ካሽ ፓቴል

4 ታህሳስ 2024

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኤፍቢአይ የተባለውን የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤትን እንዲመሩላቸው የመረጧቸው ሰው አከራካሪ ሆነዋል።

ሰውዬው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮን (ኤፍቢይ) ለመምራት ብቁ ናቸው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች መሰንዘር ጀምረዋል።

ካሽ ፓቴል፤ ትራምፕ በመጀመሪያ ዘመን ሥልጣናቸው ታማኝ ከሚሏቸው ባለሟሎች መካከል አንዱ ናቸው።

ፓቴል ኤፍቢአይ የተባለውን ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የፌዴራል መሥሪያ ቤት አፍርሰው ሊሠሩት ይፈልጋሉ ተብለው ይታማሉ።

የቀድሞው የኤፍቢአይ መርማሪ ጄፍ ላንዛ “ከቢሮው ሠራተኞች 99 በመቶ የሚሆኑት በታማኝነት፣ በትጋት እና ሥርዓታቸውን ጠብቀው የሚያገለግሉ ናቸው” ይላሉ።

“አሁን ሰውዬው መጥቶ መሥሪያ ቤቱን ድብልቅልቁን ሊያወጣው ይፈልጋል። ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ መሥሪያ ቤቱን ላገለገሉ ሰዎች ይህ ምን ማለት ነው?”

ኤፍቢአይ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ 55 ቢሮዎች 37 ሺህ ሠራተኞች አሉት። የኤፍቢአይ ዳይሬክተር እነዚህን ሠራተኞች በሙሉ ያስተዳድራል።

ኤፍቢአይ ከሀገር ውጭ ደግሞ 350 ‘ሳተላይት ኦፊስ’ የሚባሉ ጽህፈት ቤቶች ሲኖሩት በ200 ሀገራት ከ60 በላይ ቢሮዎች እንዳሉት ይነገራል።

ቢቢሲ ያናገራቸው የኤፍቢአይ እና የፍትሕ ቢሮ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ቢሮውን ማስተዳደር ቀላል አይደለም፤ እንዲህ ያለውን ተቋም እንደ ፓቴል የማስተዳደር ልምድ የሌላቸው ሰዎች የሚወጡት አይሆንም።

የቀድሞው የኤፍቢአይ ምክትል ዳይሬክተር ግሪጎሪ ብራወር ካለፉት ሁለት የቢሮው ዳይሬክተሮች ጋር አብረው ሠርተዋል። ሥራው “እረፍት የለውም” ይላሉ።

“እረፍት አልባ ነው። ብዙ ነገሮች ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው። ብስለት የተሞላበት የውሳኔ አቅም ይጠይቃል። ጥንካሬ፣ ልምድ እንዲሁም የዳበረ ሥነ-ምግባር እና ሞራል ሊኖር ይገባል” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

“ካሽ [ፓቴል] ማለት ሕግ አዋቂ፣ መርማሪ እና ‘ቅድሚያ ለአሜሪካ’ የሚል፤ ዕድሜውን በሙሉ ሙስናን በመታገል፣ ለፍትሕ በመቆም እና አሜሪካውያንን በመጠበቅ የኖረ ሰው ነው” ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ጽፈዋል።

በመጀመሪያው የትራምፕ አስተዳደር የመከላከያ መሥሪያ ቤት የጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ፓቴል የትራምፕ ታማኝ ባለሟል እና ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው።

ፓቴል የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆነው የሚሾሙት የአሁኑ ኃላፊ ክሪስቶፈር ሬይ ሥራ ከለቀቁ አሊያም ከተባረሩ ነው። ትራምፕ ሹመታቸውን ባሳወቁበት ደብዳቤ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ያሉት ነገር የለም።

ፓቴል የፌዴራል ጠበቃ ሆነው ሥራቸውን የጀመሩት በማያሚ ክፍለ ግዛት ነበር። ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2017 ባለው ጊዜ በፍትሕ ሚኒስቴር የሽብርተኝነት ዐቃቤ ሕግ ሆነው አገልግለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,ዶናልድ ትራምፕ

ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የሪብሊካን ፓርቲ ነባር አማካሪ ነበሩ። በወቅቱ ትራምፕ ከሩሲያውያን ጋር ሠርተዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በ2019 ዲሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በበላይነት ሲቆጣጠሩ ፓቴል የትራምፕ ብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ ሆነው ተሾሙ። በየካቲት 2020 ደግሞ የብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ተቀጠሩ።

በተመሳሳይ ዓመት በወርሃ ኅዳር ወደ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) በማምራት በወቅቱ ጊዜያዊ የመካላከይ ሚኒስትር ለነበሩት ክሪስቶፈር ሚለር የጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።

የትራምፕ የሽግግር አስተዳደር ቃል-አቀባይ የሆኑት አሌክስ ፋይፈር “ካሽ ፓቴል በጣም ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሠርተዋል። እሳቸው ለቦታው ከብቁ በላይ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ፓቴል ለቦታው ብቁ አይደሉም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ከዚህ ቀደም የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሰዎች ለአስርት ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ያገለገሉ መሆናቸውን በምሳሌነት ያነሳሉ።

ፓቴል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እየቀረቡ አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ። ትራምፕ ወደ ሥልጣን የሚመጡ ከሆነ “በ2020 ምርጫው እንዲጨበረበር ያገዙ ፖለቲከኞች እና የሚዲያ ሰዎችን” እንደሚያሳድዱ ተናግረው ያውቃል። የ2020 የአሜሪካ ምርጫ ስለመጭበረበሩ ግን ማስረጃ አላቀረቡም።

“መገናኛ ብዙኃን ውስጥ ያሉ አሜሪካውያንን የዋሹ ሰዎችን እናድናቸዋለን። ጆ ባይደን ምርጫውን እንዲያጨበረብሩ አድርገዋል” ሲሉ ተናግረው ያውቃሉ።

ካሽ ፓቴል ከዚህ ቀደም ኤፍቢአይን ማስተካከል በሚል ባቀረቡት ሐሳብ ቢሮው ኃላፊነቱ “እንዲገደብ” እና “ዋና ዋና ሰዎች እንዲባረሩ” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ካሽ ፓቴል
የምስሉ መግለጫ,ካሽ ፓቴል

‘ገቨርንመንት ጋንግስተርስ’ በተሰኘ ርዕስ ካወጡት የግለ-ሕይወት መጽሐፍ በተጨማሪ ሁለት ትራምፕን የሚያወድሱ የሕፃናት መጽሐፍት አሳትመዋል። ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ከተመረጡ ይህን መጽሐፍ እንደ “መመሪያ” እንደሚጠቀሙበት ተናግረው ያውቃሉ።

ፓቴል በቅርቡ አንድ ፖድካስት ላይ ቀርበው ቀጣዩ የትራምፕ አስተዳደር ዋሺንግተን ከሚገኘው የኤፍቢአይ ቢሮ 50 ሰዎች ብቻ ቀርተው ሌላው ሠራተኛ ወደ መስክ እንዲሰማራ አደርጋለሁ ብለው ነበር።

የኤፍቢአይን ዋና መሥሪያ ቤት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ሕንፃውን እንደሚያፈርሱት” ተናግረዋል።

ኤፍቢአይ ዕጩው የቢሮው ዳይሬክተር የተናገሩትን በተመለከተ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

የተባረሩት የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚን ተክተው በትራምፕ የተሾሙት ክሪስቶፈር ሬይ የሥልጣን ዘመናቸው ሊገባደድ ሦስት ዓመታት ይቀራቸዋል።

ካሽ ፓቴል ቀጣዩ የትራምፕ አስተዳደር የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆነው ሥራ የሚጀምሩት የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔቱ) ሹመታቸውን ሲያፀድቅ ነው።