ታይፕ 00 የተባለው አዲሱ የጃጉዋር ኤሌክትሪክ መኪና
የምስሉ መግለጫ,ታይፕ 00 የተባለው አዲሱ የጃጉዋር ኤሌክትሪክ መኪና

ከ 7 ሰአት በፊት

ውድ የቤት መኪናዎች በማምረት የሚታወቀው ጃጉዋር አዲስ የኤሌክትሪክ መኪና ዲዛይን ይፋ አድርጓል።

ድርጅቱ ከቀናት በፊት ይህን መኪና ለማስተዋወቅ በሚል የለቀቀው ማስታወቂያ በብዙዎች ዘንድ አከራካሪ ሆኖ ነበር።

ታይፕ 00 የተባለው የኤሌክትሪክ መኪና ይፋ ሲደረግ ማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች በሁለት ጎራ ተከፋፍለው ሐሳባቸውን ሲሰጡ ታይተዋል። ግማሹ የአዲሱን መኪና ዲዛይን ወዶታል፤ የተቀረው ደግሞ እምብዛም አይደለም ብሏል።

ባለፈው ወር ኩባንያው አዲሱን የመኪና ዲዛይን ለማስተዋወቅ የለቀቀው ቪድዮ ምንም መኪና አይታይበትም የሚል ወቀሳ ገጥሞት ነበር። ሌሎች ደግሞ ኩባንያው በድፍረት መሰል ማስታወቂያ መሥራቱ ጎልቶ እንዲወጣ ያደርገዋል ብለዋል።

መኪና አምራቹ ኩባንያ “በለውጥ ጎዳና ላይ ነኝ” ያለ ይመስላል። አዲሱን የኤሌክትሪክ መኪና ይፋ ከማድረጉ በፊት ‘ሎጎ’ መቀየሩን አስታውቋል።

ሰኞ ዕለት በአሜሪካዋ የባሕር ዳርቻ ከተማ ማያሚ በተዘጋጀ ፕሮግራም ነው ታይፕ 00 ለሕዝብ ይፋ የሆነው።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጌሪ ማክገቨርን ድርጅታቸው “በአዲስ መልክ ሥራ መጀመሩን” ለታዳሚው ይፋ አድርገዋል።

“እኛ በሁሉም ዘንድ እንወደድ ብለን ሙጥኝ አንልም” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።

እንደተለመደው ማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች በሁለት ጎራ ተከፍለው በአዲሱ ዲዛይን ዙሪያ ሲነታረኩ ተስተውለዋል።

ታይፕ 00 የተባለው አዲሱ የጃጉዋር ኤሌክትሪክ መኪና

አንዳንዶች “መቼም ይሄን ይዛችሁ ገበያ አትወጡም” ሲሉ የተቀሩት ደግሞ መኪናው ገበያ ላይ እስኪውል “በደስታ እየተጠባበቁ” እንደሆ ፅፈዋል።

በመኪና ኢንዱስትሪው ጥርሳቸውን የነቀሉ ባለሙያ ናቸው የሚባሉት ካርል ብራወር ኩባንያው ስሙን እንደ አዲስ ለመገንባት የጀመረው መንገድ ብዙም የተዋጠላቸው አይመስልም።

ኩባንያው “ያለፈውን ታሪኩን ቀብሮ የወደፊቱን ለማሳመር እየሞከረ ይመስላል” ሲሉ ለቢቢሲ የሚናገር ካርል “የሚሳካላቸው አይመስለኝም” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጃጉዋር የውድ መኪናዎቸ አምራች ኩባንያ ላለፉት 102 ዓመታት ምርቶቹን ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል።

ባፈለው የአውሮፓውያኑ ኅዳር ወር ጃጉዋር ላንድ ሮቨር አዳዲስ መኪናዎችን ከዚህ በኋላ አንሸጥም ብሎ ከ2026 ጀምሮ የኤሌክትሪክ መኪና ብቻ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

በብሪታኒያ ሶስት መኪና ማምራቻ ፋብሪካዎች ያሉት ጃጉዋር በ2021 ነው ኤሌክትሪክ መኪናዎችን ማምረት መጀመሩን ያስታወቀው።

ጃጉዋር የጃጉዋር ላንድ ሮቨር ቡድን አካል ሲሆን ንብረትነቱ የታታ ሞተርስ ነው።

በታታ ሞተርስ የሚመረቱት ሬንጅ ሮቨር እና ዲፌንደር የተባሉት መኪናዎች ከ2015 ጀምሮ እጅግ ተወዳጅ እና ለድርጅቱ ትርፍ እያጋበሱ ያሉ መኪናዎች ናቸው።