ዩኒቨርስቲው ከአፍሪካ ጋር የተገናኙ የተለያዩ ቅርሶች፣ ከአፍሪካውያን ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ለተጨማሪ ጥናቶች መሠረት ይሆናሉ የሚል እምነት አለው።
የምስሉ መግለጫ,ዩኒቨርስቲው ከአፍሪካ ጋር የተገናኙ የተለያዩ ቅርሶች፣ ከአፍሪካውያን ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ለተጨማሪ ጥናቶች መሠረት ይሆናሉ የሚል እምነት አለው።

ከ 35 ደቂቃዎች በፊት

በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ መጋዘን ውስጥ 350,000 መሆናቸው የተገመተ የአፍሪካ ቅርሶች፣ የእጅ ጽሑፎች፣ የሰው ቅሪተ አካሎች፣ ፎቶግራፎች እና የተፈጥሮ ታሪክ ናሙናዎች ተገኙ።

ዩኒቨርሲቲው ካከማቻቸው ስብስቦች ውስጥ ግብፅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርኪዎሎጂያዊ ቅርሶች እና የእጅ ጽሑፎች ያላት አፍሪካዊ አገር ነች ተብሏል።

ዶ/ር ኢቫ ናሙሶኬ ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ቅርሳ ቅርሶቹን ለመለየት ከዩኒቨርስቲው የቤተ-መጻሕፍት ሠራተኞች፣ አስተዳዳሪዎች፣ ቤተ-መዛግብት አስተዳዳሪዎች እና ሰናጆች ጋር በመሆን በመጋዘናቸው ውስጥ ለ15 ወራት ማሳለፋቸው ተገልጿል።

ትላልቅ ሙዚየሞች ያላቸውን ስብስቦች በሙሉ አለማሳየታቸው “በጣም የተለመደ ነው”፤ ነገር ግን “በዚህ መጠን እና ዓይነት ከመላው አፍሪካ አህጉር እንዲሁም አንዳንዶቹ ቅርሶች ለበርካታ አስርታት ዓመታት ተቀምጠው መገኘታቸው አሁንም የሚያስገርም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው በቅርብ ጊዜ ሙዚየሙ ከቅኝ ግዛት እና ከባርነት ጋር ተያይዞ የሚነሱበትን ጥያቄዎች ለመቅረፍ የተጀመረ ሲሆን፣ እግረ መንገዱንም አብዛኞቹ ቅርሶች በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወቅት የተገኙ መሆናቸውን አሳይቷል።

የፊትዝዊሊያም ሙዚየም ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ናሙሶኬ ከአፍሪካ ጋር የተያያዙ አብዛኞቹ ቅርሶች አሁንም ለሕዝብ ዕይታ አይቀርቡም።

አሁን ግን በስፋት ለዕይታ እንደሚቀርቡ እና ጥናት እና ምርመር እንደሚሠራባቸው ባለሙያዋ ተስፋ አድርገዋል።

እነዚህ ቅርሳ ቅርሶች በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኙት ስምንት ሙዚየሞች፣ በዕፅዋት ሙዚየም እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ቤተመጻሕፍት እና ስብስቦች እንዳሏቸው እምብዛም በማይታወቁ የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ክፍሎች እና ተቋማት ውስጥ ነው የተገኙት።

በቅኝ ግዛት አስተዳዳሪ ከተበረከቱት የማሳይ ጎሳ አባላት የክንድ አንባሮች ጀምሮ፣ በቦር ጦርነት (1899-1902) በማጎሪያ ካምፕ ከተሰበሰቡ ትንንሽ አጥቢ እንስሳት፣ የመካከለኛው ዘመን የአይሁድ የእጅ ጽሑፎች ስብስብ እና የአፍሪካ ሕዝቦችን የሚያሳዩ የመጀመሪያ ፎቶግራፎች ከተገኙት መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።

በቅኝ ግዛት ወቅት የተዘረፈ የአንገት ሀብል
የምስሉ መግለጫ,በቅኝ ግዛት ወቅት የተዘረፈ የአንገት ሀብል

ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ጋር ያለው ግንኙነት

አብዛኞቹ ቅርሶች የተወሰዱት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወቅት ነው፤ አንዳንዶቹ በስጦታ የተበረከቱ፣ የተገዙ፣ በቁፋሮ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ የተዘረፉ፣ የተወረሱ እና የተመዘበሩ ናቸው።

በዩኒቨርስቲው አርኪዮሎጂ እና አንትሮፖሎጂ ሙዚየም ከጋና የመጣ የወርቅ ሀብል ያለ ሲሆን፣ በሦስተኛው የአንግሎ-አሳንቴ ጦርነት ወቅት፣ በአሳንቴሄኔ ኮፊ ካሪካሪ ቤተ መንግሥት በ1873-4 እንደተዘረፈ ይገመታል።

በተጨማሪም እንግሊዝ በ1897 በአሁኑ ደቡብ ናይጄሪያ በዚያን ጊዜው ቤኒን ሥርወ መንግሥት ለቅጣት በሚል በወሰደችው እርምጃ የተዘረፉ 116 እቃዎች ተገኝተዋል።

ዶ/ር ናሙሶኬ እንዳሉት “በዓለም ዙሪያ ባሉ ብዙ ሙዚየሞች ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በዚህም እንደዚህ ዓይነት ቅርሶችን እንደማገኝ ጠብቄ ነበር” ብለዋል።

“ዩኒቨርሲቲው የዶዶ (እንስሳ) ቅሪተ አካልን ያገኘው በካምብሪጅ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሰው እና በሞሪሺየስ ውስጥ ባለው የቅኝ ገዢ አስተዳዳሪ መካከል ባለው ግለሰባዊ ግንኙነት አማካኝነት ነው” ትላለች።

“ከአንትሮፖሎጂ እና የቅኝ ግዛቶች አስተዳደር ጋር ጥምረት አለ፤ ማለትም ተመራማሪዎች ሕዝቡን እና ባህሉን ለማጥናት እና ለመመርመር መግባባት አላቸው።”

ይህንንም በመጥቀስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ይደረጉ የነበሩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማድረግ እና መረጃ መሰብሰብ ከቅኝ ግዛት ጋር “እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሄዱ ነበር” ትላለች።

በዩኒቨርሲቲው ስብስቦች ውስጥ ግብፅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርኪዮሎጂያዊ እቃዎች እና የእጅ ጽሑፎች ያላት አፍሪካዊ አገር ነች።
የምስሉ መግለጫ,በዩኒቨርሲቲው ስብስቦች ውስጥ ግብፅ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርኪዮሎጂያዊ እቃዎች እና የእጅ ጽሑፎች ያላት አፍሪካዊ አገር ነች።

የአፍሪካውያንን ጉልበት እና ዕውቀትን መግለጥ

የዶ/ር ናሙሶኬ መረጃ እንደሚያሳየው አፍሪካውያን ናሙናዎችን ወይም ቅርሶችን ለመሰብሰብ ስላደረጉት አበርክቶ፣ ስላካፈሉት ክህሎት፣ ዕውቀት በጣም በሚያስቆጭ መልኩ “ጥቂት” ብቻ ተሰንዷል።

“ከ1930ዎቹ ጀምሮ በካሜሩን ስለሆነው የምናገረው አንድ ምሳሌ አለ፤ ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው የአፍሪካውያን አቅም የጉልበት ሥራ ላይ መዋሉ ግልጽ ነው” ስትል ተናግራለች።

“ካሜሩናውያን ወንዶች እንስሳትን ተከታትለው በማደን፣ ሸረሪቶችን እና ቀንድ አውጣዎችን ለመሰብሰብ የሙከራ ቱቦዎች ይዘው፣ ለሰዓታት በሆዳቸው ተኝተው አሳልፈዋል።”

“ይህ ሙሉ በሙሉ የአካባቢ ጉልበት እና ዕውቀትን፣ ምሁራዊ፣ አካላዊ እና የፈጠራ ሥራን መጠቀም ነበር። ትኩረት የተደረገው ግን የመሰብሰቡን አድካሚ የጉልበት ሥራ የተወጡት ላይ ሳይሆን በአውሮፓውያን ሳይንቲስቶች ላይ ነው።”

ወደ 100,000 የሚጠጉ ከአፍሪካ የተወሰዱ ናሙናዎች በሥነ እንስሳት ሙዚየም ውስጥ የተቀመጡ ሲሆን፣ በዚህ ክፍል በጣም በጥቂቱ ጥናት የተደረገባቸው ስብስቦችም ይገኛሉ።
የምስሉ መግለጫ,ወደ 100,000 የሚጠጉ ከአፍሪካ የተወሰዱ ናሙናዎች በሥነ እንስሳት ሙዚየም ውስጥ የተቀመጡ ሲሆን፣ በዚህ ክፍል በጣም በጥቂቱ ጥናት የተደረገባቸው ስብስቦችም ይገኛሉ።

የተገኙትን ቅርሶች በጨረፍታ

ፕሮጀክቱ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተነሳሽነት የሚሠራ ሲሆን፣ ያሉትን ቅርሳ ቅርሶች ከማኅበረሰቦች ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በተለይም ከአፍሪካ ምሁራን እና ማኅበረሰቦች ጋር ተጨማሪ ምርምርን፣ ትብብርን እና ተሳትፎን ለማስተዋወቅ አቅዷል።

“የሚቀጥለው ትልቅ እርምጃ ግን ዕይታን መጨመር እና ስብስቦቹን ራሳቸው አፍሪካውያኑ እንዲመራመሩ መፍቀድ ነው” ብለዋል ዶክተር ናሙሶኬ።