
ከ 6 ሰአት በፊት
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተው ኢፕስዊች ታውን አምበል የሆነው ሳም ሞርሲ “በሃይማኖቱ ምክንያት” የቀስተ ደመና ኅብረ ቀለማት ያሉትን የአምበሎች መለያ አላደርግም ማለቱ ተሰማ።
ኢፕስዊች ባለፈው ቅዳሜ ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር በነበረው ጨዋታ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን የአምበሎች መለያ ሳያጠልቅ ነው ሜዳ የገባው።
የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ለመተሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን [ኤልጂቢቲኪው+] ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት አምበሎቻቸው የቀስተ ደመና ኅብረ ቀለማት ያሉት መለያ ክንዳቸው ላይ እንዲያጠልቁ አድርገዋል።
ይህ ዘመቻ ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 29 እስከ ረቡዕ ታኅሣሥ 5 የሚዘልቅ ነው።
ኢፕስዊች በኖቲንግሀም 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ የ33 ዓመቱ ግብፃዊ አምበል ይህን መለያ ክንዱ ላይ ያላደረገው “በሃይማኖቱ ምክንያት ነው” ሲል ክለቡ አስታውቋል።
- በአዲስ አበባ ከታህሳስ ጀምሮ የባንክ አካውንት ለመክፈት የ’ፋይዳ’ መታወቂያ ማቅረብ ግዴታ ሊሆን ነው2 ታህሳስ 2024
- ከኒው ዮርክ ወደ ፓሪስ ሳትከፍል ተደብቃ የበረረችው ግለሰብ ማንነቷ ታወቀከ 7 ሰአት በፊት
- የጃጉዋር አዲሱ የኤሌክትሪክ መኪና መነጋገሪያ ሆነከ 7 ሰአት በፊት
ኢፕስዊች ማክሰኞ ምሽት ከክሪስታል ፓላስ ይጫወታል።
ክለቡ በለቀቀው መግለጫ “አካታች እና ሁሉን የሚቀበል ክለብ” ለመሆን ያለውን ቁርጠኝነት አሳውቆ የአማካዩን ውሳኔም እንደሚያከብር ይፋ አድርጓል።
“የፕሪሚዬር ሊጉን በቀስተ ደመና ኅብረ ቀለማት የተሠራውን የአምበሎች መለያ በኩራት እንደግፋለን፤ ከኤልጂቢቲኪው+ ማኅበረሰብ ጋር አብረን እንቆማለን፤ እኩልነት እና ተቀባይነት እንዲንሰራፋ እንሠራለን” ይላል ክለቡ ሰኞ የለቀቀው መግለጫ።
ከኢፕስዊች ታውን አምበል ሳም ሞርሲ በስተቀር ሌሎች የፕሪሚዬር ሊጉ አምበሎች ይህን የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን ባንዲራ አጥልቀው ሲጫወቱ ታይተዋል።
የኢፕስዊች ታውን አማካይ እና አምበል የሆነው ሳም ሞርሲ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነው።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ስቶንዎል ከተሰኘው የእርዳታ ድርጅት ጋር በመጣመር ነው አምበሎች ይህን ባንዲራ እንዲያጠልቁ የሚያደርገው።
አሁን ለኤቨርተን የሚጫወተው ሴኔጋላዊው አማካይ ኢድሪሳ ጋና ጉየ ለፓሪ ሳን ዠርማ በሚጫወትበት ወቅት በተመሳሳይ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን ባንዲራ አላጠልቅም ማለቱ ይታወሳል።