
ከ 8 ሰአት በፊት
የሙሴቬኒ ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆነው ኪዛ ቤሲግዬ ከኬንያ ድንገት ጠፍቶ በኡጋንዳ ወታደራዊ ፍርድ ቤት መታየቱ ብዙዎችን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል።
ሁለቱ ሀገራት ምስጢራዊ የሆነ መረጃ እየተለዋወጡ ነው የሚለው ጉዳይ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘንድ ፍርሀት የፈጠረ ይመስላል።
የቤሲግዬ ባለቤትና አጋሮች የተቃዋሚ ፓርቲ መሪውን እንዴት አፍነው የወሰዱት ሰዎች ኬንያዊያን በመምሰል አታለው እንደወሰዱት ይፋ አድርገዋል።
ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ቤሲግዬ ከኢንቴቤ አየር ማረፊያ አውሮፕላን ተሳፍሮ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ስለላ ሲደረግበት ነበር። ከኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ያለምንም ሒደት ተጠልፎ እንዴት በኡጋንዳ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሊገኝ እንደቻለም ይፋ ሆኗል።
ኬንያ ግለሰቡ ተጠልፎ ከሀገር ስለመውጣቱ የማውቀው ነገር የለም፤ ሁኔታውን እየመረመርኩ ነው ትላለች። ኡጋንዳ ደግሞ የኬንያ መንግሥት ስለሁኔታው ያውቃል፤ የደኅንነት ሰዎች ባደረጉት ትብብር ነው ቤሲግዬ የተያዘው ትላለች።
ቤሲግዬ በቅርቡ ካምፓላ በሚገኘ ወታደራዊ ችሎት ፊት ቀርቦ ክሱን ይከታተላል።
ኪዛ ቤሲግዬ ማነው?
ቤሲግዬ በአውሮፓውያኑ 1986 ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን ለማውረድ አራት ጊዜ በምርጫ ሙከራ አድርጎ አልተሳካለትም።
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፖለቲካው መስክ ንቁ ሆኖ ታይቷል። በ2021 የተደረገውን ምርጫ ውጤት ከሌላው ጊዜ በተለየ በፀጋ ተቀብሎታል።
ሰውዬው አዲስ ፓርቲ ያቋቋመው እየተገባደደ ባለው የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ነው። ከሁለት አስርታት በፊት ያቋቋመው ፎረም ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ ከተባለው የቀድሞ ፓርቲው ተገንጥሎ ፒፕልስ ፍሮንት ፎር ፍሪደም (ፒኤፍኤፍ) አቋቁሟል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ለዓመታት ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ በነፃነት ሲመላለስ ነው የከረመው። ወደ ናይሮቢ በመምጣት ትላልቅ ሰዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ያውቃል።
ሰውዬው የሙሴቬኒ ቀንደኛ ተቃዋሚ እና ተቺ ከሚባሉ ነባር ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነው።
- “ከእናንተ ቀድመን የገና በዓልን እናውቃለን” – አወዛጋቢው ለ77ቱ ረሃብ የተለቀቀው ዘፈን24 ህዳር 2024
- የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስለኢትዮጵያ ምን አሉ?1 ታህሳስ 2024
- “መምህር በመሆኔ አዘንኩ” – የኢትዮጵያ መምህራን እሮሮ27 ህዳር 2024
ቤሲግዬ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?
ቤሲግዬ ወደ ናይሮቢ የመጣው የኬንያ መንግሥት ተቃዋሚ የሆኑት ማርታ ካሩዋ ያሳተሙት መፅሐፍ ምረቃ ላይ ለመገኘት ነው።
የ68 ዓመቱ ፖለቲከኛ ናይሮቢ ያረፈው በአውሮፓውያኑ ኅዳር 16 ጥዋት ነበር። ከአየር ማረፊያው ታክሲ ይዞ ሀርሊንግሀም በተባለው የናይሮቢ መንደር ወደሚገኝ ሆቴል አቀና። ታክሲው ውስጥ አብሮት የረዥም ጊዜ አጋሩ ሀጅ ኦቤይድ ሉታሌ ይገኛል።
የፖለቲካ አጋሮቹ እንደሚሉት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከሆቴሉ ወጥቶ ታክሲ ተሳፍሮ ሪቨርሳይድ ድራይቭ ወደተባለ ቦታ በድብቅ ለተያዘ ስብሰባ ሄደ።
ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ይሄኔ ነው። ከአራት ቀናት በኋላ ኡጋንዳ የሚገኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ውስጥ ታየ።

የታክሲ አሽከርካሪው እንደሚለው ፖለቲከኛውን ለ12 ሰዓታት ያክል ቁጭ ብሎ ሲጠብቀው ቆይቶ በስተመጨረሻ ስልክ ሳይደወልለት ሲቀር ነው ጥሎ የሄደው።
ኡጋንዳ የሚገኙ የቤስጊዬ ፓርቲ አባላት አለቃቸው ስልኩ እንደማይነሳ ባረጋገጡ ጊዜ የእርዳታ ጥሪ ማቅረብ ጀመሩ።
የነባሩ ፖለቲከኛ መጥፋት የቀጣናው መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆነ። ባለቤቱ ዊኒ ብያንይማ ከየተባበሩት መንግሥታት የኤችአይቪ እና ኤድስ ጥበቃ ቢሮ ጋር በመሆን ባሏ ናይሮቢ ውስጥ “መታፈኑን” በማኅበራዊ ሚድያ አወጀች።
በሚቀጥለው ቀን በመፅሐፍ ምረቃው ላይ ተገኝቶ ንግግር ያሰማል ተብሎ ቢጠበቅም ለሱ የተዘጋጀው ወንበር ባዶ ሆኖ ተገኘ። የመፅሐፍ ምረቃው አዘጋጆች ሁኔታው ግራ አጋባቸው፤ ስጋት ላይ ጣላቸው።
ቤሲግዬ እንዴት ታፍኖ ተወሰደ?
ዊኒ እንደምትለው ፖለቲከኛው እና ጓደኛው ሉታሌ ሪቨርሳይድ ድራይቭ በተባለው መንገድ ላይ ካለ አንድ አፓርታማ የተገኙት ማንነቱ ያልታወቀ አንድ ኡጋንዳዊ እና ሌላ ስሙ ያልተገለፀ ብሪታኒያዊ ለማግኘት ነበር።
ብሪታኒያዊው ግለሰብ ቤስጊዬን ፒኤፍኤፍ ፓርቲን በገንዘብ መርዳት ከሚሹ የሥራ አጋሮቹ እና ባለሀብቶች ጋር እንደሚያገናኘው ነግሮታል ትላለች።
ወደ ክፍሉ ዘልቀው ሲገቡ ገንዘብ በውስጥ የያዘ የሚመስል ሳጥን ተቀምጧል። ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ ሁለት ሽጉጥ ይዟል።
ከትንሽ ቆይታ በኋላ የኬንያ ፖሊስ አባላት ነን ያሉ ሲቪል የለበሱ ስምንት ሰዎች በር ከፍተው ገብተው ቤስጊዬና ውስጥ የነበሩት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ነገሯቸው ስትል ዊኒ ለሲቲዝን ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግራለች።
ቤስጊዬ አፓርትማው ውስጥ ካሉት ንብረቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ቢነግራቸውም ፖሊስ ነን ያሉት ሰዎች ሊሰሙት አልፈቀዱም።
አራቱ ሰዎች ቤስጊዬንና ሉታሌን የኬንያ ታርጋ ወደለጠፈ መኪና ይዘዋቸው ሄዱ። መኪናውን በምሽት እያሽከረከሩ ወደ ኡጋንዳ ድንበር አመሩ።
“ይህ በደንብ የታሰበበት እንደሆነ በግልፅ የሚያስታውቅ ኦፕሬሽን ነው” ትላለች ዊኒ።

በስዋሂሊ ቋንቋ ሲነጋገሩ የነበሩት አራቱ ሰዎች ጠረፍ አካባቢ ሲደርሱ ሉጋንዳ እና ሩንያንኮሌ በተባሉት የኡጋንዳ ቋንቋዎች ማውራት ጀመሩ።
ሁለቱ ታፍነው እየተወሰዱ ያሉ ሰዎች በእጃቸው ምንም አልያዙም። ፓስፖርታቸው ሳይቀር ናይሮቢ የሚገኘው ሆቴል ውስጥ ነበር። ፓስፖርታቸውን የቤስጊዬ ፓርቲ ሰዎች ከሆቴሉ መቀበል ችለዋል።
የፒኤፍኤፍ ቃል አቀባይ ኢብራሒም ሴሙጁ ንጋንዳ ለኡጋንዳው ሞኒተር ጋዜጣ እንደናገሩት ቤስጊዬ እና ጓደኛው በማላባ ድንበር በኩል ሲያልፉ ምንም ዓይነት ፍተሻ አልደተረገባቸውም።
“የኬንያ ታርጋ የነበረውን መኪና ድንበር ላይ ጥለው የኡጋንዳ መለያ ቁጥር ባለው መኪና ነው ወደ ካምፓላ የተወሰዱት” ይላሉ ቃል አቀባዩ።
ቤሲግዬ ለምን ታፍኖ ተወሰደ? ጉዳዩስ የታቀደበት ነበር?
የኡጋንዳ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ክሪስ ባሪዮሙንሲ እንደሚሉት መርማሪዎች ቤስጊዬን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚያስችል በቂ መረጃ ስላላቸው ነው ናይሮቢ ውስጥ የታሰረው።
የኬንያ ባለሥልጣናት ስለጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም ቢሉም ሚኒስትሩ ግን የኬንያ ኃላፊዎች በድንበር በኩል እንዲያልፍ ፈቅደው ነበር ይላሉ።
የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ብሪጋዴር ጄኔራል ፌሊክስ ኩላይጊዬ ፖለቲከኛው ሊፈፅመው ያሰበው ወንጀል ኡጋንዳ ላይ ስለሆነ ነው ካምፓላ በሚገኝ ፍርድ ቤት ክሱ የሚታየው ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ነገር ግን ለምን በሕጋዊ መንገድ ፖለቲከኛው ለኡጋንዳ ተላልፎ እንዳልተሰጠ ማብራሪያ አልሰጡም።
ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ቤስጊዬን ይዞ ወደ ኡጋንዳ መውሰድ የሚለው ‘ኦፕሬሽን’ ለወራት የታሰበበት እና ለሱ ቅርብ በሆኑ ሰዎች እርዳታ ጭምር የታገዘ ነው።
የኡጋንዳ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት ብሪታኒያዊ የተባለው ሰውዬ እና የኡጋንዳ ጦር ኃይል ባለሥልጣን የቤስጊዬ የቅርብ ሰዎች ናቸው።
ዊኒ እንደምትለው ብሪታኒያዊ የተባለው “ገንዘብ ተከፍሎት ቤስጊዬ ሽጉጥ ይዟል እንዲባል ያደረገ” ሰው ነው።
ቤሲግዬ ወታደራዊ ችሎት ፊት የሚቀርበው ለምን ይሆን?
ባለፉት አስርታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ኡጋንዳዊያን ወታደራዊ ችሎት ፊት ቀርበው ያውቃሉ። ነገር ግን የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ይህን አይፈቅድም።
ለወታደራዊ ችሎት አዲስ ያልሆነው ቤስጊዬ እና ጓደኛው የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት፣ ጄኔቫ፣ አቴንስ እና ናይሮቢ ከሚገኙ ሰዎች የጦር መሣሪያ ለመግዛት በማቀድ የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች ክሱን ያስተባብላሉ።
ቤስጊዬ እና ጠበቃዎቹ ጉዳዩ በወታደራዊ ችሎት ሊዳኝ አይገባውም ቢሉም ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ሳይቀበል ቀርቷል።

ቤሲግዬ በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ኡጋንዳ እንዲወስድ ፈቅዷል የተባለው የኬንያ መንግሥት ከሀገር ውስጥ ከኡጋንዳ ብዙ ትችቶች እያስተናገደ ይገኛል።
አንዳንድ ኡጋንዳዊያን ካምፓላ በሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ አቅራቢያ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የኬንያን ምርቶች አንገዛም ሲሉ ተደምጠዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት አራት ስደተኛ ቱርካዊያን ኬንያ ውስጥ ተይዘው በግዴታ ወደ አንካራ እንዲወሰዱ መደረጋቸው ይታወሳል። ቱርካዊያኑ በፕሬደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ላይ አሢረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።