
ከ 5 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሁለት የወንጀል ክሶች ለቀረቡበት ልጃቸው ሀንተር ኦፊሴላዊ ይቅርታ አደረጉ።
ባይደን ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለልጃቸው ይቅርታ ያደርጋሉ ተብሎ ቢነገርም ይህ አይሆንም ብለው ነበር።
ፕሬዝደንቱ በለቀቁት መግለጫ ልጃቸው “ተነጥሎ” ጥቃት ደርሶባታል፤ ይህ ደግሞ “የፍትሕ መዛባት ነው” ብለዋል።
ሀንተር ባይደን ባለፈው መስከረም ታክስን በተመለከተ ለቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ነኝ ያለ ሲሆን በሌላ ክስ ደግሞ ያልተፈቀደ ዕፅ በመጠቀምና የጦር መሣሪያ በመሸከም ባለፈው ሰኔ ጥፋተኛ ተብሏል።
ሀንተር በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ የመጀመሪያው የተቀማጭ ፕሬዝደንት ልጅ ነው።
ጆ ባይደን ለልጃቸው ይቅርታ ማድረጋቸውን ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ “ፕሬዝደንቱ ለልጃቸው ያደረጉት ይቅርታ [ሰኔ 6] ታስረው ለዓመታት የሚማቅቁትን ይመለከታል? ይህ ፍትሕ መበዝበዝ እና ማዛባት ነው” ብለዋል።
የትራምፕ ደጋፊዎች በአውሮፓውያኑ ሰኔ 6፤ 2021 ከምርጫው ውጤት በኋኃ አመፅ ቀስቅሰው ካፒቶል ሒል ወደተባለው ሕንፃ ገብተው መረበሻቸው አይዘነጋም።
ጆ ባይደን ለልጃቸው ይቅርታ ያደርጉ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተጠይቀው አላደርገውም ማለታቸው ይታወሳል።
- የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስለኢትዮጵያ ምን አሉ?1 ታህሳስ 2024
- የሶሪያን ትልቅ ከተማን ለመቆጣጠር የተቃረበው፤ ለሩሲያ እና ለአሳድ አልያዝ ያለው አማፂ ቡድን ማነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- የትራምፕ ታማኝ ባለሟል የሆኑት ግለሰብ ኤፍቢአይን እንዲመሩ ተመረጡ1 ታህሳስ 2024
ባለፈው መስከረም የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ጆ ባይደን ለልጃቸው ይቅርታ አያደርጉም ብለው ነበር።
ነገር ግን እሑድ አመሻሹን ፕሬዝደንት ባይደን በፍትሕ ሥርዓቱ ቢያምኑም “ፖለቲካ በክሎት የፍትሕ መዛባት እንዲከሰት አድርጓል” የሚል መግለጫ አውጥተዋል።
“ሥልጣን ከያዝኩ ጀምሮ በፍትሕ ሥርዓቱ ጣልቃ አልገባም ብዬ ነበር። በቃሌ መሠረት ልጄ ተነጥሎ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ሲፈረድበት ምንም ሳልል ስመለከት ነበር” ብለዋል።
ባይደን እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ብዙ እንደታገሉም አስረድተዋል።
“አሜሪካዊያን አንድ አባት እና ፕሬዝደንት የሆነ ግለሰብ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ።”
ይቅርታ የተደረገለት የፕሬዝደንቱ ልጅ ሀንተር “በጨለማው እና ሱስ ባናወዘው ዘመኔ የሠራሁት ስኅተት ለፖለቲካ ጥቅምት ውሏል” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
“ይቅርታውን እንደዋዛ የማየው አይደለም። ቀሪውን ዘመኔን የታመሙና የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት አሳልፋለሁ” ብሏል።
አባት እንደሚሉት ልጃቸው ላላፉት አምስት ዓመታት ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥም ሆነ ዕፅ ተጠቅሞ አያውቅም።
አንድ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለቤተሰብ አባል ይቅርታ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ቢል ክሊንተን ለግማሽ ወንድማቸው ሮጀር ክሊንተን ይቅርታ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
በ2020 ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባል አባት ለሆኑት ቻርልስ ኩሽነር ይቅርታ አድርገዋል።
ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ቻርልስ ኩሽነርን በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር አድርገው ሹመዋቸዋል።