
ከ 3 ሰአት በፊት
የመቀለ ማዕከላዊ ፍርድ ቤት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ያለው ተከሳሽ ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ አስተላለፈ።
በ16 ዓመቷ ማኅሌት ተኽላይ ላይ የግድያ ወንጀል በመፈፀም ተከሰው በእስር ላይ ከሚገኙት ሁለት ግለሰቦች መካከል የሞት ፍርድ የተፈረደበት አወት ነጋሲ የተባለው ተከሳሽ እንደሆነ ተገልጿል።
ሁለተኛው ተከሳሽ ናሆም ፍፁም ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።
የ16 ዓመቷ ማኅሌት መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ. ም. በዓድዋ ከተማ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት ስትሄድ ታግታ ለቀናት ከቆየች በኋላ መገደሏ ይታወሳል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት በክልሉ ከፍተኛ ቁጣ ማስነሳቱም አይዘነጋም።
ተከሳሾቹ ታዳጊዋን “በአሰቃቂ ሁኔታ አንቀው በማሰቃየት ገድልዋታል” ሲል የመቀለ ማዕከላዊ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል።
ማኅሌት ከተቀበረች ከሦስት ቀናት በኋላ አንደኛው ተከሳሽ አወት፣ ወደ አባቷ አቶ ተኽላይ ስልክ በመደወል 3 ሚልዮን ብር እንዲከፍሉት ጠይቆ ልጃቸውን እንደሚመልስላቸውም ተናግሮ ነበር።
ሁለተኛው ተከሳሽ ናሆምም ከአንደኛው ተከሳሽ ጋር ተባባሪ በመሆን ድርጊቱን ፈጽሟል ያለው ዐቃቤ ሕግ፣ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የሞት ቅጣት እንዲወሰን ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
የማኅሌት አባት አቶ ተኽላይ ግርማይ “ከብዙ ጥረት እና ድካም በኋላ የተሰጠው ፍርድ ተገቢ እና ፍትሐዊ ነው” ሲሉ መግለጻቸውን የትግራይ ቴሌቭዥን ዘግቧል።
- በአድዋ ከተማ ባልታወቁ ሰዎች ታግታ ሦስት ሚሊየን ብር የተጠየቀባት ታዳጊ10 ሚያዚያ 2024
- የትግራይ ከተሞች ነዋሪዎችን በፍርሃት እያራደ ያለው የእገታ እና የዘረፋ መበራከት11 ሰኔ 2024
- ፍትህን የሚሹት በወጡበት እየቀሩ ያሉት የትግራይ ሴቶች9 ሀምሌ 2024
በተለይም ደግሞ ባለፈው ዓመት በክልሉ ተመሳሳይ ወንጀሎች በብዛት የተፈጸሙ ሲሆን፣ አቶ ተኽላይ “በሌሎች ላይ ለተፈፀመው ግድያም ተጠያቂነት መረጋገጥ አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል፣ አድዋ ከተማ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግታ የነበረችው ማኅሌት ተኽላይ ተገድላ መቀበሯን ተከሳሾቹ ማመናቸውን የከተማዋ የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋይ አማረ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ትግርኛ መግለጻቸው ይታወሳል።
የታዳጊዋ አስከሬን ከሦስት ወራት በኋላ ከተጠርጣሪዎች በተገኘ ጥቆማ መሠረት ከተቀበረበት ተቆፍሮ ወጥቷል።
የ16 ዓመቷ ማኅሌት በአድዋ ከተማ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ. ም. ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግታ መወሰዷን ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ማኅሌት አመሻሽ ላይ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት ስትሄድ መታገቷን እህቷ ሚሊዮን ተኽላይ ተናግራም ነበር።
ተከሳሾቹ ማኅሌትን ለመልቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲከፈላቸው ለመጠየቅ ወደ አባቷ ሁለት ጊዜ ስልክ ደውለው እንደነበር እህቷ መናገሯ አይዘነጋም።