
ከ 8 ሰአት በፊት
ሪሀብ ፋውር አራት ጊዜ ከቤቷ ተፈናቅላለች።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈናቀለችው ከዓመት በፊት ነበር። የእስራኤልን የአየር ጥቃት በተደጋጋሚ ብትሸሽም ማምለጥ ቀላል አልሆነም።
ሊባኖስ ውስጥ የትኛውም ቦታ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም።
እስራኤል ጥቃት ያደረሰችው የ33 ዓመቷ ሪሀብ እና ባለቤቷ በሚኖሩበት መንደር ነው።
ባለቤቷ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ በውሃ አገልግሎት ዘርፍ ይሠራ ነበር።
የአየር ድብደባ ሲፈጸም የስምንት ዓመት ልጃቸው ቲያ እና የስድስት ዓመት ልጃቸው ናያን ይዘው ከቤይሩት አቅራቢያ ወዳለው ዳሂህ ሸሹ።
በሪሀብ ቤተሰቦች ቤት ተጠልለው ቆዩ። ልጆቻቸው ጓደኞቻቸው ይናፍቋቸው ነበር። ጥለውት የሄዱት ቤት እና መጫወቻቸው ይናፍቃቸውም ነበር።

ትምህርት ቤት መሄድ አቁመው በበይነ መረብ ይማሩ ጀመር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን አዲስ ትምህርት ቤት ተመዘገቡ።
የደንብ ልብስ ተገዝቶላቸው ለመማር እየተዘጋጁ ሳለ እስራኤል በቤይሩት አቅራቢያ የሚገኘውን ዳሂህን በአየር መደብደብ ጀመረች።
የሄዝቦላህ መሪዎች ሲገደሉ ቤቶችን የሚያወድም ጥቃት እየተፈጸመ ነበር።
በእስራኤል ጥቃት ሕንጻዎች ወደሙ። በከተሞች መዘዋወርም አልተቻለም።
የሪሀብ ቤተሰብ ወደ ጃናህ አካባቢ ሸሸ። ከባለቤቷ ሰዒድ ቤተሰቦች ጋር መኖር ጀመሩ።
በአንድ ቤት ውስጥ 17 ሰዎች ይኖሩ ነበር።
ቲያ እና ናያ ከአክስት እና ከአጎት ልጆች ጋር አብረው ኖሩ።
የቀድሞ የሊባኖስ ሠራዊት መኮንን የሆነው የሰዒድ አባት ቤት ቢከራይላቸውም ልጆቹ እዚያው መቆየት ፈለጉ።
“ከቤተሰቦቻችን ጋር እንድንቆይ ልጆቼ ለመኑኝ። ወደ አዲሱ ቤት ሄደን ከዚያ ወደ ቤተሰቡ ቤት እንደምንመለስ ነገርናቸው” ትላለች እናታቸው።
ልጆቹን ለማባበል ሲሉ ልጆቹ የመረጡትን እራት ለመብላት ተስማሙ። ዶሮ በልተው፣ ለልጆቹ መጫወቻ ገዝተው በማዕከላዊ ቤይሩት በሚገኘው ባስታ ወደተከራዩት ቤት አቀኑ።
እአአ በ2006 የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ጦርነት የተካሄደው በደቡባዊ የሊባኖስ አካባቢ ነበር። መሠረተ ልማቶች ዒላማ ተደርገውም ነበር።
በዚህኛው ጦርነት ግን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የሄዝቦላህን ከፍተኛ አመራሮችን ዒላማ ለማድረግ ሲባል በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ደርሷል።
ከዚህ ቀደም ዒላማ ባልነበሩ የቤይሩት አካባቢዎችም ጥቃት ተፈጽሟል።
ቲያ እና ኒያ አዲስ ቤት ገቡ። አዲሱ ቤት እንደ አያቶቻቸው ቤት ሳይሆን ውሃ እና መብራት ያለው ነው።
ሪሀብ እና ሰዒድም ትንሽ ተረጋጉ። የእስራኤልን የድሮን ድምጽ መስማታቸው ግን አልቀረም።

- “ወደ ቤታችን ልንመለስ ነው፤ ደስ ብሎናል” – በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን28 ህዳር 2024
- በሊባኖስ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ስለምን በጋዛ አልሳካ አለ?28 ህዳር 2024
- “በእሳት እየተቃጠልን እያያችሁ ዝምታን መረጣችሁ” – እናት እና ልጆች በእሳት ቃጠሎ ያጣው ቤተሰብ21 ጥቅምት 2024
“ምግብ አቅርበን እየበላን እና እየሳቅን ነበር። የመጨረሻ ትውስታዬ ያ ነው” ትላለች ሪሀብ።
የሚኖሩበት ሕንጻ በቦምብ ተመታ።
አሜሪካ ሠራሹ ጂዳም ቦምብ ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ነበር ቤታቸውን የመታው።
በቤታቸው አቅራቢያ ያሉ ቤቶች ወድመዋል። ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 22 ሰዎችም ተገድለዋል።
በማዕከላዊ ቤይሩት ከደረሱ ጥቃቶች የከፋው ነው።
የእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ ስላልሰጠ ሕንጻው ውስጥ ያሉ ሰዎች አልወጡም።
እስራኤል ዒላማ ያደረገችው የሄዝቦላህን አስተባባሪ ቡድን ኃላፊ ዋፊቅ ሳፋ እንደሆነ ገልጻለች።
ከሞቱት ወይም ከጥቃቱ ከተረፉት ሰዎች መካከል ግን ዋፊቅ የለበትም። ከመነሻውም እዚያ መኖሩ እርግጥ አይደለም።
እስራኤል ለምን ቀድማ በማስጠንቂያ አላሳወቀችም በሚለው ላይ አስተያየት አልሰጠችም።
ሪሀብ ራሷን ያገኘችው ዘሀራ ሆስፒታል ነው። መንቀሳቀስ አትችልም ነበር። ቢያነስ ሁለት ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ተነገራት።
ሰመመን ውስጥ ነበረች። ከልጆቿ ጋር እራት እየበላች ስትስቅ ትውስ ይላታል። ራሷን ግን ያገኘችው ሆስፒታል ውስጥ ነው።

ቤተሰቦቿ በየሆስፒታሉ እየፈለጓቸው ነበር። ኋላ ላይ ባለቤቷ ሰዒድ እንዲሁም ልጆቿ ቲያ እና ናያ መሞታቸውን አወቁ።
ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ማንነታቸው የታወቀው በዘረ መል ምርመራ ነበር።
የሪሀብ ቤተሰቦች ስለ ልጆቿ እና ባለቤቷ ሞት ለሪሀብ እንዳይነግሯት ሐኪም አስጠነቀቃቸው።
ባለቤቷ እና ልጆቿ ሌላ ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆነ እናቷ ባሲማ ነገሯት። ለሁለት ሳምንት ሆስፒታል ቆየች።
ሪሀብ ግን አንዳች ነገር መፈጠሩን ልቧ ነግሯታል።
“ቀልቧ ሳያውቅ አልቀረም” ይላሉ እናቷ ባሲማ።

ከ15 ቀናት በኋላ ባለቤቷ እና ልጆቿ እንደሞቱ ለሪሀብ የሥነ ልቦና ባለሙያ ነገራት።
ከስድስት ሳምንታት በኋላ ሪሀብ ቤይሩት ባለ መኖሪያ ውስጥ አንገቷን ደፍታ ተቀምጣለች።
ከቀዶ ሕክምናዋ ገና እያገገመች ነው። ጀርባዋ እና ክንዷ ላይ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።
ለመራመድ ትሞክራለች። አብዛኛውን ሰዓት ትተኛለች ወይም ትቀመጣለች። ሁሉም ነገር ያማታል።
የናያ ስምንተኛ ዓመት ልደት ካለፈ አራት ቀን ሆኖታል።
“ወይ አለቅሳለሁ ወይ እተኛለሁ” ትላለች ሪሀብ።
“ናያ የትም ብሄድ ትከተለኛለች። ቲያ አያቶቿን በጣም ትወዳለች። አብረናቸው ስንኖር ደስተኛ ነበረች። ሥዕል መሳል ይወዱ ነበር ልጆቼ። እቃቃ መጫወት ይወዱ ነበር። ትምህርት ቤት መሄድ ሲያቆም ትምህርት ናፈቀን ይሉ ነበር። እንደ ተማሪ እና አስተማሪ ሆነው ለሰዓታት ይጫወቱ ነበር” ስትል ታስታውሳቸዋለች።

ቲክ ቶክ ላይ አብረው ቪድዮ ማየት ያስደስታቸው ነበር።
ሪሀብ እና ሰዒድ ልጆቻቸው ሲደንሱ ቪድዮ ይቀርጹ ነበር። ልጆቻቸው ዕድሜያቸው ስላልደረሰ ቪድዮዎች ቲክ ቶክ ላይ ባይለቁትም ቀርጸው ያስቀምጡታል።
ሪሀብ ያደገችው ቤይሩት ነው። ማይስ ኤል ጃባል የተባለውን አካባቢ ከቤተሰቦቿ ጋር ስትጎበኝ ነበር ሰዒድን የተዋወቀችው።
እአአ በ2013 በጓደኞቻቸው አማካይነት ተዋወቁ። በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛ ሁለተኛ ዲግሪ ለመማር እየተዘጋጀች ሳለ ቲያ ተወለደች።
አሁን በሐዘን ተሰብራለች።
“ቀኔን የማሳልፍበት ነገር ያስፈልገኛል” ትላለች። ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ እያሰበች ነው።
ሰዒድ እና ቲያ በሞቱ በማግስቱ ተቀብረዋል።

የቀበሯቸው የሪሀብ አባት እና አጎቶች ናቸው። ጊዜያዊ የእንጨት ሬሳ ሳጥን ገዝተው በዳሂህ ቀብረዋቸዋል።
ቤተሰቡ በዚያው አካባቢ ኒያንም ቀብሯል።
ለእህትማማቾቹ መታሰቢያ አበባ መቃብራቸው ጋር ተክለዋል።
ብዙም ሳይቆይ እስራኤል በአካባቢው የአየር ጥቃት ፈጸመች። በዚህም የመቃብር ስፍራው ላይ ጉዳት ደርሷል። የሪሀብ ቤተሰቦች ቤት አቅራቢያም ሌላ ጥቃት ተፈጽሟል።
ሪሀብ ለልጆቿ የገዛቸውን የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ መጣል አትፈልግም።
ባለፈው ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል መደረሱት ተከትሎ ነዋሪዎች ወደፈራረሱ ቤቶቻቸው እየተመለሱ ነው።
የሪሀብ እና ሰዒድ መንደር ክፉኛ ተጎድቷል።
ሊባኖሳውያን በተኩስ አቁሙ ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ሪሀብ ወደ ቤቷ መመለስ አትሻም።
ባለቤቷ ሰዒድ እና ልጆቿ ቲያ እና ኒያ የተገደሉበት የእስራኤል የአየር ጥቃት የተፈጸመው ዋፊቅ ሳፋን ለመግደል እንደሆነ ተገልጿል።
ዋፊቅ ሳፋ ግን አሁንም በሕይወት ይገኛል።