
ከ 5 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ አባላትን የያዘው የብሪክስ ጥምረት አገራት ከአሜሪካው ዶላር ጋር ተፎካካሪ መገበያያ ገንዘብ መጠቀም ቢጀምሩ 100 ፐርሰንት ታሪፍ እንደሚጥሉ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።
“የብሪክስ አባል አገራት እኛ ቆመን እየተመለከትን ዶላርን መጠቀም ያቆማሉ ማለት ዘበት ነው” ሲሉ ትራምፕ ቅዳሜ እለት በማህበራዊ ሚዲያ ጽፈዋል።
ብሪክስ የዓለም ኃያላን አገራት የሆኑት ቻይና እና ሩሲያን እንዲሁም በዕድገት ላይ ያሉትን ብራዚል፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢራን፣ ግብጽ ፣የተባባሩት ኤምሬቶችን እና ኢትዮጵያን በአባልነት ይዟል።
የምዕራቡ ዓለምን የበላይነት የሚገዳደር እንደሆነ የሚቆጠረው ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እንዲኖር በማለት የተመሰረተ እንደሆነ ይነገራል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ወቅት በዋነኝነት ሲናገሩ የነበሩ መጠነ ሰፊ ታሪፎችን እንደሚጥሉ ቃል ሲገቡ ነበር። ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተለያዩ አገራት ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ሲዝቱ ተሰምተዋል።
ጥር 12/ 2017 ዓ.ም ስልጣን የሚረከቡት ትራምፕ የቅርብ ዛቻቸው ኢላማ ያደረገው በአብዛኛው ታዳጊ ኢኮኖሚ ያላቸው አገራትን በያዘው ብሪክስ ላይ ነው።
በብራዚል እና ሩሲያ ያሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች የአሜሪካ ዶላር በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ያለውን የበላይነት ለመቀነስ የብሪክስ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ለመፍጠር ኃሳብ አቅርበዋል። ሆኖም በጥምረቱ አባል አገራት ያለው ውስጣዊ አለመግባባት ምንም አይነት እመርታ እንዳይኖረው አድርጎታል።
- ኢትዮጵያን በአባልነት የተቀበለው ብሪክስ የአሜሪካን ልዕለ ኃያልነት ይገዳደር ይሆን?31 ነሐሴ 2023
- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ተወሰነ24 ነሐሴ 2023
- ብሪክስን መቀላቀል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ምን ያስገኛል?26 ነሐሴ 2023
“እነዚህ አገራት ኃያሉን የአሜሪካ ዶላር ለመተካት ወይም አዲስ የብሪክስ መገበያያ እንደማይፈጥሩ ቁርጠኝነታቸውን ሊያሳዪን ይገባል። ካለበለዚያ 100 በመቶ ታሪፍ እንደሚጠብቃቸው እና በአስደናቂው የአሜሪካ ምጣኔ ኃብት ምርቶቻቸውን ከመሸጥ እንደሚሰናበቱ ማወቅ አለባቸው” ሲሉ ነው ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘ ማህበራዊ ሚዲያቸው የዛቱት።
“ሞኛቸውን ሌላ ቦታ ሄደው መፈለግ ይችላሉ” ሲሉ አክለዋል።
የትራምፕ በአገራት ታሪፍ እጥላለሁ የሚለው ዛቻቸው የመደራደሪያ ስልቶች እንደሆኑ አንዳንድ አጋሮቻቸው ጠቁመዋል።
ታሪፍ እጥላለሁ የሚለውን የትራምፕን ማስፈራሪያዎች በተመለከተ የተጠየቁት የሪፐብሊካኑ ሴናተር ቴድ ክሩዝ “የመደራደሪያ መያዣን አስፈላጊነት” ጠቅሰዋል።
“በሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ ታሪፍ እጥላለሁ ዛቻ ምን ያህል በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ እንዳደረጋቸው መመልከት ይቻላል” ሲሉ ነው ፖለቲከኛው ለሲቢኤስ የተናገሩት።
ትራምፕ በካናዳ ላይ ታሪፍ እጥላለሁ ማለታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጀስቲን ትሩዶ ያልታቀደ ጉብኝት በአሜሪካ አድርገዋል። ወደ አሜሪካ በሚገቡ የካናዳ ምርቶች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እጥላለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው ፕሬዚዳንት ትሩዶ ወደ ትራምፕ መኖሪያ ቤት ያቀኑት።
ትራምፕ በግምጃ ቤት ጸሐፊነት ስኮት ቤሴንትን መምረጣቸው ተመራጩ ፕሬዚዳንት እየተናገሩ ያሉት የታሪፍ ጭማሪ ዛቻቸው የመደራደሪያ ስልታቸው አካል እንደሆነ ጠቁሟል።
“የእኔ አጠቃላይ እይታ ትራምፕ ነጻ ነጋዴ ነው” ሲሉ ቤሰንት በጸሐፊነት ከመሾማቸው በፊት ለፋይናንሺያል ታይምስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
“ነገሮችን ለማርገብ፣ መጀመሪያ ያጋግሉታል” ብለዋል።