (ግብጽ)

ግብጻዊው ግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል-ሃዳሪ በተደጋጋሚ አፍሪካ ዋንጫን ማሳካት ችሏል

በዓለም ዋንጫ በዕድሜ ትልቁ ተጫዋች በመሆን መሰለፍ የቻለው ግብጻዊው ኤኣም ኤል-ሃዳሪ ነው። ግብ ጠባቂው በሩሲያው የዓለም ዋንጫ በ45 ዓመት ከ161 ቀናት በመሰለፍ ክብረ ወሰኑን ይዟል።

በውድድሩ ላይ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በነበረው የመጨረሻው የደረጃ ጨዋታ ነበር። በዓለም ዋንጫው ፍጹም ቅጣት ምት በማዳን የመጀመሪያው አፍሪካዊ ግብ ጠባቂ ቢሆንም ቡድኑን 2 ለ 1 ከመሸነፍ መታደግ አልቻለም።

ለብሔራዊ ቡድኑ እአአ በ1996 በ23 ዓመቱ መጫወት የጀመረው ኤል-ሃዳሪ 159 ጊዜ ለግብጽ ለመሰለፍ በቅቷል። 40 ዓመቱን ካከበረ በኋላ ከ20 ጊዜ በላይ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመሰለፍ ችሏል።

ያስመዘገበው ቁጥር ከፍተኛ ቢመስልም ለግብጽ ብሔራዊ ቡድን በብዛት ከተሰለፉ ተጫዋቾች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚቀመጠው።

ግብጽ በሰባት የአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ ኤል-ሃዳሪ የቡድኑ አባል ነበር። እአአ በ1998፣ 2006፣ 2008 እና 2010 የአፍሪካ ዋንጫን ሲያነሱም ቡድኑን አገልግሏል።

ካሉሻ ብዋሊያ (ዛምቢያ)

ዛምቢያ የ2012ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ ካሉሻ ብዋሊያ የአገሪቱ የአግር ኳስ ፕሬዝዳንት ነበር

ካሉሻ ብዋሊያ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር እአአ በ1988 የአፍሪካ ዋንጫን አንስቷል። በ2004 ጫማውን ከሰቀለበት ተመልሶ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመሰለፍ ሲወስን ግን ብዙዎች ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ራሱን ለመመረጥ በቃ ሲሉ ብዙዎች ገልጸዋል።

በ2000 ጫማውን ከሰቀለ ከሦስት ዓመት በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ማሰልጠን ጀመረ። ዋናው ግቡ ደግሞ ለ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑን ማብቃት ነበር።

በኮሳፋ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ሞሪሺየስን 3 ለ 1 ሲረታ ራሱን ቀይሮ በማስገባት ጎል ለማስቆጠር በቃ። ከሁለት ወር በኋላ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከላይቤሪያ ጋር በነበረ ጨዋታ በድጋሚ ተሰለፈ።

ጨዋታው ያለምንም ጎል እስከ 68ኛው ደቂቃ ሲጓዝ የ41 ዓመቱ አሰልጣኝ ራሱን ቀይሮ ወደ ሜዳ አስገባ። ባለቀ ሰዓት የታወቀበትን የቅጣት ምት ጎል በማስቆጠርም ቡድኑ 1 ለምንም እንዲያሸንፍ አስቻለ።

ዛምቢያ ለዓለም ዋንጫ ሳታልፍ ቀረች። ብዋሊያም በኮሳፋ የፍጻሜ ጨዋታ ወሳኟን መለያ ምት በመሳቱ አንጎላ የውድድሩ አሸናፊ ሆነች።

ብሩስ ግሮቤላር (ዚምባብዌ)

ብሩስ ግሮቤላር ዚምባብዌን ለዓለም ዋንጫ ለማሳለፍ ከጫፍ ደርሶ ነበር

ልክ እንደ ብዋሊያ ሁሉ ግብ ጠባቂው ግሮቤላር ጫማውን ከሰቀለበት አውርዶ ከመጫወቱም በላይ አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት ራሱን ቀይሮ ወደሜዳም አስገብቷል።

ደቡብ አፍሪካ ቢወለድም ልጅ እያለ ነበር ቤተሰቦቹ በወቅቱ ሮዴዥያ ወደምትባለው አገር ያቀኑት።

በአገሪቱ የነበረውን የደፈጣ ውጊያ ለመከላከል አስገዳጅ በነበረው የብሔራዊ አገልግሎት እአአ በ1975 ተሳትፏል። በ1977 ደግሞ ለሮዴዥያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ የትውልድ አገሩ ደቡብ አፍሪካን በተቃራኒ ሆኖ ገጥሟል።

ከጦርነቱ በኋላ የሊቨርፑሉ ታሪካዊ ተጫዋች በኋላ ዚምባብዌ ተብላ ለተጠራችው አገሩ እአአ በ1982 እና 1986 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተሰልፎ ተጫውቷል። በኋላም ከብሔራዊ ቡድኑ ለረዥም ጊዜ ራሱን አገለለ።

በ1992 ወደ ቡድኑ ተመልሶ አገሩ ለ1994 የኣለም ዋንጫ ለማለፍ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ወሰነ። አሸናፊው ለዓለም ዋንጫ በሚያልፍበት ጨዋታ በካሜሮን ተሸነፉ።

በ41 ዓመቱ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ። በዚህ ወቅትም ለዚምባብዌ የመጨረሻ ጨዋታውን ለመሰለፍ ቻለ።

ጆርጅ ዊሃ (ላይቤሪያ)

ጆርጅ ዊሃ በምርጫ በማሸነፍ ላይቤሪያን ለአንድ ዙር በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በቅቷል

ብቸኛው አፍሪካዊ የባለን ደኦር አሸነፊው ጆርጅ ዊሃ በ51 ዓመቱ ለላይቤሪያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ችሏል። ይህም በዕድሜ ትልቁ ለብሔራዊ ቡድን የተጫወተ እግር ኳሰኛ አደርጎታል።

ይህን ክብረወሰን የሆነው መስከረም 2018 ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ ምርጫ አሸንፎ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቃ።

በፊፋ ዕውቅና ባልተሰጠው እና የሚታወቅበትን 14 ቁጥር ለመስቀል በሚል በተደረገ ጨዋታ ላይ ለ79 ደቂቃዎች ቢጫወትም ቡድኑ በናይጄሪያ 2 ለ 1 ተሸንፏል።

ሁለቱም ቡድኖች በጠንካራ አሰላለፋቸው ወደ ሜዳ ባይገቡም የቀድሞው የሞናኮ፣ የፒኤስጂ እና የኤሲሚላን አጥቂ እንደ ዊልፍሬድ ንዲዲ እና ኬሌቸ ኢሂናቾ ካሉ ወጣት ኮከቦች ጋር ሜዳ ላይ ተፎካክሯል።

እአአ በ2002 ለመጀመሪያ ጊዜ ጫማውን ከሰቀለበት ጊዜ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር ለብሔራዊ ቡድኑ በድጋሚ ተመልሶ የተጫወተው። በ40 ዓመቱ ሃሳቡን በመቀየር ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ ከኢንዶኔዝያ ጋር ተጫወተው እአአ በ2007 ነበር።

በምርጫ በመሸነፉ በፕሬዝዳንትነት ለመቀጠል ያደረገው ሙከራ ያልተሳካው ዊሃ ለሦስተኛ ጊዜ በ58 ዓመቱ ለብሔራዊ ቡድኑ ይሰለፍ ይሆን?