
ከ 6 ሰአት በፊት
የ68 ዓመቷ ቪዬትናሚዊቷ ባለሃብት ትሩንግ ማይ ላን ባለፈው ሚያዝያ በዓለም ላይ ትልቁ የባንክ ማጭበርበርን በማቀናበር ጥፋተኛ ተብላ የሞት ፍርድ ፍርድ ተፈርዶባታል።
ቱጃሯ ይህን ፍርድ ለመቀልበስ ይግባኝ ጠይቃ እየተጠባበቀች ዕዳዋን ለመክፈል 9 ቢሊዮን ዶላር እያሰባሰበች ነበር።
ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ማክሰኞ በዋለው ችሎት የባለሀብቷን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ የሞት ቅጣቷ ተፈፃሚ እንዲሆን ወስኗል።
በቬዬትናም ቢሮ ውስጥ በተፈጸመ ወንጀል የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው በጣም ጥቂት ሴቶች አንዷ ናት።
በቬዬትናም ህግ መሠረት አጭበርብራለች ከተባለው ገንዘብ 75 በመቶውን መመለስ ከቻለች ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ይቀየርላታል።
በአገሪቱ በትልቅነቱ አምስተኛ የሆነውን ሳይጎን ባንክ በድብቅ በመቆጣጠር ከ10 ዓመታት በላይ በውጭ አገራት በሚገኙ ኩባንያዎች አማካኝነት በድምሩ 44 ቢሊዮን ዶላር በብድር እና በጥሬ ገንዘብ መውሰዷን ፍርድ ቤት ደርሶበታል።
አቃቤ ህግ እንደሚለው ከሆነ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 27 ቢሊየን ዶላር አላግባብ ጥቅም ላይ ሲውል፤ 12 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ተመዝብሯል። በዚህ ከባድ በሆነ የገንዘብ ወንጀል ነው በሞት እንድትቀጣ የተፈረደባት።
በፍርድ ችሎትዋ ወቅት አንዳንድ ጊዜ ራሷን ለመከላከል ስትሞክር ብትታይም በቅርቡ በተደረጉ ሌሎች ችሎቶች ግን የጸጸት ምልክት አሳይታለች።
በመንግስት ላይ እንደዚህ አይነት ከባድ ተግባር መፈጸሟ እንዳሳፍራት ተናግራ እና አሁን ሃሳቧ የወሰደችውን ገንዘብ መመለስ ብቻ እንደሆነ ተናግራ ነበር።
ፍርድ ቤቱ በማክሰኞው ውሎው ውሳኔ መቀየር የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም ሲል ይግባኟን ውድቅ አድርጓል። ባለሀብቷ በቀጣይ ለሀገሪቱ ፕሬዝደንት የይቅርታ ደብዳቤ ልታስገባ እንደምትችል ይጠበቃል።

- በአዲስ አበባ ከታህሳስ ጀምሮ የባንክ አካውንት ለመክፈት የ’ፋይዳ’ መታወቂያ ማቅረብ ግዴታ ሊሆን ነው2 ታህሳስ 2024
- የጃጉዋር አዲሱ የኤሌክትሪክ መኪና መነጋገሪያ ሆነከ 7 ሰአት በፊት
- የሙሴቬኒ ቀንደኛ ተቃዋሚ እንዴት ከኬንያ ተሰውሮ በኡጋንዳ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ተገኘ?ከ 8 ሰአት በፊት
በሆቺ ሚን ከተማ ከቻይናዊ-ቪዬትናማዊያን ቤተሰብ የተወለደችው ትሩንግ ማይ ላን መንገድ ዳር ድንኳን ዘርግታ ከእናቷ ጋር መዋቢያ ዕቃዎችን በመሸጥ ነው ወደ ንግዱ ዓለም የገባችው።
በ1986 የኮሚኒስት ፓርቲው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ መሬት እና ንብረት መግዛት እና መሸጥ ያዘች። በ1990ዎቹ ትልልቅ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች ከፍታ ለማንቀሳቀስ በቅታለች።
በሚያዝያ ወር ጥፋተኛ ተብላ በተፈረደባት ወቅት ቫን ቲንህ ፋት ግሩፕ የተባለ ታዋቂ የሪል ስቴት ድርጅት ሊቀመንበር ነበረች።
ሁሉም 85 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለዋል። አራቱ የእድሜ ልክ ተፈርዶባቸዋል። ቀሪዎቹ ከ20 ዓመት እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስራት ተወስኖባቸዋል። የትሩንግ ማይ ላን ባል እና የእህት ልጅ የ9 እና 17 ዓመት እስራት ተላለፎባቸዋል።
የቬዬትናም መንግሥት ባንክ የባንኮችን ውድቀት ለመከላከል በሚል እና ሳይጎን ባንክን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን እንዳፈሰሰ ይታመናል። አቃቤ ህግ ባለሃብቷ የፈፀመችው ወንጀል “ትልቅ” ከመሆኑም ባለፈ ምንም አዘኔታ አልነበራትም በማለት ተከራክሯል።
የትሩንግ ማይ ላን ጠበቆች በበኩላቸው የሚፈለገውን 9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በተቻላት ፍጥነት እየሠራች ነው ብለው ነበር። ንብረቶቿን ገንዘብ የማውጣታቸው ነገር ግን አስቸጋሪ ሆኖባት ቆይቷል።
አንዳንዶቹ ንብረቶቿ በሆቺ ሚን ከተማ ውስጥ ያሉ ቅንጡ ንብረቶች በመሆናቸው በፍጥነት ሊሸጡ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ ንግዶች ወይም የቤት ፕሮጀክቶች ውስጥ በአክሲዮን መልክ የሚገኙ ናቸው።
መንግስት በሁሉም ግዛት ውስጥ የሚገኙ ከማጭበርበሩ ጋር የተያያዙ ከአንድ ሺህ በላይ የተለያዩ ንብረቶችን ለይቷል። እነዚህ ንብረቶች ለጊዜው እንዲታገዱ ሆነዋል። ቢቢሲ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ ባለሃብቷ ከጓደኞቿ ዘንድ ብድር እንዲሰበስብላትም ጥረት አድርጋለች።

ጠበቆቿ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ከዳኞች ምህረት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። በሞት ፍርድ ላይ እያለች ንብረቶቿን እና ኢንቨስትመንቶቿን በጥሩ ዋጋ ተደራድራ ለመሸጥ አስቸጋሪ እንደሚሆንባት እና 9 ቢሊዮን ዶላሩን ለማግኘት በጣም ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ፍርዱ ዕድሜ ልክ እስራት ቢደረግላት ብዙ የተሻለ ነገር ማድረግ ትችላለች ብለው ተከራክረዋል።
“የንብረቷ አጠቃላይ ዋጋ ከሚከፈለው የካሳ መጠን ይበልጣል” ሲል ጠበቃዋ ንጉዪን ሁይ ቲፕ ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ሆኖም እነዚህን ንብረቶች ለመሸጥ ጊዜ እና ጥረት ይጠይቃል። ምክንያቱም ብዙዎቹ ንብረቶች የሪል ስቴት ቤቶች በመሆናቸው ጊዜ ይጠይቃሉ። ትሩንግ ማይ ላን የካሳ ክፍያውን እንድትከፍል ፍርድ ቤቱ በጣም ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርላት ተስፋ እናደርጋለን።”
ዳኞች በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ ብለው የሚያስቡት ግን ጥቂቶች ናቸው። እንደተጠበቀው ዳኞቹ ይግባኝዋን ውድቅ ካደረጉ ትሩንግ ማይ ላን የሚጠበቅባትን ገንዘብ ለማሰባሰብ ከሞት ውሳኔው ጋር እሽቅድምድም ውስጥ ትገባለች።
ቬትናም የሞት ቅጣትን እንደ መንግስት ሚስጥር ትቆጥራለች። መንግስት ምን ያህል ሰዎች በሞት ፍርድ እንደፈተላለፈባቸው ይፋ አያደርግም። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግን ከአንድ ሺህ በላይ እንደሚሆኑ እና ቬትናም በዓለም ላይ የሞት ፍርድ በማስፈፈም ቀዳሚ ከሆኑ አገራት አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
ፍረደኞች ቅጣቱ ሳይተላለፍባቸው ለረዥም ጊዜ ቢቆዩም ቅጣቱን ከመፈጸሙ በፊት የሚሰጣቸው የማሳወቂያ ጊዜ አጭር ነው።
ይህ ከመሆኑ በፊት ትሩንግ ማይ ላን 9 ቢሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ከቻለች ህይወቷን ማትረፏ አይቀርም።